Christmas Vs ገና Vs Nativity – ክፍል ሦስት

Christmas Vs ገና Vs Nativityክፍል ሦስት

To read in PDF

ገና ወይስ ልደት?

ለመሆኑ ሁለት የገና (ክሪስመስ) በዐል ለምነው የምናከብረው?         

የክሪስማስ (ገና) በዐል ማክበሪያ ልምዶች…ሳንታ ክላውስ (የገና አባት??) የክሪስማስ ዛፍ ምንጩ ከወዴት ነው?

የልደት በዐልስ ስለምን ማክበር ይገባናል?

ጌታችንና መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የመወለዱን ብስራት ይዘን ሁለት ተከታታይ ክፍሎች ማቅረባችን የሚታወስ ነው:: የመጀመሪያው ክፍል የጌታን ልደት ጥንተትና የታህሳስ 25 ምክንያተ እለት በጥቅል ካነሣን በኋላ በሁለተኛ ክፍል በሠፊው እስከዛሬ የተጠኑ ጥናቶችና ትርጓሜዎች ተዳሰው በጌታ ልደት ጥንተተ ዓመትና ዕለቱ ላይ ማጠቃለያ ሰጥተንባቸዋል፡፡ የክሪስማስ ስያሜ አመጣጥና ልምዱን አንስተን በበአሉ አከባበር ወቅት የሚታዩት ልማዶች ከየት መጣነት ለማንሳት በቀጠሮ ማቆየታችን ይታወሳል፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶልን ቀጣዩን ክፍል እንደዚህ አሰናድተንዋል፡፡

የክሪስማስ (ገና) በዓል ማክበሪያ ልምዶች ከየት የተገኙ ይሆን?

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደቀላሉ እየተላመድንና የእኛ እስኪመስሉ የ’ምንዋብባቸው’ (?) የሚመስሉን የገና/ልደት በዓል ማክበሪያ ልምዶች በጣም እየደጋገሙና መልክና ሥርዓት እየጠፋቸው ይገኛሉ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊ ቀለማት ደብዝዘዋል አንድም ተፋፍቀዋል፡፡ የኢትዮጵያዊውን ቀለም እድሳት/ድማቅ እናዘግየውና የጀመርነውን የበዓሉ ‘መግለጫዎች’ (?) ምንጭ ከቦታቸው እንቆፍር….

የክሪስማስ በዓል የሚገለጽባቸው በርካታ ቁሳዊና ድርጊታዊ ሥርኣቶች ያሉት ቢሆንም በእኛ ዘንድ ሲዘወተሩ ያየናቸው የገና አባት (?)፣ የክሪስማስ ዛፍ ና የስጦታ ልውውጦች የምንዳስሳቸው አርዕስት ይሆናሉ፡፡

ሳንታ ክላውስ (የገና አባት?)

በእርግጠኝነት ማንም ሰው ባለረጅም ነጭ ጺም ያለው ወፍራም ሰው (ሳንታ ክላውስ የተባለው) ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደተገኘ ማስረጃ ማቅረብ አይቻለውም፡፡ ታዲያ ይህ ሰው ከየት መጣ?

ስለሳንታ ክላውስ አመጣጥ የተለያዩ መላምቶች የሚሰጡ ሲሆን አንደኛው ከቅዱስ ኒኮላስ ጋር የሚገናኘው ነው፡፡ ምንም እንኳ ድርጊቱ ከቅ/ኒኮላስ በፊት የነበረ መሆኑ የተረጋገጠ ቢሆንም ምናልባት እሱን ሰበብ ተደርጎ ከድሮው ልማድ ተዘፍቀው ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ኒኮላስ በቱርኳ ፓራራ በ270 ከክ.ል.በ ተወለደ፡፡ በኋላም የማይራ ጳጳስ የሆነ ሲሆን በ19ኛው መ/ክ/ዘ ቅዱስ የተባለ ብቸኛው ነበር[1]፡፡ በ345 ከክ.ል.በ ያረፈ ሲሆን በ1087 አጽሙን ከቱርክ ወደ ባሪ የጣሊያን የተቀደሠ ቦታ አፍልሰውታል፡፡[2],[3] በ13ኛው መ/ክ/ዘ የቅ/ኒኮላስ ስም በኔዘርላንድ ውስጥ የታወቀ ሆነ በተለይ ስጦታ የመስጠት ተግባሩ በአውሮፓ ናኘ፡፡ በ16-17ኛው መ/ክ/ዘ በተሃድሶ ዘመን ፕሮቴስታንቶች የስጦታ አምጪውን ወደ ክርስቶስ ልጅነት ወይም Christ kindl ቀየሩት፡፡[4] የጣኦት አምላኪያን የሆኑትን የሰሜን አውሮፓውያን የኒኮላስን አምልኮ የካቶሊክ ቤ/ክም ወረሰችው፡፡ ስጦታዎችንም በታህሳስ 6 ሳይሆን በታህሳስ 25 ላይ እንደሚያከፋፍል አስተማረች፡፡[5],[6]

የደቾች አሜሪካንን ቅኝ የመግዛታቸውና ኒው አምስተርዳምን መመስረታቸው ልጆቻቸው በትውፊት የቅ/ኒኮላስ ጉብኝት የሚባለውን የካቶሊክ ልማድ ቀጠሉት፡፡ እንግሊዝም ቅኝ ግዛቱን ተቀብላ ኒውዮርክን ከሰየመችበት በኋላም የአንግሊዛውያን ልጆች ከሠማይ መጥቶ በየቤታቸው የሚጎበኛቸውን የመፈለግ አምሮቱ በማየሉ Sinterklaasን (ሲነበብ ሳንታ ክላውስ የሚሉት) አበጁ፡፡[7] ይህም የደቾችን ሳንታክላውስ በሴይንት ኒኮላስ መልክ ሕይወት ዘሩለት፡፡[8] ዳሩ የደቾቹን ታህሳስ 5 ወደ ክሪስማስ ሲያዘዋውሩት መልክና ገጸ ባህርይውን ግን ፍጹም ቀየሩት፡፡ በሳንታ ክላውስ ስም ያቆሙት ገጸ-መልክ የጀርመን ጣኦት-አምላክ የነበረው የቶሆር-Thor (ከእርሱ በኋላ Thursday ተብሎ በስሙ በተሰየመው መጠሪያ የሚታወሰው) ገጽ አቆሙ፡፡[9] ይህ የጀርመን አፈታሪክም የአሁኑን ሳንታ ክላውስ ምንጭ የሚያስረዳን ይሆናል፡፡

ቶሆር የተርታው ሕዝብና የገበሬዎች አምላክ ሲሆን የሚወከለውም በሽማግሌ ነው፡፡ ሽማግሌውም ተጫዋች፣ ወዳጅና ወፍራም ባለ ረጅም ነጭ ጺም ነው፡፡ የተሰራው ከእሳት ሲሆን መልኩም ቀይ ነው፡፡ የመብረቅና ነጎድጓድ ድምጽ የሚፈጠረውም በነጫጭ ሁለት ፍየሎች በሚጎተተው ሰረገላዎቹ ሲጋልብ ሲሆን ከአማልክት በፈረስ የማይጋልብ ብቸኛ እርሱ ነበር፡፡ እጅግ ግዙፍ ከሆኑት ጠጣርና ብናኝ በረዶዎች ጋር ተፋልሞ የዩሎዎች አምላክ ሆነ፡፡ ከግግር በረዶዎች ላይ በሰራው ቤተመንግስቱ በሰሜናዊ ምድር ይኖራል ተብሎ ይነገራል፡፡ በቀደሞቹ ጣኦት አምላኪ ነዋሪዎች ዘንድ እርሱ የሚያዝናና ና ተወዳጅ አምላክ ሲሆን ሰዎችን ፈጽሞ ጎድቶ የማያውቅ ይልቁን የሚጠብቅና የሚረዳ ነው፡፡ በየቤቶቹ ጣራ ላይ ያለው የእሳት መውጫም ለእርሱ የተመረጠ ሲሆን እርሱም በእሳታዊ አካሉ በእሳት መውጫው በኩል ይወርዳል ይባላል፡፡[10]

ዶ/ር ሩሴል ከላይ ከተገለጸው አፈታሪክ ጋር የሚመሳሰል ሓሳቡን በክሪስቲና ሆል[11] የተጻፈውን ጠቅሶ እንዲህ አስፍሯል “በብዙ ሃገራት የሳንታ ስም ቢለያይም የገጸ መልኩ ግን ተመሣሣይ «እርሱ አንድ ምሥጢራዊ የሆነ፣ ከተለመደው የሰው አኗኗር ልማድ የወጣ፣ ቤቱም ወደሰሜን ዋልታ ወይም በጣም የራቀ ሃገር ወይም ከሰማይ የሆነ፣ በፈረስ ጀርባ ወይም በአጋዘን በሚጎተት ጋሪ የሚመጣ፣ በምሽት በምሥጢር የሚገለጥ ወይም በክረምት ላይ በገሃድ የሚታይ፣ በጭስ ማውጫ በኩል ወደቤት በመግባት ስጦታዎችን የሚሰጥ..» እንደ ጥንቱ ጣኦት «የሚጎበኛቸውን ልብ የሚያነብና የተደበቀ ሃሳባቸውንና ድጊቶቻቸውን የሚያውቅ» ነው”[12]

ሌሎች የሳንታን ስም ከናምሩድ[13] ጋር ያገኛኙታል፡፡ በጥንት ጊዜ ናምሩድ እንዴት ይገለጽ እንደነበር በሳሌሚ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው ሼልደን እንደዚህ ጽፏል፡፡ “በረጅሙ የሚወርድ ነጭ ጺም፣ የደመቀ ልብስ፣ የደጋ አጋዘንና የጽድ ዛፍ የያዘ፣ በአየር ላይ እንዲበር ክንፍ የተሰጠው በማድርግ… የናምሩድን ስዕል ሲስሉ ይገልጹበታል……በተመሣሣይ በዚህ ዘመን ሳንታ ክላውስ ላይ እንደሚታየው” [14],[15]

ሳንታ ናምሩድ

በናምሩድንና ሳንታ ክላውስ  መሐል ያለውን አንድነት ማስተዋል ይቻላል፡፡

 

 

 

 

ወደዘመነኛው የሳንታ ክላውስ ገጸ መልክ ስንመጣ ዋነኛ ተጠቃሽ የዚህ ሐሳብ አስፋፊዎች ከሚባሉት የመጀመሪያው ዋሺንግተን ኸርቪንግ ነው፡፡ በ1809 ላይ የልብወለድ ጸሐፊ የነበረው ዋሺንግተን ኸርቪንግ በጻፈው ክኒቸርቦከር[16] በተሰኘ የኒውዮርክ ታሪክ የምጸት (satire) ድርሰት ላይ ስለባለነጭ ጺምና በሚበር ፈረስ ስለሚጋልበው ሴይንት ኒኮላስ በደች ስሙ ሳንታ ክላውስ በተደጋጋሚ ጠቅሶ ጽፏል፡፡ ሌላው በ1822 ላይ ዶ/ር ክሌሜንት ሙር ይህን የክኒቸርቦከርን ድርሰት አንብቦ የሳንታ ክላውስን ገጸ ባህርይ ዋና መሠረት ያደረገውን A Visit From St. Nicholas የግጥም መጽሐፉ ጻፈ፡፡ (ይህ ድርሰት በመጀመሪያው Twas the Night Before Christmas በሚለው ስንኝ ይታወቃል)[17] በስንኙ እንዲህ ይጀምራል “የክሪስማስ ዋዜማ ምሽት ነው….

ፍጥረት ሁሉ ዝምያለው….

አይጥም ቢሆን ከጩኸቱ የታቀበው፡፡ …

ጣራ ላይ ባለው የጭስ ማውጫ …. መቀበያ ተንጠልጥሏል

ተስፋን ይዞ ቅ/ኒኮላስ ….ፈጥኖ ይመጣል በሚል..”

ሙር በዚህም ጽሑፉ ሳንታን ከባለስምንት አጋዘን ጋር ቀረጸው፡፡[18],[19]

ከዚህ በኋላ የባቫሪያኑ ሰዓሊ ቶማስ ናስት የአሁኑን ሳንታ ክላውስ መልክ በማዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ ናስት በሙር ግጥም ላይ መሠረት አድርጎ ከ1862 እስከ 1886 ባሉት ዓመታት ከ2,200 በላይ ካርቱኖችን ለሃርፐር ሳምንታዊ ጋዜጣ ስሏል፡፡ በዚህም ከቀይ ልብሱ በቀር ለሳንታ አሁን የሚታወቀውን ሁሉንም ባህርያት አላብሶታል፡፡[20],[21]

ላውረስ ኬልመን የክሪስማስ እውነተኛ ታሪክ ላይ እንደገለጸው በ1931 የኮካ ኮላ ኮርፖሬሽን የስዊዲሽ አርቲስት ከሆነው ሃደን ሰንድብሎም ጋር የሳንታ መጠጥ ለማምረት ባደረገው ውል የሳንታ ጸጉር ነጭ ሁኖ የ220px-Santa_Claus_kobeተከረከመና ቀይ ልብስ የተጎናጸፈ እንዲሆን እድርጎታል ሲል ጽፏል፡፡[22],[23],[24]

ሳንታ ክላውስ ወይም የገና አባት (?) የጣኦት አምልኮ መሆኑ የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ እርሱ (ሳንታ) በአንድ ምሽት እያንዳንዱን ቤት የሚጎበኝ (Omnipresence-የትምቦታ የሚገኝ)፣ ስለእያንዳንዱ ሕጻን ጠባይ ሁሉንም የሚያውቅ (Omniscience- ሁሉን አዋቂ)ና ጥሩዎችን ሲሸልም ክፉዎችን የሚቀጣ እንደሆነ ሕጻናት ይማራሉ- ልክ እንደ አምላክ!! ክርስቲያን የሆኑ ወላጆች’ኳ ለልጆቻቸው የሚመክሯቸው ሳንታ ምላኬ እንደሆነ ነው፡፡

“ጥሩ ብትሆን ይሻልሃል ሳንታ ከላይ እየተከታተለህ ነው” ወይም

“እስቲ ሂድና ለሳንታ የክሪስማስ ምኞትህን ንገረው” ወዘተ በማለት ወላጆች ልጆቻቸውን በፈጣሪ ፈንታ ሳንታን እንዲያመልኩ ማድረግ ምን ያህል በእግዚአብሔር ፊት አጸያፊ ነው፡፡[25] ዘጸ 20÷3 “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑርህ” ይላል፡፡ ከሳንታ ጋር የተያያዘውን መለኮታዊነት በተመለከተ አንድ ደራሲ የጥንቱ ስጦታ አዳይና በዩሉ ባህል አሁንም ተደብቆ የሚኖረው፤ ባለፉት መ/ክ/ዘመናት ገዢ ሁኖ እንደኖረባት ምድር ወደ አዲስ ዘመን እየተመለስን ይሆን?[26] ብሏል፡፡

ኢሳ 14÷14 ላይ “..በልዑልም እመሰላለሁ..” እንዳለው የእግዚአብሔርን ክብር ይገዳደራል የእግዚአብሔርን ክብሩና ምስጋናውን ይወርስ -በጌታ ክብርም ይተካ ዘንድ፡፡ በየዓመቱ ሚሊየን በሚሆኑ ደቂቅ ሕጻናት ልብና አዕምሮ ውስጥ ይህን ቦታ ሳንታ ይዟል፡፡ ክፉና ሞኝ የሆኑ ጎልማሶችም (ወላጆች) ለሕጻናቱ የሚነግሯቸው መልካሙን ነገሮች ሁሉ ሳንታ እንዲያመጣላቸው እንጂ እግዚአብሔር እንደሆነ አይደለም፡፡ ወደየ ገበያ አዳራሹ ሕጻናት የሚሮጡት “ክርስቶስ የት አለ (የተወለደው ሕጻን)?” ብለው ይመስላችኋል፡፡ አይደለም ፤አልነበረምም፡፡ ለእነርሱ በክሪስማስ እውነተኛ ጀግናቸው ሳንታ ነው እንጂ ክርስቶስ አይደለም፡፡ ልዑልን ይመስላል እንዲል!!

የክሪስማስ ዛፍ ምንጩ ከወዴት ነው?

የጥድ ዛፍ፣ ሐረግ፣ አረንጓዴ ቁጥቋጦ በጥንት ጣኦት አምላኪ በነበሩ ሕዝቦች ዘንድ የዘላለማዊነትና የልምላሜ (ወላድነት) መገለጫ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር፡፡ ምክንያቱም እነዚህ በክረምት የማይጠወልጉ (የማይሞቱ) ሁልጊዜም ለምለሞች ነበሩ፡፡ ይሄም ብቻ ሳይሆን በክረምት ያፈሩ ነበርና በክረምት በዓላት ላይ እነሱን በአስማት ሥርዓታቸው ላይ መጠቀም የአትክልቶች መልሶ መብቀልን (ሕይወት የመቀጠልን) ያመለክቱ ነበር፡፡ የቀደመችው ቤ/ክ ይህን ሥርዓት ብትከለክልም’ኳ ጥልቅ ዘልቆ የኖረ ልማድ ሆናል፡፡[27] በዚህም የጥንታዊያን ባዕድ አምላኪዎች ጣኦታዊ ሥርኣት ክ/ዘመናት አልፎ ይገኛል፡፡[28]

የክሪስማስ ዛፍ በ18ኛው መ/ክ/ዘ ከጀርምን እንደተነሣ ይታሰባል፡፡ ጀርመኖች ከሮማውያን ሮማውያን ደግሞ ከባቢሎናውያንና ግብጻውያን ተቀብለውታል፡፡[29],[30] ለዚህም ላውረስ ኬልመን እንደጻፈው የክሪስማስ ዛፍ ከሮማውያን ሳቹሪናሊያ ጋር አጣምረው ክርስቲያኖች እንደቀዱትና የአይሼሪያ አምልኮ ሥርዓትና ልማድ እንደ ክርስማስ ዛፍ ተቀብለው ተግባራዊ አድገውታል የሚለው ያስረዳል፡፡[31],[32] ቀጥሎ ያለው ደግሞ የባቢሎናውያን ስለክሪስማስ ዛፍ መነሻ ያላቸውን እምነት ያስረዳናል፡፡ የቆየ የባቢሎን ተረት ከሞተ የዛፍ ጉቶ ላይ ድንገት በቅሎ ስለተገኘ ለምለም ዛፍ ይናገራል፡፡ ያ ያረጀ ግንድ የሞተውን ናምሩድ ሲወክል አዲስ የበቀለው ዛፍ (Christmas tree)[33] ታሙዝ ሁኖ ድጋሚ ሕይወት የዘራውን ናምሩድን ይወክላል፡፡ በአስማተኞች[34] (druids) ዘንድ ሉጥ[35] (የዛፍ ዓይነት) የተቀደሰ ሲሆን በግብጻውያን ዘንድ የዘንባባ በሮማውን ዘንድ በሳቹርናሊያ ወቅት በቀያ እንጆሪዎች የሚደምቀው የጥድ ዛፍ የተመረጡ ነበሩ፡፡[36]

የካቶሊክ ባህረ ጥበባት እንደሚገልጸው የብራጋው ሊቀጳጳስ ማርቲን በ575 አካባቢ ቢከለክሉትም በ1605 በስትራስ በርግ የክሪስማስን ዛፍ በግልጽ እንደተጀመረና ወደፈረንሳይና እንግሊዝ በ1840 በመክሌንበርን ልዕልት ሄሊና እና ልዑል ኮንሰርት በየግላቸው እንደተዋወቀ ይገለጻል፡፡[37] አሁን ወደ ዘመነኛው የክሪስማስ ዛፍ አጀማመር ታሪክ ወደሚሆነው ወደ ቅዱስ ቦኒፌስ ታሪክ እንምጣ፡፡ ቅ/ቦኒፌስ እንግሊዛዊ መነኩሴ ሲሆን የጀርመኖቹን አስማተኞች (druids ጎሳ) ከጄስማር ከተማ ወጣ ብሎ ይሰብክ ነበር፡፡ ለእነዚህ አስማተኞች ሉጥ (oak) የተቀደሰ ዛፍ ነው፡፡ እርሱም ይህ ዛፍ ምንም ቅድስና እንደሌለው ለማሳመን ጥረት አደረገ፡፡ ከሚመለኩትም ዛፎች አንዱን ከስሩ ቆረጠው፡፡ ዛፉ ተገነደሰ፡፡ ሲወድቅም ከአንድ ለጋ ጥድ (fir) በቀር ሁሉንም ቁጥቋጦዎች ሰባበራቸው፡፡ አፈታሪኩ እንደሚለው ቅ/ቦኒፌስ የጥዱን መትርፍ ሲመለከት ተአምር ነው ብሎ ተረጎመው፡፡ ይህንንም ዛፍ ‘የክርስቶስ ልጅነት ዛፍ’ (the tree of the Christ Child)[38] ሲል ገለጸው፡፡ ከዚህ የምንረዳው የአሁኑ ክሪስማስ ዛፍ መነሻም የአስማተኞቹ የተቀደሰው ሉጥ ዛፍ ይኸውም የጥንቱ የእስራኤል በኣል መሆኑን ነው፡፡[39] ፌሬል ጅንሰን በ18ኛው መ/ክ/ዘ የነበረውን የቅ/ቦኒፌስን ታሪክ ጠቅሶ እንዳለው “ለኦዲን የሚቀርበው የሉጥ የተቀደሰ ዛፍ መስዋእት ባጌጠ የጥድ ዛፍ ተቀየረ፡፡ መታሰቢያውም የክርስቶስ ልጅነት ነበር” ብሏል፡፡ በዚህ ወቅት እምነት የለሾቹ’ኳ በቤታቸው ይህን ዛፍ ያኖሩ እንደነበር ተጽፏል፡፡[40]

አንዳንዶች የቆየውን ልማድ መጀመሪያ ሉተር ቆርጦ ወደ ቤቱ እንደወሰደና ከዋክብቱን ለመወከል በሻማ እንዳስጌጠው በዚህም የክሪስማስ ዛፍ ተመልሶ ሕይወት እንደዘራ ይገልጻሉ፡፡[41]

በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ‘ቅጠሉ የለመለመ ዛፍ’ ከባዕድና ጣኦት አምልኮ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ተገልጿል፡፡[42] ብዙዎች ዛፎች አረንጓዴ ቢሆኑም እኛ የምናነሣው ሁልጊዜም ስለሚለመልመው አረንጓዴ ዛፍ ነው፡፡ በነብዩ ኤርምያስ 10÷1-5 እንዲህ የሚል ቃል ተጽፏል፡፡

“እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፣ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ የተናገረውን ቃል ስሙ፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- የአሕዛብን መንገድ አትማሩ፤ ከሰማይ ምልክትም አትፍሩ፤ አሕዛብ ይፈሩታልና የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤ ዛፍ ከዱር ይቆረጣል÷ በሠራተኛውም እጅ በመጥረቢያ ይሠራል፡፡ በብርና በወርቅ ያስጌጡታል÷ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል እንደተቀረጸ ዓምድ ናቸው፡፡ እነሱም አይናገሩምና÷ ደግሞም መልካም ይሠሩ ዘንድ አይችሉምና አትፍሩአቸው” (ድምቀቱ የእኔ ነው)

በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ላይ አስተያየቱን የሰጠ አንድ ጸሐፊ እንዲህ ይላል “በኤርምያስ ዘመን የነበሩት ሕዝቦች በመጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው ከዛፍ ጣኦትን ይሰሩ ነበር፡፡ በአሁን ዘመን በቤተ ክርስቲንና በመኖሪያዎች ውስጥ የሚቀመጡት የክሪስማስ ዛፎች ለአምልኮ የተዘጋጁ ዛፎች ናቸው ለማለት አይደለም፡፡ እኛ ያልነው…… በግልጽ ቋንቋ የዛሬ የዛፉ የመጠቀም ልምድ ከጣኦት አምላኪያኖች የመጣ መሆኑን ነው..”[43]

አንድ ጥናት የዛፍ በቤት ውስጥ ስለመቀመጥን ልምድ እንዲህ ይላል”የለመለመ ዛፍ በቤት ውስጥ የማድረግ ድርጊት በዓል ከማክበር የዘለለ ተግባር ነው፡፡ፎቶ እንደምንሰቅለው የተሰበሰቡ ቁጥቋጦዎችን ከሰው በላይ ቢሰቀሉ በብርሃን የተሞላ ቤት ብርሃኑ ደምቆ ካልበራ ቤት የተለየ ተጽእኖ ማሳደር ይችላል፡፡ የተሰቀሉት ጥላ መስራታቸውና ጭለማ መሳባቸው አይቀርም ይሄም የቆመ ሕይወት የያዘ ስዕል ይከስታል፡፡ በተመሳሳይ አማካይ ቁመት ያለው የክሪስማስ ዛፍ ያለብርሃን እንደሰው ቆሞ ይታያል፡፡….. በጨለማ የሚገለጸው….. የጥንት መንፈስ ጥሪ ዓይነት…..”[44]

ክሪስማስ ብዙ የማክበሪያ ቁሶች ይኖሩታል፡፡ በተለይ ከአምልኮና ከጣኦታዊ ሥርኣት ጋር የተያያዙትን ክፉ መንፈስ የመሳብ አቅም አላቸው፡፡ ልክ ማግኔት ብረትን እንደሚያጣብቅ፡፡ የጌታ ልደት መገለጥ በዛፍ አካባቢ ባለ ድምቀት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ መቼ ይሆን ክርስቲያኖች የፈጣሪን ትዕዛዝ የሚያከብሩት “የአሕዛብን መንገድ አትማሩ…..የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና”

የክሪስማስ ወቅት ስጦታ ልውውጡ መጽሐፋዊ ይሆን?

ነጋዴዎች ሁልጊዜ እንደሚያመለክቱት ከዓመታዊ ሽያጪያቸው 60 ከመቶ የሚከናወነው በክሪስማስ የገበያ ወቅት እንደሆነ ነው፡፡[45] ይሄም የሚያመለክተው እጅግ ብዙ ስጦታዎች እንደሚገዙ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ብዙዎች እንደሚያስቡት ስጦታ መለዋወጡ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደተገኘ ነው- ለዚህም የሰብአ ሰገል ታሪክ ይጠቀሳል፡፡

መጽሐፍ እንዲህ ይላል “ኢየሱስም በይሁዳ በቤተልሔም በንጉሥ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ እነሆ ሰብአ ሰገል የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ……… ወደ ቤትም ገብተው ሕጻኑን ከእናቱ ማርያም ጋር አዩት ወድቀውም ሰገዱለት፡፡ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት” ማቴ 2÷1፣2፣11 የጥበብ ሰዎች ለክርስቶስ ስጦታ የሰጡት የአይሁድ ንጉሥ ስለነበረ ነው እንጂ የልደቱ ቀን ስለሆነ አልነበረም፡፡ ይሄ ደግሞ በምስራቅ ሕዝቦች ልማድ ወደ ንጉሥ ሆነ ገዢ ዘንድ ባዶ እጅን መቅረብ ፈጽሞ የተለመደ ስላልነበረ ነው፡፡ ይህ ልማድ በብሉይ ኪዳንም የተመለከተ ነው፡፡[46],[47]

አንድም ሰብአ ሰገል ስጦታ የሰጡት እንደተወለደ አልነበረም፡፡ የቀደመውን ምንባብ በደንብ ካየነው ወደቤት እንጂ ወደ ግርግም አልነበረም የሄዱት፡፡ ቁጥር 16 ላይ ሄሮድስ “ከሰብአ ሰገል እንደተረዳው …….. ሁለት ዓመት የሆናቸውን ሕጻናት” እንዳስገደላቸው ይገልጻል በዚህም ከተወለደ በኋላ እስከ ሁለት ዓመት በሚቆጠር ጊዜ መሐል እንደመጡ እንረዳለን፡፡ እንደውም ስንክሳር ዘወርኃ ታኅሳስ እንደሚለው በሁለት ዓመቱ እንደገበሩለት ይገልጻል፡፡[48] ስለዚህም የልደት ስጦታ አልነበረም የንግሥናው እጅ መንሻ እንጂ፡፡

የጓደኛሞችና የወዳጃሞች የስጦታ ልውውጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም፡፡ ይልቁን ከጣኦት አምላኪያን ልማድ ተቀዳ እንጂ፡፡[49] “በበዓላት ወቅት ስጦታ የመለዋወጥ ትውፊት የጀመረው ክሪስማስ ከመጀመሩ በፊት ነው፡፡ የጥንት ሮማውያን በክረምቱ የሳቹርናሊያ በዓል ወቅት ስጦታ ይለዋወጡ ነበር፡፡” ሲል የሌስሊይ ጎበር የክሪስማስ ወዳጆች የእጅ መጽሐፍ የሚል መጽሐፍን ጠቅሶ ዶ/ር ሩሶል ጽፏል፡፡[50] በመጀመሪያው መ/ክ/ዘ የነበሩ ክርስቲያኖች በክሪስማስ ወቅት ስጦታዎች አይሰጣጡም ነበር፡፡[51] ተርቱሊየንም (de Idol, xiv & v) አጥብቆ ይቃወም እንደነበር የካቶሊክ ባህረ ጥበባት ያስረዳል፡፡[52]

እስቲ በክሪስማስ ወቅት ስጦታ መግዛት የማይችሉትን ከእኛ ዘንድ ያሉ ድሆችን አስቧቸው፡፡ ለምን ይሆን በክሪስማስ ወቅት ቁጣና ስቃይ የሚጨምረው? ሆድ ብሶት፣ ቤተሰብ ውስጥ ጭቅጭቅ ብሎም መፍረስ፣ ራስን ማጥፋት፣ ግድያ በተለይ በምዕራቡ ዓለም በክሪስማስ ወቅት ይጨምራሉ፡፡ ብዙዎችችን ከማህላችን ካሉ ሰዎች ስጦታ በመግዛት አቅማቸው ሲያደኸየው የሚያድርባቸውን ስቃይ ሲናገሩ እንሰማለን ይሄም ወደ ብሶት፣ ተስፋ መቁረጥና ራስን ማጥፋት ይመራቸዋል፡፡ (ስለእኛ ሃገር ልማድና ተያያዥ ጉዳይ የኢትዮጵያን በማነሣበት ክፍል ለመመለስ እናቆየዋለን) ብዙዎች ሊታይ የሚገባው ለመስጠት ማሰቡ ነው ቢሉም እውነታው ግን የከበቡንና የምንማረክባቸው ማስታወቂያዎች የሚነግሩን “ምን ያህል እንደምትወደው ማሳየት የምትችለው ለምትሰጠው ስጦታ ባወጣህው መጠን ነው” እያሉ ነው፡፡ ልደት ተጠርተህ በሄድክበት ቦታ ሁሉ ሰው ስጦታ ሲለዋወጥ ብታይና አንተ ብቻህን ብትቀር ምን ይሰማሃል? እንዲህ ቢያጋጥምህ ያው ሰዎች ራስ ወዳድ ስለሆኑ አንተን እንደረሱህ ማጽናኛ ልትፈጥር ትችላለህ፡፡ ግን ብዙ ሰዎች በክሪስማስ ወቅት ለሌላው ስጦታ የሚሰጡት ለራሳቸው ስጦታዎች ስለሚጠብቁ ነው፡፡

በዓለ ልደት (ጌና) የክርስቲያን ክብረ በዓል ከሆነ……. ይህን ያህል ህመምና የልብ መሰበር በድሆችና በወጪ ምክንያት በሚደኸዩት ውስጥ ለምን ይፈጠራል? ክርስቶስ ፍስሐና ሕይወትን ለተናቁቱ ሁሉ አምጥቷል -ታዲያ ለምን ህመምንና ልብ ስብራትን!? ለክሪስማስ ግብይት ወቅት በግብይት ማዕከላት ያለው መጨናነቅ፣ ለአክስት የሚሆን አንድ ጥሩ ነገር ፍለጋ ከተማዋን ማሰስ፣ ዓመቱን ሙሉ ሲጠራቀም የመጣውን የባንክ ቁጠባ ማውደም ከዚያም ቀሪውን ጊዜ በገንዘብ ቀውስ መሰቃየት…. ይህን ሁሉ በ21ኛው መ/ክ/ዘ ለምን?

በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ቦታ ብቻ ስለስጦታ መለዋወጥ እንደተጠቀሰ ታውቃላችሁ? “በምድር የሚኖሩት በእርሱ ደስ ይላቸዋል በደስታም ይኖራሉ፡፡ እርስ በእርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ፡፡” ራዕ 11÷10 ይህ በእርግጥ የክሪስማስ ወቅትን የሚገልጽ ይመስላል፡፡ ቃሉ የሚነግረን ግን በእግዚአብሔር አገልጋዮች ሞት ምክንያት እርጉሞች የሚያደርጉትን ፈንጠዝያ ነው፡፡ እስቲ ከማስታወቂያዎቹ፣ ከቁሳቁሶቹ፣ ከስካርና ፈንጠዝያ ውስጥ ክርስቲያናዊ የሆነ ነገር ይታያችኋል??

ለመሆኑ ሁለት የገና (ክሪስመስ) በዓል ለምነው የምናከብረው?

አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ስለክርስቶስ ልደት አንዳንድ ጥያቄዎች በመለሱበት ጽሑፋቸው ከላይ ለተነሣው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ልዩነቱ የዶግማ ወይም የነገረ መለኮት ልዩነት ሳይሆን የሣይንሳዊ ቀመር ልዩነት ነው፡፡ እንደሚታወቀው አንድ ዓመት 365 ከሩብ ቀን ይይዛል፡፡ እንዚህ ሩብ ቀናት ተደምረው በአራት ዓመት አንድ ጊዜ አነድ ሙሉ ቀን ይሆኑና ተረፈቀን [53] ይሆናል ዓመቱም ተረፈ ዓመት (leap year) ሲባል 366 ቀናት ይኖሩታል፡፡ ነገር ግን በግሪጎሪሳያውያን የዘመን አቆጣጠር[54] አንድ ዓመት 365 ከሩብ ቀን እና ከ11 ደቂቃ ይሆናል፡፡ ይህ የዓመት አቆጣጠር በ15ኛው መ/ክ/ዘ ከክ.ል.በ የተጀመረ ሲሆን ክርስቶስ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ያለፉት መቶ ክ/ክ/ዘመናት ያልተቆጠሩትን 15 ደቂቃዎች በመደመር ወደ 13 ቀን ገደማ ስላመጧቸው የታህሳስ 25 እና የጥር 7 ሁለት ጊዜያትን ፈጠሩ፡፡

እኛ በፈርኦን የፈለክ ጥናት ስነ-ጥበብ (ሳይንስ) ምርጥነት ምክንያት በኮፕቲክ የዓመት ቀመር ስለምንተማመን የክርስቶስን ልደት በኪሃክ 29 (ጥር 7 በግሪጎሪሳያውያን- [ታህሳስ 29 በኢትዮጵያውያን]) እናከብራለን፡፡ ሌሎች የእኛን ቀመር የሚጋሩ አብያተ ክርስቲያናትም አሉ፡፡[55]

የጎርጎሮሳውያን ዘመን አቆጣጠር ሲመሠረት በዓለማችን ላይ ላለው ልዩነት መሠረት እንደጣለ ዝክረ ዘመን በሚል ማኅበረ ቅዱሳን ያሳተመው መጽሔት ያስረዳል፡፡ ፖፕ ጎረጎርዮስ የጁሊዮስን የዘመን አቆጣጠር እርማት በሠጠበት ጊዜ ካደረጋቸው ማስተካከያዎች የተከሰተ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ያገኘውን የ 10 ቀን ልዩነት ጥቅምት 4 ቀን 1582 ላይ እንዲስተካከል አወጀ፡፡ ይኸውም ኖረንባቸው ግን ያልተቆጠሩ ቀናት ነበሩ በማለት በማግስቱ ጥቅምት 5 በመሆን ፈንታ ጥቅምት 15 ቀን 1582 ሆነ፡፡ በዚህም ከተቀረው ዓለም ጋር የቀናት ልዩነትን አስከተለ፡፡ ይኽንንም ለማገናዘብ ያህል በ1582 ዓ.ም በኢትዮጵያና በአውሮፓውያን መካከል ያለው ዘመን እንድ እንደሆነ ነው፡፡[56]

የልደት በዐልስ ስለምን ማክበር ይገባናል? ገና ወይስ ልደት ትክክለኛ ስያሜ? ኢትዮጵያዊ የገና/ልደት በዓል አከባበር ምን ይመስላል? እግዚብሔር ቢፈቅድ በሚቀጥለው ክፍል የምንዳስሰው ነገረ ጉዳይ ይሆነናል፡፡ ይቆየን!

 

[1] (KELEMEN)

[2] Domenico, Roy Palmer (2002). The regions of Italy: a reference guide to history and culture. Greenwood Publishing Group. p. 21. ISBN 0-313-30733-4.

[3] Collins, Ace (2009). Stories Behind Men of Faith. Zondervan. p. 121. ISBN 9780310564560

[4] Forbes, Bruce David (2007), Christmas: a candid history, University of California Press, ISBN 0-520-25104-0, pp. 68–79.

[5] ታህሳስ 25 የክሪስማስ በዓል መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

[6] (Wikipedia, christmass)

[7] (Salemi)

[8] Jona Lendering (2008-11-20). “Saint Nicholas, Sinterklaas, Santa Claus”. Livius.org. Retrieved 2015-01-25

[9] (Salemi, p. 8)

[10] Handbook of Christian Feasts and Customs (1958), New York: Harcourt, Brace and World, Inc., , pp. 113, 114

[11] ክሪስቲና ሆል, Christmas and Its Customs, p. 42፣43.

[12] (Russell K. Tardo (Dr.))

[13] ናምሩድ በዘፍ 10÷8 ላይ እንደተጠቀሰው የባቢሎን ንጉሥና የአሦራዊያን መሥራች ሲሆን በራእይ 18÷2 ላይ እንደተጠቀሰው ስለባቢሎን ፍጻሜ በነብዩ ኢሳይያስ ተተንብዮለታል ኢሳ 14÷4፣25 እንዲሁም ዴቪድ ፓክ የክሪስማስ እውነተኛ መነሻ ባለው ጽሑፉ ላይ “በራእይ 2÷6፣ 15 ላይ እንደምናነበው ክርስቶስ የኒቆላውንን ትምህርት እንደሚጠላና የእነርሱ ትምህርት የሚጠብቁ ሰዎች በእርሱ ዘንድ ስላሉ እንደሚነቅፈው ተጽፏል፡፡ ኒቆላውያን የኒቆላስ ተከታዮች ሲሆኑ ኒኮስ ‘ድል አድራጊ፣ አጥፊ’ ማለት ሲሆን ላኦስ ማለት ‘ሕዝብ’ ማለት ነው፡፡ በዚህም ኒቆላውያን ማለት የድል አድራጊው ወይም አጥፊው የናምሩድ ተከታይ ማለት” ነው ብሏል፡፡ (David C. Pack)

[14] ከእኔ ማጉያ ሃሳብ ጭማሪ ጋር (Is Christmas Christian? Sheldon Emry, p.12). (Salemi, p. 9)

[15] እንደ ላንገር የዓለም ታሪክ ባህረ ጥበባት ገለጻ ሳንታ በታናሿ እስያ የተለመደ የናምሩድ ስም ነው፡፡ እርሱም በጭስ መውጫ በኩል የሚወርድ የእሳት አምላክ ነው ይላል፡፡ (David C. Pack)

[16] The Legend of Sleepy Hollow and Rip Van Winkle ከፍተኛ ዝናን ያተረፈለት ድርሰቱ ሲሆን Knickerbocker በደች ባህል ላይ የተጻፈ የምጸት (satire) ድርሰቱ ነው፡፡

[17]The history of Christmas: Christmas history in America, 2006 ላይ የተገኘ፤ retraived on 25/01/2015

[18] (KELEMEN)

[19] Forbes, Bruce David, Christmas: a candid history, pp. 80–81.

[20] (Wikipedia, Christmas)

[21] (KELEMEN)

[22] ዝኒ ከማሁ

[23] Mikkelson, Barbara and David P., “The Claus That Refreshes”, Snopes.com, 2006.

[24] (Wikipedia, p. christmass)

[25] (Russell K. Tardo (Dr.))

[26] ክሪስቲና ሆል, Christmas and Its Customs, p. 36

[27] ዝኒ ከማሁ ገጽ 21፣22

[28] R. F. Becker. The Truth About Christmas, pp. 19.20.

[29] (David C. Pack)

[30] (Roll, 1995)

[31] (KELEMEN)

[32] (Wikipedia) van Renterghem, Tony. When Santa was a shaman. St. Paul: Llewellyn Publications, 1995. ISBN 1-56718-765-X

[33] አሌክሳንደር ሂስሎፕ The Two Babylons ላይ የክሪስማስ ዛፍ የናምሩድን በታህሳስ 25 በድጋሚ የመወለዱን ትንሣኤ ያመለክታል ይላል፡፡ ገጽ 98.

[34] በአስማተኞች (druids) አስተምህሮ አንድ አምላክ ሲኖር ስሙም በኣል ይባላል፡፡ የሴልቴክ የቅሪት መሳሪያዎች እንዳስረዱት በኣል ማለት የሁሉ ነገር ሕይወት ወይም የፍጥረት ሁሉ ምንጭ ማለት ነው፡፡ በኣል በዛፍ እንደሚመለከው የጥንት አውሮፓ ድሩዶችም በተመሳሳይ ሲያመልኩ እንደነበር ጥርጥር የለውም፡፡ (Salemi, p. 6)

[35] የካቶሊክ ባህረ ጥበባት vol. V. p.162 እንደገለጸው የሉጥ (oak) ዛፍ እነሱ አምላክ የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱሱ በኣል ነው፡፡ መሣ 2÷13፣      2ኛ ነገ 10÷26-28

[36] Walsh, Curiosities of Popular Customs, p. 242

[37] (Martindale, 1908)

[38] Frazer, in The Golden Bough

[39] (Salemi, p. 6)

[40] (Ferrell Jenkins, 2005, p. 3)

[41] (KELEMEN)

[42] ዘዳ 12÷2፣ 1ኛ ነገ 14÷23፣ 2ኛ ነገ 16÷4፣ ሕዝ 6÷13

[43] ራልፍ ዉድሮው Babylon Mystery Religion. pp. 165፣166

[44] ዊሊያም ሳንሰም A Book of Christmas, pp. 45፣46

[45] በአሜሪካ የተደረገ ጥናት ነው (David C. Pack)

[46] (Adam Clarke, p. 46)

[47] ራልፍ ዉድሮው Babylon Mystery Religion, p. 164

[48] (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን, ፲፱፻፺፬ ዓ.ም, ገጽ ፭፻፵፪)

[49] ክሪስቲና ሆል, Christmas and Its Customs, p. 35

[50] (Russell K. Tardo (Dr.), p. 8)

[51] ክሪስቲና ሆል Christmas and Its Customs, p. 36

[52] (Catholic church, Christmas)

[53] Leap day በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ጳጉሜን ስድስት የምትሆንበት ቀን ሲሆን ዘመኑም ዘመነ ዮሐንስ ይሆናል፡፡

[54] እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ማለት ነው፡፡

[55] (Shenouda III, 1999, pp. 20-21)

[56] (ማኅበረ ቅዱሳን, ፳፻ ዓ.ም, ገጽ ፳፮)

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑