በታጋዮች ክንድ የደቀቀው ፍርድ

Bereket-Simon

በታጋዮች ክንድ የደቀቀው ፍርድ – ታሪኩ አባዳማ

ታጋዩ አቶ በረከት ስምኦን ሲኖሩበት ከነበረ ንብረትነቱ የአቶ መሀሪ ተወልደ ብርሀን የሆነ የተንጣለለ ቪላ ለቀው እንዲወጡ እና ለባለንብረቱ እንዲያስረክቡ ፍርድ ቤት ቢወስንም ለሳቸው የሚመጥን ሌላ ቤት ባለመገኘቱ ውሳኔው ተፈፃሚ ሊሆን አልቻለም። ቤቱ ለባለንብረቱ እንዲመለስ ላለፉት ስምንት አመታት በተከታታይ በህግ ቢወሰንም ከህግ በላይ የሆነ ሰው ስለሚኖርበት ተፈፃሚ አልሆነም –

ይህ ባለፈው ሳምንት ኖቬምበር 29 ቀን ‘ሪፖርተር’ ጋዜጣ ላይ የተነገረ ዜና ነው። ድህነታቸውን ተረት ያደረጉት አቶ በረከት የሚመጥናቸው ቤት ከአዲስ አበባ ጠፋ። ጉዳዩን ዜና ያደረገው ይኼ ይመስለኛል። እንጂ ታጋይ በረከት አዲስ አበባን ከሩቅ በዝና እንጂ በአይናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ያዩዋት ህወሃት መንግስት ሲሆን ነበርኮ። ቁምጣ ለብሰው አዲስ አበባ የገቡት አቶ በረከት ዛሬ ለሳቸው የሚመጥን ቤት ሊገኝ አልቻለም። መፍትሔው ለሳቸው የሚመጥን ቤት የሚገነባ መሀንዲስ እስከሚገኝ አንድ ሌላ ዜጋ ካፈራው አንጡራ ንብረቱ ተፈናቅሎ እንዲቆይ ማድረግ መሆኑን ዜናው አክሎ ነግሮናል። የንብረቱ ባለቤት አቶ መሀሪ በአሁኑ ጊዜ የሚኖሩት ቤት ተከራይተው ወይም ከዘመዶቻቸው ጋር ተዳብለው በውል የታወቀ ነገር የለም።

ሪፖርተር እንደ ዘገበው “… የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ሲሳይ ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ ፣ በቤቱ ውስጥ የሚኖሩትን ባለስልጣን የሚመጥን ቤት ስላልተገኘ ንብረቱን ለባለቤቱ አናስረክብም…” ሲል አቶ በረከት ድህነትን ተረት ለማድረግ ምን ያህል ገፍተው እንደሚሄዱ መሰክሯል። ህግ ፣ ፍርድ ቤት የሚሉት ትዕዛዝ በነ በረከት ፊት ዋጋ የለውም።

አዲስ አበባ ሆይ የአቶ በረከት ችግር እንዴት አይገባሽም? በቁምጣ ምትክ ሱፍ አልብሰሻቸው ፣ በቂጣ ምትክ ፍትፍት አጉርሰሻቸው ፣ ከባዶ እግር ወደ ተንደላቀቀ ኦቶሞቢል አሸጋግረሻቸው ፣ በስልጣን ላይ ስልጣን አጎናፅፈሻቸው ፣ ከትቢያ አንስተሽ ፅጌረዳ ፍራሽ ላይ አስተኝተሻቸው ፣ ከባዶ ሜዳ ተንደርደረው እንዳልመጡ ሰፋፊ ቢሮ ውስጥ እንዲኮፈሱ አድርገሻቸው… – ምነው ዛሬ የሚመጥናቸው ቤት አጣሽላቸው?

ቆየት ካሉ ተመሳሳይ ዜናዎች ብናክልበት – የመለስ ዜናዊ ሚስት ባሏ መሞቱ ዘግይቶ ከታወጀ ጀምሮ የርዕሰ ብሔር መቀመጫ ከሆነው ቤተ-መንግሰት አልወጣም ብላ አስቸገረች። ምክንያቱ የሚመጥናት ሌላ ቤት አዲስ አበባ ውስጥ ሊገኝ አለመቻሉ። ዘግይቶ ፣ አለም ተሳልቆባት ሲያበቃ የሚመጥናት ቤት በስንት አበሳ ተገኘ አሉን። ወደተገኘላት ቤት ለማዘዋወር ከሶስት ወር በላይ ፈጅቷል።

ከዚያ ትንሽ ቆየት ብሎ ደግሞ አዛውንቱ መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እንደ ድንች ተወዝተው ከነበረበት ቤተ መንግስት በጋሪ ተገፍተው ሲወጡ የሚመጥናቸው ቤት ማግኘት አስቸጋሪ ሆነ። መቶ አለቃ ግርማ ለወያኔ አገዛዝ ላበረከቱት ውለታ በብርቱ ፍለጋ አንድ በአመት ከአምስት ሚሊየን ብር በላይ ኪራይ የሚጠይቅ የተንጣለለ ቤት ተገኘላቸው። በተንጣለለው ቪላ ግማሹን ቀን በንቅልፍ ቀሪውን ደግሞ በወግ ጥረቃ ይምነሸነሹበታል።

ግርማ የጫካ ታጋይ አልነበሩም – ለጫካ ታጋዮች ስልጣን መቆናጠጥ የሚጠበቅባቸውን ግዳጅ ግን እንደ ማንኛውም ሆዳም ባንዳ በሚያመረቃ ደረጃ ተወጥተዋል። እናም የሰው ጎመን human vegetable የሆኑት አዛውንት ቀሪ ዘመናቸውን በጋሪ ተገፍቶ ለመውጣት ለመግባት ፣ በሰው እጅ ለመብላት ለመጠጣት ፣ በሞግዚት እጅ ቀበቶ ለመፍታት እና ለመታጠቅ እንዲያው ባጭሩ በአሽከርና ገረድ እጅ የሚንዠባረሩበት ቪላ ተገኝቶላቸዋል።
አዛውንቱ የድሀውን ህዝብ ሀብት አለርህራሄ ለመቦደስ ከሚራኮቱት ወያኔዎች ተርታ ለመሰለፍ አላመነቱም። ዕድሜ ከሰጣቸው አምስት ሚሊየን ብር ከአስራ አምስት ሚሊየን ረሀብተኛ ዜጎች የእለት ጉርስ የተነጠቀ በመሆኑ ሂሳቡን የሚያወራርዱበትን ቀን ያያሉ ብዬ አምናለሁ።

ወደ ታጋይ በረከት ልመልሳችሁ – የወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ቁጥጥር ስር የቆየ የአቶ መሀሪ ተወልደ ብርሀን ንብረት ቪላ ለባለቤቱ እንዲመለስ ፍርድ ቤት የወሰነው ከአስራ ሰባት ዓመታት በፊት የያኔው የወያኔ ጀነራል ፃድቃን ሲኖሩበት በነበረ ጊዜ ጭምር ነው። ጀነራሉ የሚመጥናቸውን ቪላ ለራሳቸው ገንብተው የአቶ መሀሪን ንብረት ደግሞ ለአቶ በረከት አስረክበው የወጡት ከስምንት ዓመታት በፊት ነው። የአቶ መሀሪን ንብረት ጀነራሉ ታጋይ ፃድቃን ለታጋይ በረከት ጓዳዊ ቅብብሎሽ ፈፅመውበታል።

ታጋይ በረከት ደግሞ የህግ በላይነት እና ዲሞክረሲ እንዲሰፍን ላደረጉት አስተዋፅኦ ከህግ በላይ ሆነው የትግሉን ፍሬ እንዲያጣጥሙ የተፈቀደላቸው ባለስልጣን መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ድህነትን ከራሳቸው በማራገፍ ተረት ማድረግ ችለዋል – ተረቱ ግን መራራ ፣ ጎምዛዛ ሆነሳ!

መሀንዲሱ ለበረከት ስምኦን የሚመጥን ቤት ሲነድፍ በቂ መመሪያ መቀበል ሊኖርበት ነው። መሀንዲሱ ለራሱ ደህንነት ሲል ጥያቄ ማንሳቱ አይቀርም – ታጋይ በረከት ስምኦን የሚመጥናቸው ቤት ምን አይነት ይሆን?
እነዚህ ሰዎች የሚመጥነን ቤት አልተገኘም ሲሉ ለመሆኑ መመጠኛው በምን መስፈርት እየተለካ ነው ብለን ብንጠይቅ ጥፋት አይመስለኝም። ጉዳዩ ተደጋገመ ፤ አዲስ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በወያኔ መዳፍ ስር ወደፊት ስንቱ የፍየል እረኛ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጥነኝ ቤት ፈልጉ ሊል እንደሚችል ሳስበው ይከነክነኛል። በረከት አደረገ ተብሎ የሰማነው ዜና በያንዳንዷ ቀበሌ እና ክልል የወያኔ ሹማምንት የሚፈፀም ጉዳይ ነው።

የምናወራው ስለ አንድ በረከት ስምኦን አይደለም – ህዝቡን መቀመቅ ወርውሮ መሪዎቹን ከድህነት ተራ ነፃ ላወጣው የወያኔ አገዛዝ እና የፖለቲካ ስርዓት እንጂ። ባዶ እጅ ከሰው ቤት ገብቶ አልወጣም የሚል ነፃ አውጪ እየገዛን መሆኑን ስንቱ ዜጋ እንደተገነዘበው ባላውቅም ሪፖርተር ጋዜጣ ግን በይፋ እየመሰከረ ነው። የወያኔ ሹማምንት ድህነትን ተረት ማድረጋቸው እንዲህ ይገለፃል።

ተረቱ ሬት ሬት አለሳ!
ደግሞም ጉዳዩ በተመጣጣኝ መኖሪያ ቤት ጥያቄ የሚገታ አልመሰለኝም… ታጋዮቹ የሚመጥናቸው ሆስፒታል ፣ የሚመጥናቸው ሆቴል ፣ የሚመጥናቸው መኪና ፣ ለልጆቻቸው የሚመጥን ትምህርት ቤት … የሚመጥናቸው አሽከር ፣ ገረድ ፣ የሚመጥናቸው ውስኪ… እንዲህ እያለ ታጋይ ነን ለሚሉ ወሮበሎች አገሪቱ ስብእናቸውን የሚመጥን ነገር ፍለጋ በመባዘን መቆየቷን እየታዘብን ነው።

በረከት ስምኦን አንድያ መፅሀፉን በሸራተን ሆቴል ባስመረቀበት ዕለት አላሙዲን የተባለው ቱጃር በክብር እንግድነት ተገኝቶ ‘በረከት ሲታመም ‘ጆሮውን አንጠልጥዬ’ ደቡብ አፍሪካ ወሰድኩት’ ብሎ ባላስልጣናቱ ምን ያህል በመዳፉ ውስጥ እንደሚንፈራፈሩ ተናገረ። ጨምሮ መፅሀፉን ለማሳተም ወጭውን የሸፈነልኝ ‘ደጉ ሩህሩሁ ሼህ’ ነው ሲል በረከት ምርቃቱን አሰማ። ህወሃት/ኢህአዴግ ዝናብ አይፈራም – አደባባይ ቆሞ ከቱጃሮች ይህ ተደርጎልኛል ብሎ በልበ-ሙሉነት ይመሰክራል።

እንግዲህ ልብ በሉ አንድ የመንግስት ሚኒስትር እና ቁልፍ የፖለቲካ ወሳኝነት ቦታ የያዘ ባለስልጣን አገሪቱ ውስጥ ብዙ የኢንቨስትመንት አለኝታ እና ጥቅም ከሚያገኝ ሀብታም እጅ ‘ችሮታ’ መቀበሉን በይፋ ሲያረጋግጥ። በረከት ከአላሙዲ ይህን ያህል ወሮታ መቀበሉ ማን ስለሆነ ነው? አላሙዲን በምላሹ ምን እንዲደረግለት ይጠብቃል? ሩቅ ሳንሄድ ስለ ሼሁ ዘረፋ ብዙ ማለት ጥቻላል። ከአዲስ አበባ ጀምሮ እስከ ጋምቤላ ያሻውን መሬት አጥሮ ቢከርም ፣ ወርቅ አላንዳች ቁጥጥር እየጫነ ቢያወጣ ምንም ይሁን ምን ቢፈፅም ጠያቂ የሌለበት ፣ የህግም ሆነ ሞራል ገደብ የማይነካው ልቅ ዋልጌ ቱጃር መሆኑን እንዲህ አረጋግጧል።

አላሙዲን ከነበረከት ጋር በጓዳ የሚፈፅመው መሞዳመድ አገሪቱ ምን ያህል ህግ የተረገጠባት መሆኗን ጉልህ ማሳያ ነው – ይህ የሚፈፀመው ህግ የበላይ በሆነበት አገር ውስጥ ቢሆን ኖሮ በከባድ ወንጀል የሚያስጠይቅ እና ወህኒ የሚያስገባ ድርጊት ነበር። ህግ በነፃ አውጪ ታጋዮች ኮቴ ስር ተጥላለች።

ሪፖርተር ጋዜጣ አገራችን ውስጥ ሞልቶ ከፈሰሰው የግፍ ገንቦ ቂጥ ስር አበስ እያደረገ ሊያሳየን ይሞክራል። ከፈሰሰው ሳይሆን ከሞላው የግፍ ገንቦ ጠልቆ እየቀዳ ሊያሳየን ቢችል ደግሞ ይበልጥ መልካም ነው። ይህ ዛሬ በረከት ለፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልገዛም አለ የሚለው ዜና ለህዝቡ ዜና አይደለም – አገር የሚያውቀው ፣ ፀሐይ የሞቀው ውነት ነው።
እነ በረከት ስምኦን ‘ነፃ’ ያወጡት ዜጋ የተቀማ ንብረቱን ለማግኘት አልተፈቀደለትም – ህግ ያላስከበረውን ንብረት ፣ ህግ ያልታደገውን መብት ማን ያስከብረው?

ምንጭ: ሳተናው

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑