Christmas Vs ገና Vs Nativity – ክፍል አራት

Christmas Vs ገና Vs Nativityክፍል አራት

  • P ገና ወይስ ልደት ትክክለኛ ስያሜ?            
  • P ኢትዮጵያዊ የገና/ልደት በዓል አከባበር ምን ይመስላል?

To read in PDF

 በቀደሙት ሦስት ተከታታይ ክፍሎች ከጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደትና በዓል ጋር ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን እያነሣን ለዛሬ ማቆየታችን የሚታወስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ፈቅዶልን ቀጣዩን ክፍል እንዲህ አሰናድተንዋል፡፡

ገና ወይስ ልደት ትክክለኛ ስያሜ?

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ (አሁን እየቀነሰ ነው ለማለት ያህል ነው) “እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ” ከሚል የመልካም ምኞት መግለጫ መረዳት እንደምንችለው በዓሉ የልደት በዓል መሆኑን ነው፡፡ መወለዱ የሚበሰርለትም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ የእርሱ የመወለድ ዜና ታላቅ የምስራች፣ ዓለም ካጨለማት የሰይጣናዊ ግብር ጽልመት ተገፍፎ ይበራላትና ሁሉን አድራጊ፣ ሁሉን ፈጣሪ የሆነው ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስን ትቀበለው ዘንድ ደስታ የሚዘራበት በዓል ነው፡፡ እንኳን ለእውነተኛ (ጽድቅ) ፀሐይ መገለጥ፣ ሰው መሆን፣ በጠባብ ደረት በአጭር ቁመት መወሰንና እኛን መምሰል አደረሳችሁ ሲል እንደሆነ የምኞት ቃሉ ያስረዳናል፡፡ አሁን እየተለመደ የመጣው ግን “እንኳን ለገና በዓል አደረሳችሁ!” ማለትን ነው፡፡ ስለዚህ ‘ገና’ ምን ማለት ነው የሚለውን ወደማየት እንገባለን፡፡

ጌና ….ገና …. ገናና

የገና ስያሜ ወይም ትርጉም መምህር ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት ሐዲስ ላይ ጌና ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ጌና ከጽር[1] የተገኘ ሲሆን የልደት ዋዜማ መጠሪያ ወይም ድራር[2] ማለት ነው፡፡ ይኸውም ገሃድ ወይም ልደት፣ በዓለ ልደት ማለት ነው፡፡ የቀድሞ ስንክሳር የታህሳስ 28 ወይም 29 መግቢያ “እንተ በኵሉ ክብርት ጌና ዘይእቲ ልደቱ በሥጋ”[3] ሲል የልደት በዓልን -ገና ብሎ እንደሚጠራ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ጠቅሰዋል፡፡[4] በ1994 በትንሣኤ ማተሚያ ድርጅት የታተመው ስንክሳር ዘወርኃ ታኅሳስ “እምኵሎን በዓላት ዕለተ ልደቱ ለእግወዉ ኢየሱስ ክርስቶስ…” በማለት መግቢያውን የገናን ስያሜ ቀይሮ ጽፎታል፡፡[5]

ከዚህ የምንረዳው የገና ስያሜ ከልደት በዓልነት እየወጣና ወደ ትውፊታዊ ጨዋታው ስያሜነት እየተሳበ የሚገኝ መሆኑን ነው፡፡ ገና መምህር ኪዳነ ወልድ እንዳሉት፤ ብዙ የኢትዮጵያን ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ የመስህብ ቦታዎች የሚያስጎበኙ ድርጅቶች እንደሚሉት ቃሉ ከግሪክ ገናና ከሚል ቃል የተገኘ እንደሆነ አባቶች ያሏቸውን ጠቅሰው ጽፈዋል፡፡ ትርጉሙም በእንግሊዘኛ ‘imminent’- የጊዜው መድረስ፣ ሊፈጸም ያለው እንደማለት ሲሆን የጌታ መምጣትና የሰው ልጅን ከኃጢአት መንጻት ለመግለጽ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡[6]

የገና ሌላኛው ስያሜ (ትርጉም አለመሆኑን ልብ ይሏል) የምዕራባውያን ሆኪ(hockey) ጨዋታ የመሰለውን የኢትዮጵያውያን ጨዋታ መጠሪያ ነው፡፡ የኢትዮጵያውን አፈታሪክ እንደሚያስረዳው እረኞች የክርስቶስን መወለድ በሰሙ ጊዜ እንደተደሰቱና በደስታቸውም ወቅት በሚያግዱበት በትር (ዱላ) ጨዋታ እንደጀመሩ ይነግረናል፡፡ ይህን የተከተለው ጨዋታ በገና በዓል ላይ ወጣቶችንና ወንዶች ይጫወቱታል፡፡ ጨዋታውን በሚዳኙት ሽማግሌዎችና ጨዋታውን በሚከታተለው ነዋሪ የገናው ጨዋታ ይደምቃል፡፡

የተለያዩ አባቶችና አዛውንቶችን ስለገና ስያሜ ለማናገር ሞክሬያለሁ፡፡ ብዙዎቹ ገና የልደት በዓል ሌላኛው መጠሪያ እንደሆነና እንዲሁም የበዓሉ ጨዋታም የገና ጨዋታ እንደሚባል ያስረዳሉ፡፡ ዳሩ ብዙ ወጣቶች (ከእኔ ጋር ጨዋታ የነበራቸው) የሚገምቱት ገና ማለት ከጨዋታው ጋር የተያያዘ እንደሆነና የእርሱ መጠሪያ ስያሜ እንደሆነ ነው፡፡

ከላይ ለማየት እንደሞከርነው በቀደመው ጊዜ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከዋዜማ አንስቶ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ያለውን ጊዜ ገና እንደሚባል ሲሆን በዚህ ክብረ በዓል ላይ ያለው ባህላዊና ትውፊታዊ ጨዋታም የገና ጨዋታ እንደሚባል ነው፡፡ እርግጥ ከግሪክ (ጽር) የገና ስያሜ መጣነት ለማረጋገጥ ያደረኩት ጥረት ለጊዜው አልተሳካልኝም፡፡ በትውፊት ያገኙትን ትርጉም ያስቀመጡት ትርጉሙ ከጌታ ልደት ጋር የተያያዘ እንጂ ከጨዋታው ጋር አለመሆኑን ያስረዳናል፡፡ እንዴታ በዛ በዓል ላይ ልዩ ጨዋታ ስላለ የዛ በዓል (ገና) ጨዋታ ተብሏል፡፡

genaበመሆኑም በበለጠ ጥናት ልዩነቱ እስኪሰፋልኝ ገና- የጌታ በዓል የሚከበርበት በዓል (ልደት) ስያሜ መሆኑን መቀበል ይገባኛል፡፡ የልደት በዓልን የገና በዓል ማለት ሃይማኖትን ከዓለማዊ (Secular) ወይም ባህላዊ ልማድ ጋር ማጣረስ አይመስለኝም፡፡ ዳሩ የእኛ የኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ በዓላት (በተለይ የክርስትና እምነት ተከታዩ) በባህላዊ ትውፊት የበለጸጉ የሃገር በዓላት (የእምነቱ ተከታይ ብቻ ያልሆነ) ናቸው፡፡

ኢትዮጵያዊ የገና/ልደት በዓል አከባበር ምን ይመስላል?

አስቀድመን እንዳልነው የኢትዮጵያውያንና ሃይማኖታዊ በዓላት[7] ከባህላዊ ትውፊት ጋር ለይቶ ማየት የሚከብዳና ፍትሃዊ የማይሆን ነው፡፡ ከእምነት ሥርዓት ሰፍተውና ባህላዊ ልማዳትን አጎልብተው ብሔራዊ በዓላት አድርገውታል፡፡ ስለሆነም ከእምነት በዓላቱ ውስጥ የሃይማኖታዊ ሥርዓት ትውፊትና የባህላዊ ልማድ ትውፊት ተሰባጥረው እናገኛለን፡፡

የልደት/ገና በዓልን ስናስብ እንዲሁ ነው፡፡ በዘመናችን ደግሞ ሌላ ሦስተኛ ወገን ገብቶበታል፡፡ የባዕድ ሃገራት ልማድና ሥርዓት ተቀላቅለውበት ጉራማይሌ አከባበር ላይ እንገኛለን፡፡ በተለይ በከተማና ራሳቸውን ከተማ አድርገው በሚቆጥሩ የሃገሪቷ ክፍሎች ይኸው የባህልና የሃይማኖት ወረራ የሆነ ልማድ/ሥርዓት በይበልጥ እየሰፈነ ይገኛል፡፡ በዚህም በሃገሪቷ ራሱን ዓለማዊ (Secular) ወይም እምነት የለሽ (atheists) አድርጎ የሚቆጥር ክፍል እየተፈጠረ ይገኛል፡፡ ይህ አንጃ ግን መነሻው የሃገሪቷ እምነትና ባህል ቢሆንም አሁን ደርሶ አንድም ለእምነቱም ሆነ ለባህሉ በቂ ማፋለሻ (disproof) ሳያቀርብ ወይም የያዘውን እምነት ሳይለቅ ባህሉንም እንደለበሰ ሌላ ‘የሰለጠነ’ ወይም ‘የዘመነ’ የመሰለውን፤ መነሻና መድረሻውን የማያውቀውን ባህል ይቀነብባል፡፡ ይደርበዋልም፡፡ ለዚህም የረዳው ግዴለሽነቱና ምን አገባኝ ስሜቱ፤ ራሱን ከዘመነው ጋር ያዘመነ እየመሰለውና የራሱን ባህል በመናቅ ባህር ውስጥ በመዘፈቁ ነው፡፡

ይህ ክፍል የሁሉም ነገር ማስተጋቢያና ማስተላለፊያ እንደሆነ ሳይሆን ከሁሉም ነጻ የሆነ (neutral) አድርጎ በማሰብ ራሱን ተራማጅ፣ ሃገሩን ቀያሪና አሳዳጊ አድርጎ ይመለከታል፡፡ በዓለም የትኛውም ታሪክ ውስጥ ሃገር ያለማንነት አልተገነባችም፡፡ የሚያቆያት ያ ማንነቷ ሲሆን የሚያጠፋት ደግሞ ማንነት አልባ መሆኗ ሳይሆን ያንን መሠረተ ማንነቷን አለመጠበቋ ነው፡፡ ጠፋች ስንል ወደመች ባድመ ምድረ በዳ ሆነች ማለታችን አይደለም እርግጥ እርሱም ባይቀርላትምና የሆነችው ከዚህ ባያንስም ጠፋች ስንል መሠረቷን በመርሳቷ ወይም በማስወሰዷ ወይም የሌላ ማንነት በመውረሷ ሲሆን ከዛ በኋላ መገለጫዋ ሌላ ማንነት፤ ሌላ ሕይወት ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ለውጡ ልክ አባጨጓሬ ወደ ቢራቢሮነት እንደመቀየር ያለ የመሻሻል ለውጥ፣ ሃገርን ከነበረችበት ማንነት ወደ በለጠ ማንነት ነው እንዳንል፡- አዲሱ ማንነቷ የተዋቀረው በቀደመ ማንነቷ ላይ ሳይሆን ከወረሰቻቸው (ከቀዳቻቸው) የማታውቃቸውና ያላቦካቻቸው ጭቃ ማንነቶች በመሆኑ የምናገኛት አዲሲቷን የለውጥ ሃገር ሳይሆን ሌላኛይቷን ባዕድ ሃገር መስላ ነው፡፡ ሌላ ቅጂ ሃገር! ይሄ ደግሞ ምድረ በዳ ከመሆን አይሻልም፡፡

ብዙዎች ሲናገሩ እሰማለሁ፡- ምእራባዊቷ አሜሪካ ባህል የላትም ሲሉ፡፡ ከእኛ መሠረተ ባህሎች አንጻር ተመሳሳይነት የሌላቸው ሆነው ይሆናል እንጂ ባህል የሌለው ሃገር የለም፡፡ ምእራባዊ ባህል ብለን የምንጠራው ምንጩ ከዚህችው ሃገር ነው፡፡ ከእምነት አንጻር ካየነው የኢትዮጵ ቤተ ክርስቲያን ዓለም እንቅልፉን ከድንጋይ ላይ ሲለጥጥ በነበረበት ዘመን እርሷ ድንጋይን በፈጠረ አምላክ አምልኮ ስትቃትት ነበረች፤ የክርስትና እምነት መነሻ የነበረውን የአይሁድ እምነትና ክርስትናን አጣምራ ይዛ የተገኘች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ የክርስትና እምነትን ከሃይማኖት ቧንቧዎች የቀዳችው ሳይሆን ከምንጩ ላይ በእጇ የቀመሰችው ኢትዮጵያዊት ቤ/ክ ነች፡፡ ለሦስት ሺህ ዘመናትም የራሷ እምነት ሆኖላት የራሷን መምህራን፣ ሊቃውንት፣ አሳብያን፣ ጠቢባንና መሪዎችን አፍርታ ኢትዮጵያዊነት ያለው ክርሰትናን አቆይታለች፡፡

ከዚህ በላይ ያነሣናቸው ባይተዋሮች፣ ራሳቸውን እንደ ዘመናዊ የሚቆጥሩቱ ምናልባት እምነታቸው ክርስትና ባህላቸው ኢትዮጵያዊ ነው ግና አስቀድመን እንዳልነው በቸልተኝነትና በግዴለሽነታቸው የእምነት ሥርኣታቸው እንዳይፈጽሙት ያሰራቸው ይመስላቸዋል፤ ባህላቸው ደግሞ ያረጀና ኋላ ቀር ይሆንባቸዋል፡፡ እናም ላረጀው ባህል የታደሰ ለሚያስረው እምነት ልቅነትን ይናፍቃሉ፡፡ ስለዚህም እምነትን ስሙን ተላብሰው ግብራቸው ግብረ-ባዕድ ይሆናል፡፡ የመጤውን (ለባዕድ ሃገር) ባህል እጅ ነስተው ይቀበሉታል፡፡ የታደሱበት ይመስል ሊጠፉበት ይቀውሱበታል፡፡

የገና/ልደት በኣል አከባበራችንን ስናየው ይበልጡን በቀደሙት ክፍሎች ያነሣናቸውን የበዓል አከባበር ልማዶች ተሰንገውበት እናገኘዋለን፡፡ ከዋዜማ እሰከ ተፍጻሜተ በኣሉ በዳንኪራና ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ፣ በስካርና ዝሙት፣ በምግብና አልባሳት ሽሚያ ይደምቁበታል፡፡ የምሽት ክበቦች በራቸው በሰፊው የሚከፈተው፣ የሚታደሰውና የሚመረቀው የገና በዓልን አስታኮ ይመስላል፡፡ በየቤቱ ከሚያድረው በየመንገዱና በየማጎሪያው የሚደፋውና የሚንከለበሰው ይበልጣል ማለት ያስደፍራል፡፡ የሃገሩን ቄጤማ የሚጸየፈው በሺህ ብሮች የሚገዛው የክሪስማስ ዛፍ ክብር እንዲሞላለት ያስባል፡፡ አስገራሚው ነገር ደግሞ በእነዚህ ክንውኖች ላይ ሲሳተፍ የምናገኘው ክርስቲያን ነኝ የሚለው ነው፡፡ ለመሆኑ በዓሉ የማነው? በየትኛው እንቅስቃሴዎች የጌታን መወለድ እንደሚያስቡት የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ ወይም የትኛው ምልክት በዓሉ የጌታ ልደት መሆኑን እንደሚገልጽ መረዳት የሚያስቸግር ነው፡፡ እምነታችን ክርስትና ነው የሚሉትን ትተን እንኳ በባህል ኢትዮጵያዊ የሆኑት በየትኛው አከባበራቸው ኢትዮጵያዊ እንደሚሸቱ ማሰብ አስገራሚ ነው!

ነጭ የሃገር ባህል ልብስ መልበሱ ይሆን? የገና ጨዋታ መጫወቱ? ዘመድ አዝማድ በመጠያየቁ? በማስታረቅና የታመመ በመጠየቁ? ለታረዘና ለተራበው በመለገሱስ ይሆን? እንደው ሁሉንም ሊያግባቡ የሚችሉና ዘመን የማያጠወልጋቸው ባህሎች ይሆናሉ ያልኳቸውን ለማንሳት ያህል እንጂ በየሃገሩና በየስፍራው ያሉቱ መገለጫዎች የበዙ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡

ነጭ ወይም የሃገር ባህል ልብሱ ከሃገር ለወጡት የተተወ ይመስላል ምናልባት እነሱ የሚናፍቃቸው ስለሆነ ይሆን? የገና ጨዋታው ከነሙሉ ትዝታው የህንጻ ጫካና የመኪና ጉማጆች ወዳልበዙበት መንደር ተሰዷል፡፡ ለዘመድ አዝማድ ጥየቃ ያለው ጉዞና የወዳጅነት ጨዋታው ‘ዘመናዊ’ በሆነው ‘ግላዊነት’ በመጠመቁ ለግል ለሚያጠፉት ጊዜው አልበቃ ያላቸው ይመስላሉ፡፡ ማስታረቅና የታመመ ማሰቡ -እንኳን ወጣቱ አዛውንቱም ዳግቷቸው በየቤታቸው ባለ ጩኸት የደነቆሩ ይመስላሉ፡፡ የራበው ሰው – ለሆዳቸው በሰበሰቡት ዓይነት ምግብና መጠጥ በተጨናነቀ ሆዳቸው ምክንያት እርሱን እንዳያስቡት የፈረደበት ይመስላል፡፡ የታረዘው በክሪስማስ በሚዘንበው ብናኝ በረዶ የሚሸፈን ይመስላቸው ይሆን ያሰኛል ያው በየቤቶቹ የሞሉት ምዕራባዊ ዜማ፣ ምኞትና ቁሳ ቁስ ስለሆነ፡፡ ነው ወይስ ሃገሪቷ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ እየተሰለፈች ስለሆነ ይሆን¡¡

አንተ ክርሰቲያን ነኝ የምትል በበዓሉ ውሎህ የጌታን መወለድ እንዴት እንዳስታወስከው ብትነግረን እንዴት ደስ ባለን፡፡ ስሙ እየተጠራ በሚወደስበትና በሚከበርበት ሥፍራ ተገኝተህ ይሆን? ስለመወለዱ ክብር በሚዜምበትና እረኞችን በሆን ከሚባልበት ደጃፍ ረግጠህ ይሆን? ዋዜማውን ስለመወለዱ ክብርና ጸጋ እየተሞላህ በቅድስቱ ተገኝተህ ይሆን? ሌሊቱን የምስራቹን ለማብሰር በብርሃን ታጅበህ በየመንደሩ ተገልጠህ ይሆን? ነው ወይስ እኒያ ቀን የጣላቸውን ሰብስበህ በዓሉ የእነርሱም እንደሆነ እያበሰርክ ይሆን? እስቲ የበዓሉ ምሽትና ውሎኣችሁን አካፍሉን…….

የልደት በዐልስ ስለምን ማክበር ይገባናል? ለቀጣዩ የመጨረሻ ክፍል ይቆየን!

[1] ጽር የግሪክ ጥንታዊ ቋንቋ የነበረ ነው፡፡

[2] ድራር ማለት ድሮ፣ ዋዜማ፣ ቅበላ፣ የማታ ምግብ ማለት ሲሆን ጾመ ድረረ ሲል ልደት ወይም ጥምቀት እንደማለት ነው፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ, ፲፱፻፹፬ ዓ.ም, ገጽ. 325)

[3] በሥጋ የተወለደባት ከሁሉም የከበረችው ገና ናት እንደማለት ነው፡፡

[4] (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ, ፲፱፻፹፬ ዓ.ም, መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ-ንባቡ በግዕዝ ፍቺው ባማርኛ, ገጽ. 325)፣ ተረ. ቄር 25

[5] (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን, ፲፱፻፺፬ ዓ.ም, ገጽ. 542)

[6] Adopted from http://awazetours.com/Visit-Ethiopia/Ethiopian-Festivals/Ethiopian-Christmas.html and http://www.ethiopiauncovered.com/specialevents/gennaethiopianchristmas/default.aspx retrieved date January 12, 2015

[7] የኢትዮጵውያን ሃይማኖታዊ በዓላት ሲባል በሃገሪቷ ሥሩን ሰዶ፣ ተንሰራፍቶና መሠረቱን ይዞ የሃገሪቷ መለያ የነበረውና የሆነው የክርስትና እምነት በዓላት ማለታችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ የክርስትና ታሪክ የኢትዮጵያ ታሪክ ነውና፡፡ ይህ ማለት አሁን መንግስትና ሃይማኖት የዝምድና ሰንሰለታቸው ተበጥሷል በሚባልበት ዘመን የማይነሳ ደረቅ የታሪክ ሀቅ ነው ማለት አይደለም፡፡ የዛሬዋ መነሻ ይህ ደረቁ ታሪክ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ታሪክን ማውሳት ትላንትን የመናፈቅ ጽንፈኝነት ሳይሆን መነሻን ለመረዳት ያለ ጉጉትና ግዴታ ነው፡፡ ታሪክ ከነአሳር ግሳንግሱ (በጎም ሆነ መልካም ያልሆነውን ጨምሮ) ተፈጽሞ ያለፈ እንደነበረ መቀበል ይኖርብናል-ያልተዛባ እስከሆነ ድረስ፡፡ ይህም እምነት ለዛሬው እየቀጠለ ላለው ታሪክ ውለታ መዋል ነው- የጠፋና ያልተያያዘ ታሪክ ባለመስራት፡፡ ዛሬ ላይ

ትላንት መልካም ተደርጓል ማለት የነበሩት መልካምነት አልባ ታሪኮችን መደምሰስ ማለት አይደለም፡፡ ወይም የትላንት ታሪክ ጠባሳዎችን ዛሬ ላይ ማንሣት ትላንት በሙላው መልካምነት የተነፈገው ጠባሳ የሞላው ብቻ ነው ማለትም አይደለም፡፡ ሁለቱም (ጠባሳውም ንቅሳቱም) ያስፈልጉናል፡፡ በአንድ ወቅት በታሪክ አጋጣሚ የተፈጸሙ የእኛው ታሪኮች ናቸውና፡፡ ምን እንኳ ባንካፈልባቸውም እነኚሁ ታሪኮች ዛሬ ላይ እኛን ፈጥረዋል፡፡ እኛም በዘመናችን እንዲሁ እያደረግን እንገኛለን፡፡ ለአንዱ ጥሩ ንቅሳት ስናበጅ ለሌላው ጠባሳ እናተርፋለን፡፡ እንደግለሰብ፣ እንደ ሕዝብ፣ እንደማኅበረሰብ ሆነ እንደ መንግስት ይህ የእኛ የዛሬ ሥራችን ነው የነገዋ የሃገራችን ታሪክ፡፡

One thought on “Christmas Vs ገና Vs Nativity – ክፍል አራት

Add yours

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑