Christmas Vs ገና Vs Nativity – ክፍል ሁለት

Christmas Vs ገና Vs Nativity – ክፍል ሁለት

ለመሆኑ ሁለት የገና (ክሪስመስ) በዐል ለምነው የምናከብረው?             በምድር ዘመን አቆጣጠር ክርስቶስ መቼ ተወለደ?

የክሪስማስ (ገና) በዐል ማክበሪያ ልምዶች ከየት የተገኙ ይሆን?            ታህሳስ 25 እንዴት መከበር ጀመረ?

የመጀመሪያው የተዘገበ የኔቲቪቲ (ክሪስማስ) በአል የትና መቼ ነበር?      የልደት በዐልስ ስለምን ማክበር ይገባናል?

To Read in PDF

ጌታችንና መድኃኒታችን የNativity essay 3 To Read In PDFኢየሱስ ክርስቶስ የመወለዱን ዜና ባነሣንበት ጽሑፋችን የልደቱን በዓል ጥንተት፣ ምክንያተ ጥንተት፣ ፈርና ትርጉም ያጣ አከባበሩን ለማውሳት በመጀመሪያው ክፍል ሐተታ ጀምረን ነበር፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶልን ቀጣዩን ክፍል እንዲህ አዘጋጅተነዋል፡፡

የመጀመሪያው ክፍል የጌታን ልደት ጥንተት (መነሻ) ስናቀርብ ጥቅልና ሰብስብ ባለ ሐሳብ ነበርና በዚህ ክፍል እርሱን ከመዘርዘር እንጀምራለን፡፡ እንዲሁም የጽሑፋችንን መነሻዎች ከመጨረሻው ክፍል ዋቢ ለማቅረብ አሳባችን ቢሆንም ፍላጎታችሁን ለማደስ በየክፉሉ የግርጌ ማስታወሻ ለመተው መርጠናል፡፡ ሠናይ ንባብ..

የዓመቱ ጊዜ ያልተረጋገጠ ነው፡፡ በምዕራብ ሃገራት ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ታህሳስ 25 ከ4ኛ መ/ክ/ዘ በኋላ የመጣ ልማድ ነው፡፡ በየግሪክ ቤ/ክ ተቀባይነት ያለው (ጥር 6) በእኛ ቤ/ክ ጥር 7 (እ.ኤ.አ) የሚከበረው የተሻለ የቆየ ልማድ ቢሆንም አንዳቸውም አስተማማኝ ማስረጃ (ማረጋገጫ) የላቸውም፡፡ የካቶሊክ ቤ/ክ ባህረ ጥበባት መደምደሚያ በምስራቅ ሆነ በምዕራብ የበዓሉ መነሻ የክረምት አጋማሽ ሰፊ ጊዜ የሚወስዱት በዓላት የጊዜ አመችነት የታህሳስ ወርን ለመምረጥ አግዞ ሊሆን ይችላል፡፡ የማይሸነፈውን ፀሐይ አምላክ ልደት ቀን እንደ ወሰኑት (ሆን ተብሎ የተወሰደ ወይም ታቅዶበት የተቀመረ ባሆንም) ክርስቲኖችም በዓላቸውን ወስነው ይሆናል ይላል፡፡[1][2]

ቅዱስ ማቴዎስ[3] ክርስቶስ በሄሮድስ የንግስና ዘመን እንደተወለደ ይነግረናል፡፡ ጆሴፈስ[4] ደግሞ ሄሮድስ ሀገሪቷን ለ34 ዓመት እንደማስረጃዎች (de facto) 37 ዓመት እንደህግ (de jure) ከመራት በኋላ እንደሞተ ይነግረናል፡፡ ሄሮድስ የይሁዳ ገዢ የነበረው በAUC 714 ሲሆን ትክክለኛ የመሪነት ዘመኑ የጀመረው ኢየሩሳሌምን በAUC 717 ከያዘ በኋላ ነው፡፡ እስራኤላውያን ወራቸውን ከኒሳን እስከ ኒሳን[5] ስለሚቆጥሩ ትናንሽ ክፍለ ጊዜያትንም እንደ አጠቃላይ ዓመት ስለሚቆጠሩ ከላይ የተጠቀሰውን የሄሮድስን ሞት በAUC 749፣ 750፣ 751 ያደርገዋል፡፡ ጆሴፈስ እንደሚለው የፀሐይ ግርዶሽ የተከሰተው ከሄሮድስ ሞት በፊት ብዙም ሳይርቅ ሲሆን ይህ ግርዶሽ የተከሰተው 12-13 መጋቢት AUC 750 ነው፡፡[6] ስለዚህም ሄሮድስ በዛው ዓመት ሚያዝያ 12 ከነበረው የፋሲካ/የቂጣ በዓል (passover) ቀድሞ መሞት ነበረበት፡፡[7] ሄሮድስ አዲስ የተወለደውን ህጻን ለማጥፋት እስከ ሁለት ዓመት የሞላቸው ህጻናት እንዳስገደለ በመጻፉ የክርስቶስን ልደት AUC 747፣ 748 ወይም 749 ሊሆን እንደሚችል ወደ ማመን ይወስደናል፡፡[8]

ዮሐንስ አፈወርቅ (386 አካባቢ) የኤልሳቤጥን የ6 ወር የመጥምቁ ዮሐንስን እርግዝና ከብስራተ ገብርኤል ጋር በማያያዝ ወንጌላዊው ሉቃስ በተዘዋዋሪ መንገድ የክርስቶስን ልደት ታህሳስ አድርጎ እንዳስቀመጠው ይገለጻል፡፡[9][10][11][12] በተጨማሪም ዮሐንስ አፈወርቅ ለአንቲዎች ባቀረበው ስብከት ወቅት የክርስቶስ መጸነስ[13] የተነገረው በኤልሳቤጥ 6ኛ ወር እርግዝና[14] ወቅት መሆኑን ዘካሪያስ የሚያገለግልበት እጣ የወጣለትን ጊዜ አጣቅሶ ታህሳስ 25 መከበር እንዳለበት አስረድቷል፡፡

የቤተክርስቲያን ታሪክ አባት የሚባለው ታሪክ ጸሐፊው አውሳብዮስ ዘቂሳሪያ “በአውግስጦስ 42 የግዛት ዘመን፣ ግብጽ ተወራ እጇን ከሠጠችበትና ከክሊዮፓትራ ሞት 28 ዓመት በኋላ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም ይሁዳ ተወለደ.”[15] በማለት ዘግቧል፡፡ አውሳብዮስ የአውግስጦስን ዘመን ጅማሬ የጁልየስ ቄሳር ሞትን ተከትሎ እንደሆነ በማመኑ (ጆሴፈስ[16] በዚህ ይስማማል) የክርስቶስን ልደት በ752 AUC አድርጎታል (2 BC) ፡፡ በዚህ ሐሳብ ከእስክንድርያው ቅሌሜንጦስ (ከግብጽ መሸነፍ 28ኛ ዓመት ላይ የክርስቶስን ልደት በማድረጉ)፣ ኤጲፋንዮስና አሮሲነስ ጋር በአንድነት ይስማማሉ፡፡ ኦረንየስና ተርቱሊያን በሌላ መንገድ በአውግስጦስ 41ኛ ዓመት በ751 AUC (3 BC) ነው ብለዋል፡፡[17]

የአውሳብዮስ መጽሐፍት እንግሊዘኛ ትርጉም ኤዲተር ፒ. ስካፍ የእራሱን ማጠቃሌ ሲጽፍ “ነገር ግን እነዚህ ሁሉም ቀናት በእርግጠኝነት ብዙ የዘገዩ ናቸው” ብሏል፡፡ ትክክለኛው የክርስቶስ ልደት ዓመት ምንግዜም የክርክር ምንጭ ቢሆንም ልደቱ በ 750 AUC (4 BC) ጸደይ ወራት ከሞተው ከሄሮድስ አስቀድሞ የግድ መፈጸም ይኖርበታል፡፡ ተቀባይነት ካገኙት ሁሉ በብዛት ስምምነት ላይ የደረሰው ሀሳብ ቢዘገይ በ5ኛ ወይም በ4ኛ BC መጀመሪያ የሚለው ነው፡፡ ምንም እንኳ አንዳንድ ሊቃውንት አመቱን እስከ 7 BC ቢያርቁትም፡፡[18]

ዊኪፕዲያ ላይ የመሐለኛው ዘመን ገለጻ ከሆነው ከሆርተሪያና ሄራልድ ኦፍ ላንድስበርግ (12ኛ መ/ክ/ዘ) ላይ ወስዶ ክሪስማስን ለመግለጽ በቀረበው ዘገባ ኢራንየስ (130-202 አካባቢ) የእመቤታችንን መጸነስ መጋቢት 25 በማድረግ ዘጠኝ ወር ቆጥሮ ልደቱን በታህሳሰ 25 አድርጎታል፡፡[19] ሂፖሊተስ ሮማዊ (170-235) በኢራንየስ ሐሳብ በመስማማት ቀመሩን እንደእርሱ ገልጾታል፡፡[20][21] እንዲሁም ጁሊየስ አፍሪካነስ (160-240 አካባቢ) በ221 በተጻፈው የማጣቀሻ መጽሐፉ Chronographai [22] ላይ እመቤታችን በጸደይ ወራት የቀንና ሌሊት ሰዓት እኩል በሚሆኑበት ወቅት እንደጸነሰች ያለውን ግምንት ያስቀመጠ ሲሆን[23][24] በሮማውያን የቀን መቁጠሪያ የቀንና ሌሊት ሰዓት እኩል የሚሆንበት መጋቢት 25 በመሆኑ ልደቱ ታህሳስ እንደሚሆን ግልጽ እንደሆነ ጽፏል፡፡[25][26]

የዊኪፕዲያ በማስረጃ የታገዘ መረጃ እንደሚገልጸው ትክክለኛ የክርስቶስ ልደት ታህሳስ 25 የተወሰነበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ በተጨማሪም እንደዘገበው የተለያዩ መረጃዎች ግንቦት 20፣ ሚያዝያ 18 ወይም 19፣ መጋቢት 25፣ ጥር 2፣ ጥቅምት 17 ወይም 20 እንደሆነ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡[27][28]

ዝነኛ የነበረውና በታህሳስ 25 የሚከበረው የፀሐይ አምላክ ልደት በዓል የክሪስማስ ቀንን በመወሰን ታላቅ ድርሻ እንደተወጣ ይታመናል፡፡[29] ይህ በዓል ዝነኛነቱ ጣራ የነካው በሮማው ገዢ ዩሬሊየን ዘመን በ274 ሲሆን በ4ኛ ክ/ዘ ዮሐንስ አፈወርቅ በ”del Solst. Et Æquin.” (II, p. 118, ed. 1588), እንዳለው “እንዴታ፣ የእኛ ጌታ በታህሳስ ወር …. 8ቀን ከጥር አስቀድሞ [ታህሳስ 25] ተወልዷል ….. እነርሱ ግን “የማይሸነፈው ልደት ነው” ይላሉ …… ታዲያ ከእኛ ጌታ ሌላ የማይሸነፍ ማነው ……? ወይም እነሱ የፀሐይ ልደት ነው ካሉም እርሱ የፍትህ [የጽድቅ] ፀሐይ ነው” ብሏል፡፡[30]

የካቶሊክ ባህረ ጥበባት (encyclopedia) የክርስቶስን የልደት ወርና ቀን ለመወሰን የተለያዩ ንድፈ ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡ ከቀረቡት ሃስብ መሐል የዘካሪያስ የመቅደስ አገልግሎት አንደኛው ሲሆን በዚህም አቆጣጠር ታህሳስ ወር የልደቱን ቀን አድርጎ ይወስናል ዳሩ ግን እዛው ጽሑፍ ላይ የዘካሪያስን የመቅደስ አገልግሎት መሠረት ያደረገ መከራከሪያ አስተማማኝ ያልሆነ እንደሆነ ይገልጻል፡፡[31][32][33] ሌላው የብሉይ ኪዳን ክብረ በዓላትን ንጽጽር ምሳሌ አድርጎ የሚወስደው የቀን ቀመር ሲሆን የፋሲካ/የቂጣ በዓል (passover)እና በዓለ አምሳ (Pentecost)፣ የትንሣኤና ሰንበት በዓል ጋር ልደቱን ከዳስ በዓል (tabernacles) ጋር በማነጻጸር በዘካሪያስና ዳንኤል ላይ የተገለጹት አቆጣጠሮች መሠረት በማድረግ ልደቱን በመስከረም ያደርጉታል፡፡[34][35]

በ18ኛው መ/ክ/ዘ አንዳንድ ምሁራን አማራጭ አስረጂዎችን ለማቅረብ ሞክረዋል አይዛክ ኒውተን ሮማውያን በታህሳስ 25 የሚያከብሩት ብሩማ[36] በዓል አያይዘው ፀሐየ ጽድቅ የተባለውን[37] ክርስቶስ የተወለደበት ቀን፤ የክሪስማስ ቀን እንዳከበሩ የእርሱን መከራከሪያ አቅርቧል፡፡[38]

የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጊዜ መስመር (chronology) ማጠቃለያ

የክርስቶስ የልደት ዓመት

በሮማዊው መነኩስ ዲዮናስዮስ ኤክስጂየስ የተዋወቀው የዓለም (የእኛን ጨምሮ) የክርስትና ዘመን የሁለት ክፍለ ዘመን ቆይታ በኋላ በቻርልማጅን[39] ዘመን የልደት (Nativity) ቀን ታህሳስ 25፣ AUC 754 አደረገው፡፡ ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ ይህ ቀን ቢያንስ በአራት ዓመት እንደተሳሳተ ይስማማሉ፡፡ ምናልባ ካልፈጠነ ክርስቶስ በAUC 750 (ወይም BC 4) ተወልዷል፡፡ ይህንንም ከሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ የጊዜ መስመር (chronology) ማስረጃዎች ፣ከጆሴፍና የጊዜው ጸሐፊያን (contemporary writers) እንዲሁም ከሥነ ፈለካዊ ጥናት ቀመር (astronomical calculation) ማረጋገጫዎች ጋር በማነጻጸር እናቀርባለን፡፡ ለዚህ ድጋፍ የ ፊሊፕ ስካፍ የክርስቲያን ቤ/ክ ታሪክ፡ ሐዋሪያዊት ክርስትና ከ AD 1-100 ከሚለው መጽሐፉ ሐሳብ እንዋሳለን፡፡

የሄሮድስ ሞት

እንደ ማቴዎስ 2÷1 (ሉቃ 1÷5፣ 26 ጋር አነጻጽር) ክርስቶስ የተወለደው ‘በንጉስ ሄሮድስ ቀዳማዊ ወይም ታላቁ ዘመን ነው’ እንደ ጆሴፈስ ገለጻ ሄሮድስ ለ37 ዓመት[40] ከገዛ በኋላ ከፋሲካ/የቂጣ በዓል በፊት በ70ኛ ዓመቱ በኢያሪኮ AUC 750 ሞቷል፡፡ ይሄም ቀን የተረጋገጠው በመጋቢት 13፣ AUC 750 ከሄሮድስ መሞት ጥቂት ቀናት በፊት የተገለጠው የፀሐይ ግርዶሽ[41] በሥነ ፈለክ ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡

በሄሮድስ ሕጻናት የተገደሉበትና በክርስቶስ ልደት መሐል 2 እና ከሁለት ወር በላይ ቢተውለት ልደቱ ቢያንስ በየካቲት ወይም ጥር AUC 750 ወይም (ከ.ክ.ል.በ-BC 4) ይሆናል፡፡ ሌሎች በቤተልሔም የህጻናቱ መቀላት “ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑ ” ማቴ 2÷16 ስለሚል ከሄሮድስ ሞት ሁለት ዓመት ቀድሞ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ እርሱ ግን የቆጠረው ኮከቡ ለሰብአ ሰገል ለመጀመሪያ ጊዜ ከታየበት ጀምሮ ነው (ማቴ 2÷16)፡፡

ሰብአ ሰገልን የመራው ኮከብ

ሌላው የማቴ 2÷1-4፣9 የጊዜ መስመር መነሻ ነው፡፡ይሄውም በሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች የተረጋገጠው ኮከብ ማስረጃ ነው፡፡ ከይሁዳ ታላቅ ንጉስ የመገለጡን[42] ነገር በመጠበቅ የምሥራቅ የሥነ ፈለክ ጠቢባን ቀልብ የሳበው ከሄሮድስ ሞት በፊት የተገለጠው ኮከብ ነው፡፡

በጊዜው ከሥነ ፈለክ ቀመር በላይ የሆነው የኮከቡ መገለጥ ወይ ከተወርዋሪ ኮከብ የተገኘ አሊያም ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንደተገለጠ ይታመን ነበር፡፡ ታታሪውና ታላቁ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ ኬፕለር በ1603 እና በ1604 የጁፒተርና ሳተርን ፕላኔቶች ትይይዝ (የአንድ ቦታ ግጥምጥም-conjunction) ተመለከተ፡፡ በመጋቢት ወር 1604 ማርስ ተጨምሮ ድምቀታቸው ጎላ፡፡ በበልግ ወራት (ጥቅምት 10) በዚያው ዓመት የሳተርንና ማርስ ፕላኔት ባልተለመደ አዲስ ኮከብ ድምቀት ሁናት ተመለከት፡፡ መገለጣቸው ‘ፍጹም የሆነ ታላቅ የእግዚአብሔር ሥራ’ ሁኖበት ነበር፡፡ ይሄም ሁናት የክርስቶስን ልደት ዓመት ወደ መለየት አመራው፡፡ ጥንቃቄ በተሞላው ቀመር ተመሳሳይ የጁፒተርና ሳተርን ትይይዝና ዘግይቶ የማርስ ምናልባትም ፍጹም ያልተለመደ ኮከብ በAUC 747 እና 748 ተደጋግመው በሐረግ (ጭራ -pisces) መልክ መገለጣቸውን አረጋገጠ፡፡

እዚህ ላይ የሚነሣው ተቃውሞ ወንጌላዊ ማቴዎስ ያየው የኮኮቦች ስብስብ ሳይሆን አንድ ኮከብ የማየቱ ጥያቄ ነው፡፡ (ማቴ 2÷9 አነጻጽር) ስለዚህም ዶክተር ዌስለር የኬፕለርና አይድለርን[43] ቀመር ደግፎ በAUC 750 የካቲት የታየውን አንድ ጅራታም ኮከብ አቀረበ፡፡ እነዚህን ቀመሮች ከተቀበልን ሁለት የልደት ዓመት ይኖረናል፡፡ በAUC 748 (ኬፕለርና) እና በAUC 750 (ዌስለር)፤ ልዩነቱ የተፈጠረው ሰብአ ሰገል የተነሱበት ጊዜና የተጓዙበት እርዝመት ላይ እርግጠኛ አለመሆን ነው፡፡

የጢባሪዮስ 15 የሥልጣን ዓመት

ሉቃ 3÷1፣23 መጥምቁ ዮሐንስና ክርስቶስ እንደሌዋውያን ሥርዓት[44] በሠላሳ ዓመታቸው ማስተማር የጀመሩበት ወቅት ላይ የነበረውን የአገዛዝ ሁኔታ ጠቃሚና አስረጂ በሆነ መልኩ ምልከታውን ይሰጠናል፡፡

መጥምቁ ዮሐንስ ማጥመቅ የጀመረው በጢባሪዮስ 15ኛ የስልጣን ዘመኑ[45] ሲሆን ከእርሱ በስድስት ወር የሚያንሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ማስተማር ሲጀምር “ሠላሳ ዓመት ያህል ሆኖት ነበር” (ሉቃ 3÷23)፡፡ ጢባሪዮስ ከአውግስጦስ ጋር በAUC 764 በጥንድ መግዛት (እንደ “collega imperii,”) ሲጀምር ለብቻው ግን ከነሐሴ AUC 767 (AD 14) ጀምሮ ገዝቷል፡፡ ስለዚህም 15ኛ ዓመት የሥልጣን ዘመኑ ወይ በAUC 779 (በጥንድ ከገዛበት ጀምረን -ምናልባትም ቅዱስ ሉቃስ ይሄን ሳይጠቀም አልቀረም) አሊም AUC 782 (የራሱን የሥልጣን ጊዜ ብቻ ስንቆጥር -እንደ ሮማዊያን መንገድ)ይሆናል፡፡

አሁን ሠላሳ ዓመት ከAUC 779 ወይም 782 ወደ ኋላ ስንቆጥር AUC 749 ወይም 752 ስድስት ወር ከክርስቶስ ልደት የሚቀድመው የዮሐንስ ልደት ይሆናል፡፡ ስለዚህም የመጀመሪያው (749) ያለምንም ችግር ተመራጭ ይሆናል፡፡ በዚህም ክርስቶስ በሄሮድስ ዘመን መወለዱን ከሚገልጸው ሀሳብ ጋር የተስማማ ይሆናል (ሉቃ 1÷5፣26)፡፡ ምናልባት ዲዮናስየስ ቀመሩን ሁለተኛውን ቆጥሮ ቢሆን’ኳ 754 አይመጣም የእርሱም ቀመር የሉቃስና የማቴዎስ ሐሳብ የተጋጨ ያደርገዋል፡፡

በቆሬኔዎስ ዘመን የተደረገ የሕዝብ ቆጠራ

በሉቃ 2÷2 ላይ የተገለጸው የቄሬኔዎስ ዘመን የህዝብ ቆጠራ የጊዜ መስመር ሌላኛው መረጃ ይሆናል፡፡ ክርስቶስ ቄሬኔዎስ የሶርያ ገዢ በነበረበት ዘመን ለእርሱ የመጀመሪ የሆነ ጽሕፈት በአውግስጦስ ትዕዛዝ አዋጅ በወጣበት ዘመን እንደተወለደ ይነግረናል፡፡ የጠቀሰበትም ምክንያት አረጋዊ ዮሴፍና ድንግል ማርያም ወደ ቤተልሔም የተጓዙበትን ምክንያት ለማስረዳት ነው፡፡ የእመቤታችን መጓዝ ምክንያታዊ ነው (ዮሴፍ ይጠብቃትና ያግዛት ዘንድ አብሯት ያለ መሆኑ አንድ ነገር ሁኖ) ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች (ባሪያዎችን ጨምሮ) እስከ 65 ዓመታቸው ድረስ በሮማውን ግዛት ይገብሩ ዘንድ ህግ ነበር (14 ዓመት የሞላቸው ወንዶች ጭምር)፡፡[46] ነገር ግን የወንጌላዊው አገላለጽ ከቄሬኔዎስ የሥልጣን ዘመንና በእርሱ ዘመን ከተደረገው ምዝገባ (ቆጠራ) ጋር የሚጋጭ ይሆናል፡፡ ምክንቱም የቆሬኔዎስ ሥልጣን የሚጀምረው ክርስቶስ ከተወለደ 10 ዓመት (AD 10) በኋላ ነውና፡፡[47]

ይህን ልዩነት ለማጥበብ የተደረገ የመካነ ቅርስ ጥናት(archeological) እና የቋንቋዎች ታሪክ (ሥነ ልሳን-philological) ጥናት ከነገረ መለኮት ጥናት(theology) በተናጥል በርግማን፣ ሞምሰንና በተለይ ዛምፕት አረጋግጠዋል፡፡ ቄሬኔዎስ ሁለት ጊዜ የሶሪያ ገዢ እንደነበር፤ ጊዜውም የመጀመሪያው AUC 750 እስከ 753 (BC 6-4) እና በድጋሚ ከAUC 760 እስከ 765 (BC 6-11) ይህ የሁለት ጊዜ ሥልጣን የተገኘው የታሲተስን ጽሑፍ መሠረት አድርጎ ነው.[48] ስለዚህም ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ክርስቶስ በተወለደበት በቄሬኔዎስ ዘመን የተደረገውን ቆጠራ የመጀመሪያ ያለበት ትክክለኛ አጠራር ሳይሆን አይቀርም ምክንያቱም ቀጥሎ ከነበሩት ቆጠራዎች እርሱም ሁለተኛ በጻፈው ላይ ከጠቀሰውን ለመለየት ስለሚያስችል (ሐዋ 5÷37) ፡፡ ምናልባትም የመጀመሪያ ቆጠራ ላይ ያለው ልምድ በድጋሚ ወደ ሶሪያ እንዲሄድ አስመርጦት ሳይሆን አይቀርም፡፡

ልዩነቱ ግን አሁንም የተፈታ አይመስልም፡፡ ከሳንቲም ላይ እንደተገኘ መረጃ መሰረት ቄኔቲለስ ቫሬስ ከAUC 748 እስከ 750 (BC 6-4) ገዢ እንደነበረና ከሄሮድስ ሞት በኋላ ቢሮውን እንደለቀቀ ያስረዳል፡፡[49] በዚህም ቄሬኔዎስ ከመኸር AUC 750 (BC 4) በፊት ሥልጣን ላይ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ይህ ጊዜ ደግሞ መጋቢት 750 ከተፈጸመው ከሄሮድስ ሞት ብዙ ወራት በኋላ (ማለትም ክርስቶስ ከተወለደ በኋላ) ያደርገዋል፡፡

ይህን ግጭት ለማስታረቅ የሞከረው ዘምፕት እንደሚያስበው የሶሪያ ገዢ በነበረው ሴንቲየስ ሳቹርኒነስ (AUC 746 ወይም BC 9 እስከ AUC 749 ወይም BC 6) በይሁዳ ቆጠራ እንደጀመረ ከዛም የእርሱ ተተኪ የነበረው ቄኔቲለስ ቫሬስ (BC 6-4) እንደቀጠለውና ቄሬኔዎስ (BC 4) እንዳጠናቀቀው ነው፡፡ ሌላው ምናልባት ዝቅተኛ ግምት የሚሰጠው እይታ ቄሬኔዎስ በቆጠራ ወቅት የምስራቅ ልዩ ኮሚሽነር ሁኖ ሄዶ ሊሆን ይችላል የሚለው ነው፡፡ ፊሊፕ ስካፍ እንደሚለው ችግሩ ባይፈታም ለመጪው ጥናት ያለው ተስፋ ቄሬኔዎስ በክርስቶስ ዘመን ከምስራቅ የሮማ ግዛት ጋር ግንኙነት እንደነበረው የተመሠረተው መላምት ይሆናል፡፡[50]

ሄሮድስ ያስገነባው 46 ዐመት መቅደስ

ዮሐ 2 ÷20 ጌታችን በመጀመሪያዎቹ የትምህርት ጊዜያት “ይህ ቤተ መቅደስ ከ46 ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር አንተስ በሦስት ቀን ታስነሳዋለህ?” ሲሉ የጠየቁትን አይሁዳውን ያስታውሰናል፡፡ ከጆሴፈስ እንደተማርነው ሄሮድስ መቅደሱን በኢየሩሳሌም ዳግመኛ ለማሰራት የጀመረው በ18ኛ የሥልጣን እድሜው ላይ ማለትም AUC 732 እንደሆነ ይነግረናል፡፡[51]

የመቅደሱን እድሜ 46 ዓመት ብንጨምርበት የክርስቶስ የመጀመሪያ የትምህርት ወቅት AUC 781 (ከክ.ል.በ-AD 27) ይሆናል ማለት ነው፡፡ ቀጥሎ ሠላሳና ግማሽ ወይም ሠላሳ አንድ ዓመት ከ781 ቢቀነስ ወደ AUC 750 (ቅ.ል.ክ-BC 4) ወደ ጌታ ልደት ዓመት ይወስደናል፡፡

ክርስቶስን የሰቀሉበት ዘመን

ተርቱሊየን የክርስቶስን ልደትና የተቀበለውን መከራ ጊዜ ለማስላት ከነብዩ ዳንኤል 70 ሣምንታት ጋር በዝርዝር በማጥናት ክርስቶስ የተሰቀለው በሁለቱ የሮማ ቆንስላዎች ጄሚኒ (ሬቤሉየስ ጄሚኒ እና ፉፊየስ ጀሚኒ) ዘመን፤ ጊዜውም AUC 782-83 (AD 28-29) እንደሆነ ለይቷል፡፡[52] ክርስቶስ ለነበረው የማስተማር ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ዓመት በመስጠትና መከራ በተቀበለበት ወቅት 33 ዓመት እንደሆነው በመግለጽ ተርቱሊየን የልደቱን ዓመት ወደ AUC 750 ወይም 749 ያደርገዋል፡፡[53]

ስለዚህም ስናጠቃልል በሦስቱ ወንጌላውያንና በተርቱሊየን መግለጫ ከተጠቀሱት ብዙ ድርጊቶች በመነሳት ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን፡፡ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እውነተኛነት ከአፈታሪክ መላምቶች በመለየት ማረጋገጥ ያስችለናል፡፡ ግና ፍጹም ትክክል የሆነ መረጃ ባለመኖሩና በቀመሮች ላይ ባለን እይታዎች እርግጠኝነት ማነስ ምክንያት እስከአሁንም የልዩነት ክተት አለ፡፡ ይኸውም ቢዘገይ በAUC 747 (ቅ.ል.ክ-BC 7) እንዲሁም ቢፈጥን AUC 750 (ቅ.ል.ክ-BC 4) የጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ዓመት ሊሆኑ የሚችሉ ጽንፎች ናቸው፡፡[54]

የክርሰቶስ የልደት ቀን

መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን ብቸኛ ሀቅ መድኃኒታችን በተወለደበት ወቅት እረኞች መንጋዎችን እየጠበቁ በሜዳ እንደነበሩ ነው (ሉቃ 2÷8) ይህ እውነታ ወቅቱን ከክረምት በቀር በማንኛውም ወቅት ሊሆን እንደሚችል ይነግረናል፡፡ ስለዚህም የተለመደው የልደት ቀን የማይደገፍ ይሆናል ማለት ነው፡፡

እንደ ታልሙድ መረጃ ፍልስጤማውያን አርብቶ አደሮች የመንጋ መጠበቂያ ጊዜ[55] የሚጀምረው በመጋቢት ሲሆን የሚያበቃው በኅዳር ላይ ይሆናል፡፡ የካቲት እስኪያልቅም መንጎቹ ከሜዳ ላይ መጥተው በመጠለያ ውስጥ ይጠበቃሉ፡፡ የብራማ ቀናት በታህሳስና ጥር ላይ በተደጋጋሚ የመከሰቱ እድል ከምዕራብ አገራት ጋር ሲነጻጸር የምስራቃውያን የበረታ ነው፡፡ ወደ ቅስት ሃገር የመጓዝ ብዙ ልምድ ያለው ቶብለር በክሪስማስ ወቅት ያለው የቤተልሔም የአየር ጸባይ መንጎችን ለመመገብ የሚመች አስደሳች ጊዜ እንደሆነ ተናግሯል፡፡[56] በሌላ መልኩ ጠንካራና ቀዝቃዛ ንፋስ ብዙውን ጊዜ በሚያዝያ ወቅት እንደሚገለጥ በዮሐ 18÷18 ላ የተነሣው እሳት ያስረዳናል፡፡ ይህን የጌታ ልደት ቀን በተመለከት ስናጠቃልል የሚከተለውን ሐሳብ እናገኛለን፡፡

፩. የትውፊታዊው ታህሳስ 25 ቀን በጀሮሜ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ባሮንየስ፣ሌሚ፣ አሸር፣ ቤንገል (አድለር)፣ ሴይፋርትና ጃርቪስ የተደገፈ ሐሳብ ነው፡፡ መጋቢት 25 ድንግል ማርያም ብስራት የሰማችበት ቀን ተደርጎ ሲቀመጥ መስከረም 24 ደግሞ ኤልሳቤጥ ዮሐንስን የጸነሰችበት ቀን ተደርጓል፡፡[57]

የሮማውን ብዙ በዐሎች (ሳቹርናሊያ፣ ሲጊላሪያ፣ የማይሸነፈው ፀሐይ፣ ብሩማሊያ፣ ጃቬናሊያ) በታህሳስ ወር መከበራቸውን መሰረት አድርጎ በሮማ ለመጀመሪያ ጊዜ በ4ኛመ/ክ/ዘ (ከAD 360 በፊት) የክሪስማስ በዐል ሲተዋወቅ ምንም ዓይነት ታሪካዊ ተጽእኖ እንዳልነበረ ፊሊፕ ስካፍ አስተያየት ሰጥቶበታል፡፡[58]

፪. እንደ ኤጲፋንዮስና ካዚያነስ አገላለጽ ጥር 6[59] የቆየ ትውፊታዊ ቁርኝት ነበረው፤ በአውሳቢዮስም ተደግፎ ቆይቷል፡፡ ከ3ኛ መ/ክ/ዘ ጀምሮ የጥምቀት በዓል ሁኖ እየተከበረ ይገኛል፡፡[60] በዐሉም የክርስቶስን መወለድ፣ መጠመቅ፣እንዲሁም አይሁዳዊ ላልሆኑትም የመገለጡን ዜና (በሰብአ ሰገል እየተወከለ) እየታሰበበት ይከበራል፡፡[61]

፫. ሌሎች ጸሐፊዎች ሌላ ቀንን በየካቲት (ሁግ፣ዌስለርና ኤሊኮት)፣ ወይም በመጋቢት (ፓውለስና ዊነር)፣ ወይም በሚያዝያ (ግሬስዌል)፣ ወይም በነሐሴ (ሌዊን) ወይም በመስከረም (ላይትፉት)[62]፣ በጥቅምት (ኒውከም) ላይ ሌላ ቀን መርጠዋል፡፡ ላንድለር ልደቱን በነሐሴ አጋማሽ እና በኅዳር አጋማሽ መሐል ሲያደርገው ብራውን በታህሳስ 8፣ ሌቸንስቴይ በበጋ ፣ ሮቢንስነ ደግሞ በጠቅላላው አይታወቅም ብሎ ትቶታል፡፡[63]

Mass of Christ (Christmas) (ገና ?)

ክሪስማስ ከየት ተገኘ? ምንስ ማለት ነው?

በድሮ የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት Christmas የሚለው ቃል AD 1038 በኋላ መታየት ጀምሯል፡፡[64] መጀመሪያ ላይ Cristes Maesse ተብሎ የተቀመጠ ሲሆን ከAD 1131 በኋላ Cristes-messe ተብሎ የታየ ሲሆን ‘የተቀቡት[65] ስብስብ’ የሚል ትርጉም ነበረው፡፡[66][67] ይህ ትርጉም (ቃል) በክርስቲያኖች ቤተክርስቲያን ከጣኦት አምላኪዎች በዓል ለመለየት የተፈጠረ ቃል ነበር፡፡ በአራተኛው መ/ክ ዘመን የነበረ የነገረ መለኮት ጸሐፊ ” ይህን ቀን ቅዱስ አድርገን የምንጠብቀው እንደጣኦት አምላኪያኑ የፀሐይ ልደት ስለሆነ አይደለም፤ ፀሐይን የፈጠረው የእርሱ ልደት ስለሆነ እንጂ” ማለቱ ተዘግቧል፡፡[68] በኔዘርላንድ ደች ቋንቋ Kerst-misse ፣ በላቲን Dies Natalis ፣ ሲባል በፈረንሳይ Noël ሲሆን በእንግሊዘኛም ተመሳሳይ ትርጉም ተሰጥቶታል ፤ እንዲሁም ጣሊያኖች Il natale ; በጀርመኖች ከጥንት በዐላቸው ቪግል ተወርሶ Weihnachtsfestl ይባላል. Yule የጣኦት አምላኪያን የበዓል ስም ቢሆን በጥንት የክሪስማስ መጠሪያ ከነበሩ ስሞች አንደኛው ነው፡፡[69] የኢትዮጵያ ገና ከእነዚህ ትርጉሞች የተለየ ነው፡፡ ስለኢትዮጵ በምናነሳበት ክፍል እናየዋለን፡፡

የመጀመሪያው የተዘገበ የኔቲቪቲ (ክሪስማስ) በአል የትና መቼ ነበር?

ክሪስማስ በጥንታዊዋ ቤተክርስቲያን ዘንድ ያልተለመደ (የማይታወቅ) በዓል እንደነበረ መዛግብቶች ያስረዳሉ፡፡ የብሪታኒካ ባህረ ጥበባት በክሪስማስ ዘገባው ላይ “ክሪስማስ (ማለትም የተቀቡት[70] ስብስብ)…. ጥንታዊ የቤተክርስቲያን በዓላት ከነበሩት የሚካተት አልነበረም..”[71] በክርስቶስ የተመሠረተ ወይም ሐዋሪያት የጀመሩት አሊያም መጽሐፍ ቅዱስ ያዘዘው አልነበረም ይልቁን ከጣኦት አምላኪያኑ ተወረሰና ተጀመረ እንጂ፡፡[72]

የአሜሪካ ባህረ ጥበባት እንደሚከተለው አትቷል “ክሪስማስ… እንደብዙዎቹ ጸሐፊያን፤ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘ በክርስቲያኖችን ቤተክርስቲያን አልተከበረም ምክንያቱም ገድል የሰሩ ሰዎችን እረፍታቸውን እንጂ ልደታቸውን ማክበር ያልተለመደ ነበርና”[73]

የካቶሊክ ቤ/ክ ባህረ ጥበባት ከቤተክርስቲያን እንዳልመነጨ ያስረዳናል “ክሪስማስ የቤተክርስቲያን ጥንታዊያን ክብረ በዓላት ውስጥ የተቆጠረ አልነበርም” ስለዚህ ፔተር ሳሌሚ በጽሁፉ ላይ[74] ዱራንት እንዳለው “ክርስትና የጣኦት አምልኮን አላጠፋውም ተቀበለው እንጂ” ብሎ እንደገለጸው የክሪስማስ በዓል ዘግቶ ከአምላኪያነ ጣኦት ልማድ የተዛመደ ነበር፡፡

ጥንታዊ መረጃ ይዞ የተገኘው የጥንት የሮማ ጳጳስ በAD 354 ጽፎታል በተባለው መረጃ ላይ ቃሉ በAD 336 እንደሚታወቅ ይገልጻል “25 Dec.: natus Christus in Betleem Judeae.”- ታህሳስ 25 ክርስቶስ በቤተልሔም ይሁዳ ተወለደ፡፡ ይሄም የመጀመሪያ የተመዘገበ የልደት በዓል ሁኗል፡፡[75] [76]

የክሪስማስ (ገና) በዓል ማክበሪያ ልምዶች ከየት የተገኙ ይሆን?

የክሪስማስ አከባበር ልማዶች ከተገኘበት ምንጭ እንደሚቀዳ መገመት የሚከብድ አይሆንም፡፡ የጣኦት አምላኪያኑ የበዓል አከባበር ልምዳቸው (በወቅቱ ክርስቲያኖችም ቅድመ ክርስትናና ጊዜ ክርስትና የሚፈጽሙት ነበርና) አብሮ መከተሉ የማቀር ነው፡፡ የብሪታኒያ ባህረ ጥበባት ይሄን ይላል “በሮማው ዓለም ሳቹርናሊያ[77] (ታህሳስ 17) የደስታ የፈንጠዚያና (merrymaking) ስጦታዎች የመለዋወጫ ጊዜያቸው ነበር፡፡ ታህሳስ 25 የኢራኒያን ሚስጥራዊ አምላክ የፍትሐዊው ፀሐይ የሚትህራ የልደት ቀን ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ በሮማውያን የአዲስ ዓመት (ጥር 1) ቤቶች በአረንጓዴ ቅጠሎችና መብራቶች ይዋባሉ፣ ስጦታዎች ለሕጻናትና ለድሆች ይሰጣሉ፡፡ ብሪቴይንና መሐከላዊ አውሮፓ እንዚህን አይነት ልማዶች የቴዩቶኒክ[78] ጎሳዎች ወደ ጉዋል[79] ገፍተው ሲገቡ ከጀርመንና የሴልቲክ ‘ዩሉ’ ክብረ በዓል ተቀብለውታል፡፡ ምግቦች፣ መልካም ወዳጅነት፣ የዩሉ ባህላዊ ኬኮች፣ አረንጓዴ ቅጠሎችና ጥድ መሳይ ዛፍ፣ ስጦታዎችና መታሰቢያዎች መዘከር የዚህ ክብረ በዓል የተለየያዩ መገለጫዎች ናቸው፡፡ እሳትና መብራቶች፤ የጋለ ልባዊ ስሜትና የዘላለም ህይወት ምልክቶች [ተምሳሌት] በጣኦት አምላኪያንና በክርስቲያኖች ዘንድ ምንጊዜም ከክረምት ክብረ በዓል ጋር እየተያያዙ የሚኖሩ ናቸው፡፡”[80]

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደቀላሉ እየተላመድንና የእኛ እስኪመስሉ የምንዋብባቸው (?) ሳንታ ክላውስ (የገና አባት??) ማነው?የገና ስጦታ ልውውጡ መጽሐፋዊ ይሆን? የክሪስማስ ዛፍ ምንጩ ከወዴት ነው? ከልክ ያለፈ ደስታና ፈንጠዝያውስ (merry-making)? የዩሉ ሎግና ኬክ ከተዛማቾቹ አረንጋዴ ቅጠላቅጠሎች ጋር እንዲሁም የክሪስማስ ካሮልና ዝማሬ ከየት የተገኙ ይሆን?

ለመሆኑ ሁለት የገና (ክሪስመስ) በዓል ለምነው የምናከብረው? በቀጣዩ ክፍል እግዚአብሔር ቢፈቅድ የምናያቸውይሆናል፡፡ ይቆየን!

 

[1] (Catholic church, Chronology of the Life of Jesus Christ)

[2] (Jean-Yves Lacoste, 2005)

[3] ማቴ 2÷1

[4] Josephus (Ant., XVII, viii, 1)

[5] መጽሐፍ ቅዱስ በእስራኤላውያን የአመት አቆጣጠር እስራኤላውያን ከግብጽ የወጡበትን የኒሳን ወር የመጀመሪያ ሁኖ እንደሚቆጥሩ ( ዘጸ 12÷2) ይገልጻል፡፡ ሆኖም ህዝቡ በግብርና ስለሚኖር አጨዳ ሲጨርሱ የዐመት መለወጫ በዐልን ያከብሩ ነበር (ዘጸ 23÷16፣ 34÷22)፡፡ ብዙውን ጊዜ በወሩ ሳይሆን በግብርና ሥራ ጊዜው ይገለጣል፡፡ (Ethiopian Bible Society, 1992, p. 18)

[6] ቅዱስ ማቴዎስ እንደጻፈው ሄሮድስ ከሞተ በኋላ በግብጽ ስደት ላይ ለነበረው ለቅዱስ ዮሴፍ የጌታ መልአክ በህልም ታይቶት ሄሮድስ በመሞቱ እንዲመለስ እንደነገረውና ወደ ኢየሩሳሌም እንደተመለሱ ዘግቧል (ማቴ 2÷19) ፡፡ በመሆኑም ጆሴፈስ ስለጸሐይ ግርዶሽ ሲያነሳ በጌታ ስቅለት ወቅት ስለተከሰተው ምድር መጨለም አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡

[7] April (Josephus, “Ant”., iv, 4; viii, 4)

[8] (Catholic church, Chronology of the Life of Jesus Christ)

[9] McGowan, Andrew. “How December 25 Became Christmas, Biblical Archaeology Review, Retrieved 2009-12-13”. Bib-arch.org. Retrieved 2014-02-24

[10] (Martindale, 1908)

[11] Hillerbrand, Hans J. (December 14, 2012). “Christmas”. Encyclopædia Britannica. Retrieved 2015-01-25.

[12] “Elesha Coffman, “Why December 25?”. Christianitytoday.com. 2008-08-08. Retrieved 2015-01-25.

[13] ሉቃ 1÷26

[14] ሉቃ 1÷10-13

[15] (Eusebius, 1890, p. 160)

[16] ፍላቪየስ ጆሴፈስ በ A.D. 37/38-95/100 የኖረ ሲሆን በመሐለኛው ዘመን ከጥንታውያን የላቲን ቅጅዎ የታወቀ የታሪክ ጸሐፊ ነው፡፡

[17] (P. Schaff, ed. Church History)

[18] (Eusebius, 1890, P. Schaff, ed., p. 160 ከግርጌ ጽሑፍ)

[19] “Historical Dictionary of Catholicism”.

[20] “St. Basil (330–379)”. Skiathosbooks.com. Retrieved 2014-02-03.

[21] (Martindale, 1908)

[22] (Matera)

[23] “Watson E. Mills, Roger Aubrey Bullard (editors), Mercer Dictionary of the Bible (Mercer University Press 1990 ISBN 978-0-86554-373-7), p. 142″. Google.com. Retrieved 2013-12-25.

[24] Gibson, David J. (October – December 1965).The Date of Christ’s Birth. Bible League Quarterly.

[25]Christmas, Encyclopædia Britannica Chicago: Encyclopædia Britannica, 2006.

[26] Hillerbrand, Hans J. (December 14, 2012). “Christmas”. Encyclopædia Britannica. Retrieved 2015-01-25.

[27] (Martindale, 1908)

[28] “Historical Dictionary of Catholicism”.

[29] Hillerbrand, Hans J. (December 14, 2012). “Christmas”. Encyclopædia Britannica. Retrieved 2015-01-25.

[30] (Catholic church, Chronology of the Life of Jesus Christ)

[31] Kellner (op. cit., pp. 106, 107)

[32] Friedlieb (Leben J. Christi des Erlösers, Münster, 1887, p. 312).

[33] (Catholic church, Chronology of the Life of Jesus Christ)

[34] ዝኒ ከማሁ, ዘካ 14÷16፣ ዳን 9÷27

[35] Lightfoot (Horæ Hebr, et Talm., II, 32)

[36] bruma- በሰሜን ፀሃይ ከምትነግስበትና ቀኑ በሚረዝምበት ወር

[37] (Newton, 1733) A sun connection is possible because Christians consider Jesus to be the “Sun of righteousness” prophesied in Malachi 4:2.

[38] (Hijmans, 2009, p. 595)

[39]በካርልማጅን ዘመን አባቶች በመወለድና (Nativity- ማቴ 1÷18) ሥጋ በመልበስ (Incarnation) መሐል ልዩነት አበጅተውለታል፡፡ የክርስቶስን ሥጋ መልበስ ከድንግል ማርያም መጸነስ ወይም (conception) ከቅ/ገብርኤል ብስራት ጋር ሲለዩት (Annunciation) ከካርልማጅን በፊት ግን ሁለቱ ቃላት በተለዋዋጭነት በተለዋዋጭነት (በተመሳሳይ ትርጉም) ይጠቀሙበት ነበር፡፡ Ideler, Chronol., ii. 383, and Gieseler, i. 70 (4th Germ. ed.).

[40] Jos., Antiqu., xvii. 8,1: “ሄሮድስ….. አንቲጎነስ እንዲቀላ እስኪያደርገው ድረስ [AUC 717 ወይም BC 37] 34 ዐመት ገዝቶ ሞተ፡፡ ነገር ግን በሮማውያን ንጉስ እንዲሆን ከታወጀ ሲቆጠር [AUC 714 ወይም BC 40]   37 ዐመት ገዝቷል”

[41] እንደ ጆሴፈስ “…. በዛ ምሽት የፀሐይ ግዶሽ ነበር ” ብሏል፡፡ ለAntiqu. xvii. 6, 4:

[42] ዘኁ 24÷17 “…ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል..” የሚለውና ሌሎች የኢሳይያስና የዳንኤል ትንቢት ቃሎች በአይሁዶች መስፋፋት ምክንያት በምስራቅ በሰፊው የታወቁ ነበር፡፡

[43] ኤድለር የኬፕለርን ሀሳብ ለማረጋገጥ ባደረገው ጥረት በ747 ተመሳሳይ የጁፒተርና ሳተርን ትይይዝ በሰኔ፣ ነሐሴና ታህሳስ ላይ መታየታቸውን አረጋገጠ፡፡ በቀጣዩ ዐመትም በየካቲት፣ መጋቢት ላይ ማርስ ተጨምሮበት ወይም ምናልባትም ሌላ ፍጹም የተለየ ኮከብ፡፡ ሰብአ ሰገልም መጀመሪያ አዲሱን ኮከብ ቀጥለውም የኮኮቦችን ስብስብ ተመልክተው ይሆናል ብሏል፡፡ በሌላ ጽሑፉም “ደካማ የሆነ አይን ሁለት ፕላኔቶችን ምናልባት እንደ አንድ ኮከብ ታይተውት ይሆናል” ሲል አክሏል፡፡ (Ideler Vol II. 405, Lehrbuch der chronologie, 1831 Vol. 1 pp, 424-431)

[44]ዘኁ. 4÷3፣35፣39፣43፣47 አነጻጽር

[45] ሉቃ 3÷1፣2 “ጢባርዮስ ቄሣርም በነገሠ በአስራ አምስተኛይቱ ዓመት÷ ጴንጤናዊው ጲላጦስም በይሁዳ ሲገዛ÷ሄሮድስም በገሊላ የአራተኛው ክፍል ገዥ ……ሳሉ”

[46] Ulpian, በ Zumpt, Geburtsjahr Christi, p. 203 sq. ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሰ

[47] ሐዋ 5÷37

[48] የታሲተስ Annal., iii. 48፤ ዘምፕት in a Latin dissertation: De Syria Romanorum provincia ab Caesare Augusto

ad T. Vespasianum ላይ እንደተረጎመው እንዲሁም ኢፒገራፍ Berol. 1854, vol. ii. 88-125 ላይ አስተያየት እንደሰጠበትና ሞምሰን በRes gesstae divi Augusti 121-124እንዳረጋገጠው. ዘምፕትሙሉ ሓሳቡን በደንብ ያሳደገው በDas Geburtsjahr Christi, 1869, pp. 1-90. ላይ ሲሆን ታሲተስን አሸር ሳንክሌሜንት አድለር (II. 397), እና ብራውን (p. 46) ታሲተስን እንደ ዘምፕት ተረድተውታል፡፡ (Schaff, 1882, p. 77)

[49] ጆሴፈስ, Antiqu., xvii. 11, 1; Tacitus, Hist., v. 9: “post mortem Herodis … Simo quidam regium nomen invaserat; is a

Quintilio Vare obtinento Syriam punitus,” etc.

[50] (Schaff, 1882, p. 79)

[51] ጆሴፈስ “ሄሮድስ በ 18ኛ ሥልጣን በያዘ ዓመቱ ….. ታላቅ ሥራ እርሱም የእግዚአብሔርን መቅደስ መገንባት ጀመረ፡፡ …..ከሥራዎቹ ሁሉ ዋናው አስደናቂ ሥራው … …… እርሱን የሚያስታውስ ዘላለማዊ ማስታወሻ ሁኖለታልና.. “Antiqu. xv. 11, 1

[52] ፊ. ስካፍ, 1882, History of the Christian Church, Volume I: Apostolic Christianity.A.D. 1-100. ገጽ 80፣ 138ኛ የግርጌ ጽሑፍ

[53] (Schaff, 1882, p. 80)

[54] The French Benedictines, Sanclemente, Münter, Wurm, Ebrard, Jarvis, Alford, Jos. A. Alexander, Zumpt, Keim, decide for a.u. 747; Kepler (reckoning from the conjunction of Jupiter, Saturn and Mars in that year), Lardner, Ideler, Ewald, for 748; Petavius, Ussher, Tillemont, Browne, Angus, Robinson, Andrews, McClellan, for 749; Bengel, Wieseler, Lange, Lichtenstein, Anger, Greswell, Ellicott, Plumptre, Merivale, for 750. (Schaff, 1882, p. 80)

[55] ፍልስጤማውያን ያላቸው የዓመቱ ወቅት እርጥብና ደረቅ የሚባል ሁለት ወቅት ብቻ ነበር፡፡ ክረምታነ በጋ ማለት ነው፡፡

[56] (Schaff, 1882, p. 80)

[57] የትውፊታዊው ቀን ተከራካሪ ዮሐንስ ብራውን ማክሌን ክርስቶስ ታህሳስ 25 AUC 749 (BC 5) እንደተወለደ ለማረጋገጥ ጥሯል፡፡ New Test., etc. vol. I. 390 sqq.

[58] (Schaff, 1882, p. 81)

[59] ዝኒ ከማሁ

[60] “Elesha Coffman, “Why December 25?”. Christianitytoday.com. 2008-08-08. Retrieved 2013-12-25.

[61] Hil l erbrand, Hans J. (December 14, 2012). “Chri stmas”. Encycl opædi a Bri tannica. Retri eved 2015-01-25.

[62] ላይትፉት በጊዜ መስመር መሠረት በዳስ በዐል (Tabernacles) እንደተወለደ እና በፋሲካ/የቂጣ በዐል እንደሞተ እንዲሁም በበዐለ አምሳ (Pentecost) መንፈስ ቅዱስ እንደላከላቸው ገምቷል፡፡

[63] (Schaff, 1882, p. 81)

[64] (History of Christmas)

[65] በግሪክ ክርስቶስ( Khristos) ማለት የተቀባ ማለት ነው፡፡

[66] ዝኒ ከማሁ

[67] (Catholic church, Christmas)

[68] History of Christmas adopted from http://christianity.about.com/od/christmas/f/christmashistor.htm

[69] ዝኒ ከማሁ

[70] የተቀባ ማለት የእብራይስጡ መሲህ (mQ_Wa0) ሲሆን የግሪክ ትርጉሙ (አቻው) ክርስቶስ (Khristos) ማለት ነው፡፡ መሲህም ክርስቶስም ትርጉማቸውም የተቀባ ማለት ነው ፡፡ (Ethiopian Bible Society, 1992, pp. 32, 164)

[71] Encyclopedia Britannica, 1946 edition

[72] (Salemi, p. is christmas christian?)

[73] The Encyclopedia Americana, 1944 edition, (የእኔ ተጨማሪ ማብራሪያ አለበት)

[74] (Salemi)፣ ዱራንት vol. 3, p.595

[75] First recorded celebration adopted from http://www.christianity.com/church/church-history/timeline/301-600/the-1st-recorded-celebration-of-christmas-11629658.html

[76] በግብጽ ኮፕቲክ ቤ/ክ ድህረ ገጽ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ የእስክንድሪያው ቅ/ቀሌሜንጦስ ባስተላለፈው ጽሑፍ ላይ የእርሱ ዘመን ግብጻውያን የጌታን ልደት Nativity ተብሎ በግንቦት 20 የሚገልጽ መረጃ አላቸው ይህ ከመጀመሪያው የቀደመ ቢሆንም ታህሳስ 25 ስለማክበር (ክሪስማስ በዚህ ቀን ስለሚከበር) ስለማይገጽ ይሆናል የመጀመሪያ ያልተባለው፡፡ (Editorial, p. Coptic Church Website)

[77] ሳቹርናሊያ የሳተርን ፕላኔት ክብር የሚከበር መነሻው ለአንድ ቀን የነበረ በኋላ ግን ለሰባት ቀን የቀጠለ ምንም አይነት ክልከላ የሌለበትና ለሁሉም የኑሮ ክፍል (ባሪያዎችን ጨምሮ) የተፈቀደ ልቅ የሆነ ከልክ በላይ በመጠጣት የመጨፈር በዐል ነው፡፡ concise oxford dictionary (tenth edition) on CD-ROM 2001 V. 1.1 , the free dictionary by farex, 2012 (the android app, http://thefreedictionary.com)

[78] በ4ኛ መ/ክ/ዘ በጁትላንድ የኖሩ የጀርመን ህዝቦች ሲሆኑ የጀርመኒክ ክፍል የሆነው የኢንዶ-ዩሮፒያን ቋንቋ ተናጋሪ ቤተሰቦች ስያሜም ነው፡፡

[79] የጥንት የጉአል አውሮፓ ክልል ነዋሪዎች ወይም ዜጎች ነበሩ፡፡

[80] Encyclopedia Britannica, 15th ed., vol. II, p. 903.

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑