የመንግስት ብክነት፡ በቢሊዮንና በሚሊዮን—–

ዮሃንስ ሰ. አዲስ አድማስ

• የመንግስት ኤሌክትሪክ፡ በአመት ከ6 ቢ. ብር በላይ ያከስረናል
• የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል፤ የ5 ሚሊዮን ብር ‘አስደናቂ ድራማ’
image

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ እንደ ኡጋንዳ ቢሻሻል፣… በአመት 6 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ሃብት መፍጠር ይቻል ነበር ይላል፣ የአለም ባንክ ያወጣው አዲስ ሪፖርት። እንደ ጋና ማሻሻል ደግሞ ከዚያ የበለጠ ጥቅም ያስገኛል።
የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የጋናን ያህል ሳይሻሻል በመቅረቱ ብቻ፣… … ኢትዮጵያዊያን፣ በየአመቱ 7 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እንደሚደርስባቸው ሪፖርቱ ያመለክታል። ኤሌክትሪክ በየእለቱ ስለሚቆራረጥ፣ የኤሌክትሪክ መስመር ለማግኘት ብዙ ጊዜ ስለሚፈጅ፣ ወዘተ ማለት ነው። (Report No: 99399-ET Ethiopia’s Great Run፡ November 18, 2015፡ ገፅ 137)።

ያው፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆን የተደረገው፣ አገልግሎት ለማስፋፋትና ለኢኮኖሚ እድገት ለሚጠቅሙ ፋብሪካዎች በቂ ሃይል ለማቅረብ እንደሆነ ሲገለፅ በየአመቱ እንሰማለን። ነገር ግን፣ ወደ ኋላ ነው ያስቀረን። እንዲያውም፣ ከኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመር ይልቅ፤ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ላይ፣ ደህና ስኬት የተገኘው፣ የማመንጫ ጣቢያዎቹ በመንግስት ሳይሆን፣ በኮንትራት ለኩባንያዎች ተሰጥተው ስለሚገነቡ ነው።

ያለአገልግሎት ያረጁ መሳሪያዎችን ለመተካት፣ አዳዲስ ተገዝተው ይመጣሉ – በ1.5 ቢሊዮን ብር ብድር።
ለእንፋሎት ሃይል ፍለጋ፣ ጥልቅ ጉድጓድ ለመቆፈር ለሁለት ማሽኖች መግዢያ፣ 65 ሚሊዮን ዶላር ብድር እንደመደበ ይገልፃል – ባንኩ። በጣም ውድ ናቸው። አንዱ ማሽን 35 ሚሊዮን ዶላር (ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ) ይፈጃል ማለት ነው። ያ ሁሉ ገንዘብ ወጥቶባቸው፣ አገልግሎት ይሰጣሉ ወይ ነው ጥያቄው። እንዴት ብትሉ፣ ከአመታት በፊት የተገዙ ሁለት መቆፈሪያ ማሽኖች፣ ከአስር ዓመት በላይ፣ ያለ አገልግሎት መጋዘን ውስጥ ተቀምጠው እንዳረጁ የአለም ባንክ በሪፖርቱ አስታውሷል።

(አንደኛው መቆፈሪያ ማሽን፣ በቅርቡ እድሳትና ጥገና ቢደረግለትም፤ አገልግሎቱ ለጊዜው ነው። ይህንን መቆፈሪያ ማሽን ለመተካት ነው፤ አዲስ ማሽን በ700 ሚሊዮን ብር ተገዝቶ የሚመጣው። በዚያ ላይ፣ ያለ አገልግሎት ያረጁት ማሽኖች፣ የእድሳትና የጥገና ወጪያቸው ቀላል ስለማይሆን፣ ‘ያዋጣል ወይ?’ ተብሎ መታሰብ እንዳለበት ባንኩ አሳስቧል።)

በአጭሩ… እነዚያ ውድ ማሽኖች፣ በከንቱ እድሜያቸውን ጨርሰዋል ማለት ይቻላል። የመንግስት ብክነት እንዲህ፣ ከባድ ነው። (ገፅ 46፡ Report No: 83994-ET፡ GEOTHERMAL SECTOR DEVELOPMENT PROJECT፡ May 5, 2014)።

የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል፤ የ5 ሚሊዮን ብር ‘አስደናቂ ድራማ’

የቱሪዝም ኢንደስትሪን ዕድገት ለማፋጠን፣… የሰለጠነ የሰው ኃይል በጥራት ማፍራት! (በ8 የቆርቆሮ ክፍሎች? ያለ መማሪያ መፅሃፍ?)

ሞዴል ሆቴል ገንብቶ፣ ከሁሉም በላቀ የሙያ ብቃት፣ የሌሎችን አቅም ይገነባል! (የማሰልጠኛ ክፍሎችን አድሳላሁ ብሎ፣ በቦምብ የታረሱ እያስመሰለ?)

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የስልጠና ብቃቱን በማሻሻል፤ በምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ ማዕከል ይሆናል (አንዲት የኢንተርኔት መስመር መዘርጋት እያቃተው?)

ለተማሪዎች የመማሪያ መፅሃፍ የማይሰጥ የስልጠና ማዕከል ይታያችሁ! ምናልባት ተማሪዎች፣ ቤተመፃህፍት እየገቡ ይጠቀማሉ እንዳይባል፤ እዚያም ከቁጥር የሚገባ መፅሃፍ የለም። ለምን እንደሆነ የቤተመፃህፍት ሃላፊው ምላሽ አላቸው።

ለመፃህፍት ግዢ፣ በመንግስት መመሪያ መሰረት፣ ጨረታ ማዘጋጀት እንኳ ባይቻል፣ ቢያንስ ቢያንስ ከተለያዩ ቦታዎች፣ የዋጋ መጠን አጠያይቆ፣ መረጃ መሰብሰብ ያስፈልጋል። መረጃው፣… ለግዢ ኮሚቴ፣ ለበላይ አካል፣ ለፋይናንስ ሃላፊ ወዘተ… ቀርቦ፣ ቀጠሮ ተይዞለት፣ ስብሰባዎች ተጠርተው፣ ውይይቶች ተካሂደው፣ የውሳኔ ሃሳቦች ቀርበው፣ ለውሳኔና ለአስተያየት ወደ ሚመለከታቸው ሃላፊዎች ተመርተው… …በጀት ተይዞለት እንደሆነ ተጣርቶ… እስኪወሰን፣ የበጀት አመቱ ያልቃል። ወይም ደግሞ፣ መጻህፍቱ ተሽጠው አልቀዋል። ወይም ዋጋቸው ተለውጧል። ባለፈው አመትም፣ በሚቀጥለው አመትም፣ ተመሳሳይ ‘ችግር’ ይፈጠራል። ዋጋ ከተጠየቀ በኋላ፣ ግዢ እስኪፈፀም ድረስ፣ የቢሮክራሲው አሰራር ረዥም ጊዜ ይወስዳል ብለዋል የቤተመጻህፍቱ ሃላፊ።

በፅንሰ ሃሳብ የተራቀቀ፣ በተግባርም ከሁሉም በልጦ የመጠቀ የሙያው ተቋም ይሆናል የተባለው ማዕከል… መጽሃፍ ብርቅ ሲሆንበት አስቡት።

መፅሃፍ መግዛት፣ እጅግ ከባድና ውስብስብ ስራ ሆኖባቸው ቢቸገሩም፤… እዚያው፣ በአስተማሪዎች የተዘጋጁ የ‘መማሪያ’ ፅሁፎች፣ ተጠርዘው ለተማሪዎች እንደቀረቡ የተቋሙ ሃላፊዎች ገልፀዋል። ድሮ ድሮ፣ ‘ሃንድ አውት’ ይባል እንደነበረው ማለት ነው። ግን፣ እሱም እንደልብ አይገኝም። ለሁሉም ተማሪ አይዳረስም።

ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ‘ሃንድ አውት’፣ በ30 ኮፒ ተዘጋጅቶ፣ ቤተመጻህፍት ውስጥ እንዲቀመጥ አድርገናል ብለዋል የስልጠና ማዕከሉ ሃላፊዎች። በተግባር ሲታይ፣ በ30 ኮፒ የተዘጋጀ ‘ሃንድ አውት’ የለም። አስር ኮፒ ብቻ ነው የተዘጋጀው። ለአንድ ሺ ተማሪ፣ አስር ኮፒ? በዚያ ላይ፣ መቶ ለማይሞሉ ተማሪዎች የተዘጋጀ ቤተመጻህፍት፣ ይሄን ሁሉ ተማሪ እንዴት ማስተናገድ ይችላል? ያው፣ ከቤተመፃህፍት፣ በተውሶ መውሰድም አይቻልም።

ለነገሩ፣ በኮምፒዩተርና በኢንተርኔት ዘመን፣ ይሄ ሁሉ ጭንቀት አያስፈልግም ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። በእርግጥም፣ ላወቀበት፣ ብዙ ‘ዲጂታል’ መፃህፍት እንደልብ ማግኘትና ማቅረብ ይቻላል።

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አቅሙን በመገንባትና የስልጠና ብቃቱን በማሻሻል፤… በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ተመራጭ ማዕከል እንዲሆን የተቋቋመ ድርጅት ምን ይሳነዋል? የተራቀቀ የኮምፒዩተሮችና የኢንተርኔት ኔትዎርክ ይኖረዋል ብላችሁ ከጠበቃችሁ ተሳስታችኋል። አንዲት ተራ የኢንተርኔት መስመር እንኳ አላስገቡም። ኮምፒዩተርም የለም። የሆቴል ብቻ ሳይሆን የቱሪዝም ስልጠና መሆኑን አትርሱ። መንገደኞችን ለማስተናገድ፣ ከአውሮፕላን ቲኬት ጀምሮ፣ እስከ አልጋ ‘ሪዘርቬሽን’ ድረስ፣ በዘመኑ ቴክኖሎጂ እንዴት እንደሚከናወን ስልጠና እሰጣለሁ ይላል።

ግን፣ ኮምፒዩተር የለም። ተፈልጎም ይሁን ተገዝቶ ቢመጣ ደግሞ፣ አስፈላጊ ሶፍትዌር አይኖረውም። ኮምፒዩተሮቹ አገልግሎት ላይ አልዋሉም። ለበላይ ሃላፊዎች ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አላገኘም ብለዋል፣ የስልጠናው ሃላፊዎች።
የበላይ ሃላፊስ ምን ይላሉ? ‘ሶፍት ዌር’ ለመግዛት፣ ጥረት እየተደረገ ነው በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። በመንግስት ቤት ውስጥ፣ እያንዳንዷ ነገር፣ ከባድ ስራ ናት።

ይህንን እንርሳው። አርባ ዓመት የሞላው፣ ‘አንጋፋ’ የመንግስት ተቋም፣ እንዲህ ወደ ኋላ መቅረቱ፣ ይገርማል? አይገርምም። የተለመደ ነው። ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚራመድ የመንግስት ተቋም፣ ስንት አይታችኋል?
ምናልባት በተማሪዎች ቁጥር፣ ትንሽ ተራምዶ ይሆናል። 100 ተማሪዎችን ያስተናግዳል ተብሎ የተመሰረተው ተቋም፣ ዛሬ አንድ ሺ ተማሪዎችን ያስተናግዳል። የአርባ አመት እድገት! ግን ይህችም እድገት፣ ውስጧ ሲታይ፣ ባዶ ነው።(በፌደራል ዋና ኦዲተር የተረጋገጡ ጥቂት መረጃዎችን እንመልከት)

መቼም፣ የሆቴል ሙያ ስልጠና፣ በአብዛኛው የተግባር ስልጠና መሆን ስላለበት፣ በተለይ በተለይ፣ የንፅህና መሳሪያዎችን ጨምሮ በምግብ ማብሰያና ማዘጋጃ መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች፣ መደራጀት የግድ ነው። ከ40 ዓመት በፊት፣ እንደዚያ ነበር። አሁንም፣ እነዚያው መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ናቸው ያሉት።

ለመቶ ተማሪ የተዘጋጁ መሳሪያዎችን ይዞ፣ አንድ ሺ ተማሪዎችን ማሰልጠን እንዴት ይቻላል? የባሰም አለ። ግማሾቹ መሳሪያዎች፣ አርጅተው አይሰሩም። ውሃ ማሞቂያው ደንዝዟል፤ ምድጃው ተበላሽቷል፤ እቃ ማጠቢያው ተሸነቋቁሯል… እያለ ይዘረዝራል ሪፖርቱ። የእቃ ማጠቢያ ብቻ ሳይሆን፣ ለተማሪዎቹም መታጠቢያ ቦታ የለም።
በእርግጥ፣ የትምህርት ክፍል ሃላፊው፣ ሌላ ቅሬታ አላቸው። የማሰልጠኛ ተቋሙ፣ ለስልጠና ጉዳዮች ሳይሆን፣ ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች ነው ትኩረት የሚሰጠው ብለዋል። ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች? ስልጠናን ከማቀላጠፍ ውጭ፣ ሌላ ‘አስተዳደራዊ ስራ’! እና፣ የተግባር መማሪያ ቁሳቁሶችን ለማሟላት፣ ትኩረት አይሰጥም።

የበላይ ሃላፊው ለዚህ ምላሽ አላቸው። ተማሪዎቹ፣ ተግባራዊ ስልጠና የሚያገኙት፣ ወደ ተለያዩ ሆቴሎች በመሄድ ነው ብለዋል ሃላፊው። ‘ልምምድ’ ለማለት ፈልገው ይሆናል። መሰረታዊ የተግባር ስልጠና ካገኙ በኋላ ነው፣ ለልምምድ ወደ ተለያዩ ሆቴሎች መመደብ ያለባቸው። አለበለዚያማ፣ የስልጠና ተቋሙ፣ ከ‘ስልጠና’ ሙያ ለቅቆ እንደወጣ ይቆጠራል። እውነትም፣ ለ‘ስልጠና’ ትኩረት አልተሰጠም ያስብላል። ከዚያም አልፎ፣ ዋነኛ ስራው፣ ‘ስልጠና መስጠት’ እንደሆነ የዘነጋው ይመስላል። ‘የስልጠና ማዕከል’ የሚል መጠሪያ ስም እንዳለው ማስታወስ አለባቸው።

ከዚሁ ጎን ለጎን፣ በሆቴልና በቱሪዝም ሙያ፣ የአገሪቱ ዋነኛ የጥናትና የምርምር ማዕከል ይሆናል ተብሎ ነው በአዋጅ የተቋቋመው። እስካሁን ግን፣ የጥናትና የምርምር ምልክት አልነካካውም። ኢንተርኔት፣ ኮምፒዩተር፣ ጥናትና ምርምር… እያልን ስንዘረዝር፣ ትንንሹን ነገር ረሳነው። በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ብር በጀት የሚመደብለት ይሄው የስልጠና ማዕከሉ፣ 10 የመማሪያ ክፍሎች አሉት። 8ቱ፣ ከቆርቆሮ ተለጣጥፈው የተሰሩ ክፍሎች ናቸው – የድሮው ገነት ሆቴል ውስጥ።

ግን ችግር የለም። ተማሪዎች፣ ለስድስት ወር ቢቸገሩ ነው። የቆርቆሮ ክፍሎች ጊዜያዊ ናቸው። … ማለቴ፣ እንደዚያ ተብሎ የተሰሩ ናቸው። አንደኛው የገነት ሆቴል ግቢ ውስጥ፣ በጥራትና በብቃት ለሌሎች ሁሉ አርአያ የሚሆን ‘ሞዴል ሆቴል’ ይገነባል። በሌላኛው ግቢ ደግሞ፣ የመኝታ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ክፍሎችን፣ በማሻሻልና በማስተካከል ለስልጠና ክፍሎች እንዲሆኑ ይደረጋል።… ተባለ ብላችሁ ጨምሩበት።

የ‘ሞዴል ሆቴል’ ዲዛይን እንዲያዘጋጅ፣ ሥራው ለአንድ የስነህንፃ ድርጅት ተሰጥቷል። ግን፤ መጨረሻው አላማረም። ገንዘብ በከንቱ ባከነ። ሆቴሉ አልተገነባም። ለአራት አመታት ሲጓተት ቆይቶ፣ በዚያው ጨርሶ ተረሳ። ይህ የሆነው በ1988 ዓ.ም ነው። ከሃያ ዓመት በፊት። የማዕከሉ የበላይ ባለስልጣን ግን፣ ካሁን ቀደም የተጀመረ የሆቴል ፕሮጀክትና ዲዛይን አናውቅም ብለዋል። የሆቴል ግንባታ ፕሮጀክቱን የምንጀምረው፣ በ2008 ዓ.ም ዲዛይን በማሰራት ነው ብለዋል – የበላይ ሃላፊው። ከሃያ ዓመት በኋላ፣ ‘አዲስ ፕሮጀክት’ ሆኖ ተወለደ ማለት ነው። አስደናቂ ታሪክ!
ነባር ፕሮጀክታችን፤ የገነት ሆቴል የመኝታ ክፍሎችን ወደ ማሰልጠኛ ክፍል የሚቀይር ፕሮጀክት ነው ሲሉም የበላይ ሃላፊው ተናግረዋል። ይሄኛው ‘ነባር ፕሮጀክት’ም፣ የድንቅ ታሪክ ባለቤት ነው። በ1998 ዓ.ም የዲዛይን ጨረታ በማውጣት ይጀምራል ታሪኩ።

ዲዛይኑ፣ አዲስ ህንፃ ለመገንባት አይደለም። የእድሳትና የጥገና ዲዛይን ልትሉት ትችላላችሁ። ጨረታውን ያሸነፈ ድርጅት፣ ዲዛይን አዘጋጅቶ አቅርቧል። ነገር ግን፣ ትንሽ ቆይቶ ሲታይ፣ ዲዛይኑ ዋጋ የለውም ተባለ። ደግነቱ፣ ብዙ ገንዘብ አልባከነም። 86ሺ ብር ብቻ የተከፈለበት ዲዛይን ነው።

እንግዲህ፤ የእድሳት ስራውን ለመቆጣጠር የመጣ ሌላ ሁለተኛ ድርጅት ነው፣ ‘ዲዛይኑ የተሟላ አይደለም’ ብሎ ውድቅ ያደረገው። በዚያው አልተሰናበተም። እስቲ አንተ ደግሞ ሌላ የእድሳት ዲዛይን ስራልን ተብሎ፣ እዚያው በዚያው ስራ አገኘ። በ238ሺ ብር፣ ዲዛይን ሰርቶ ካቀረበ በኋላ ግን ተሰናበተ።

እድሳትና ጥገናው፣ በአንድ የስራ ተቋራጭ ድርጅት ተጀመረ (ሌላ የእድሳት ተቆጣጣሪ ድርጅትም ተጨምሮበት)።
ወደ አስር ሚሊዮን ብር ገደማ እንደሚፈጅ በተገመተው በዚሁ ፕሮጀክት፤በሮችንና መስኮቶችን፣ ኮርኒስና ወለሎችን፣ ግድግዳና መተላለፊያዎችን ለማስተካከል፣ በቅድሚያ… ነባሮቹን መንቀል፣ መገንጠል፣ መሸርከት፣ መናድ… ያስፈልግ የለ? መስኮትና በር፣ የመፀዳጃ ቤት ቁሳቁስና ኮርኒስ ወዘተ… ተነቃቀለ።

በዚህ መሃል ነው፤ ‘ዲዛይኑ ችግር እንዳለበት’ በእድሳት ተቆጣጣሪው ድርጅት የተረጋገጠው። ታሪክ እንደገና ተደገመ። ‘አንተው ራስህ፣ የተስተካከለ ዲዛይን ስራልን’ ተባለ – በ268ሺ ብር።

ዲዛይን የሰራ ድርጅት፣ ክፍያውን ተቀብሎ ከሄደ በኋላ፣ “ዲዛይኑ ዋጋ እንደሌለው ተረጋገጠ” እየተባለ እስከ መቼ ይቀጥላል? የእድሳት ዲዛይን ወጪው፣ ወደ 600ሺ ብር ተጠግቷል። ይሄ አዙሪት፣ ማብቂያ ይኖረው ይሆን?

በአዲሱ ዲዛይን መሰረት፣ እድሳቱና ጥገናው፣ 10 ሚሊዮን ብር አይበቃውም። 23 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል ተባለ። በጀት ደግሞ የለም። እድሳቱና ጥገናው፣ በዚሁ ተቋረጠ – በ2003 ዓ.ም። ግን፣ በርና መስኮት፣ ኮርኒስና ምናምን ተነቃቅሎ ተገነጣጥሎ፣ አካባቢው በአውሮፕላን ሲደበደብ የከረመ መስሏል። ይሄ የሆነው በነፃ አይደለም። ለስራ ተቋራጩ፣ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ተከፍሎታል።

በአጭሩ፣ የመኝታ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ገነት ሆቴል፣ በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተቦዳድሶ፣ በዝናብ እየተበላሸ ሙጃ እየወረረው፣ የጥንት ዘመን ፍርስራሽ መስሎ አረፈው። ይሄውና አምስት አመቱ!

(ይሄ ነው፣ የቱሪዝምና የሆቴል ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል፡… የቱሪዝም ኢንደስትሪን ዕድገት ለማፋጠን፣… የሰለጠነ የሰው ኃይል በጥራትና በብቃት የሚያፈራ! በሆቴልና በቱሪዝም ሙያ፣ ከሁሉም የላቀ “የልዕቀት” ማዕከል፤ ሞዴል ሆቴል ገንብቶ፣ በአርአያነት የአገልግሎት ጥራትን የሚያሳድግ!)

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑