ኢትዮጵያ በሁለቱም ጫፍ የምትቃጠል ሻማ እንዳትሆን

ኢትዮጵያ በሁለቱም ጫፍ የምትቃጠል ሻማ እንዳትሆን

ያንዲት አገር ዜጎችን በዘር ሸንሽኖ በወርቅ እና በነሀስ መፈረጅ ብሎም ከዚህ ፖሊሲ በመነጨ ኢኮኖሚውን ፣ መገናኛ አውታሩን ፣ መከላከያውን ፣ ቁልፍ የመንግሰት ስልጣን ብሎም አጠቃላይ የፖለቲካ ህይወት ከዚያ ‘ወርቅ’ ብሎ ከሸነገለው ዘር ተመርጦ በተመለመለ ሀይል ሙሉ ቁጥጥር ስር እንዲውል ማረጋገጥ የለየለት የህገወጥ መንግሰት ባህሪ መሆኑን የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ወቅት ላይ ደርሰናል። ወያኔ በተፈጥሮው መንግስታዊ ተጠያቂነት እና ግልፅነት የሌለበት ፣ ህግ አውጭ እና አስፈፃሚ አካላት ተደበላልቀው ዘረኞች ያሻቸውን በፈቃዳቸው የሚፈፅሙበት ፣ የተፃፈ ሰነድ ሳይሆን ግለሰብ ወይም ቡድን ህግ የሆኑበት የፖለቲካ ስርዓት ነው።

ላለፉት ሀያ አራት ዐመታት ህጉም ዳኛውም ወያኔ ነው። የምንታገለው ደግሞ ለህግ የበላይነት ነው። ወያኔ ለከት ባጣ የጎጥ መከታ ሥልጣንን እና ዘረፋን ግቡ ያደረገ ፣ ባንድ ጀምበር ቱጃር የሚቀፈቀፍበት የጠረባ ቡድን መሆኑን ሁሉም ያውቃል። በእጃቸው አንጠልጥለው የሚዞሩት ሞባይል ፣ የሚያሽከረክሩት ውድ መኪና የሚንደላቀቁበት ቪላ በጠረባ ተዘርፎ የተገኘ እንጂ ለዕድገት አመቺ ሁኔታ ፈጥረው በዚያ በተካበተ ጥሪት የተገኘ አለመሆኑን ከሁላችንም በላይ እነሱ ያውቁታል።

ዕድገት ዳይናሚክ ነው – የፈጠራ እና አዳዲስ ግኝቶች ውጤት እንጂ የመሬት ወረራ በሚፈፅሙ ስግብግብ ዘረኞች እውን የሚሆን ክስተት አይደለም። አገር እየነቀዘ አይፋፋም። ወያኔ ዕድገት ያመጣል ብሎ መገመት ደግሞ ከእባብ እንቁላል እርግብ የመጠበቅ ያህል ነው።

ዕድገት ኢንቬስተር ይጠይቃል ፣ ያውም በፖለቲካ ሥርዓት እና በሕግ የበላይነት የሚመካ ልበ ሙሉ ኢንቬስተር። አንድ የፖለቲካ ቡድን ያሻውን ደንብ እና ሥርዓት እየደነገገ እና እየሻረ በሚፈጥረው ውስብስብ መሰናክል ውስጥ ታፍኖ የሚመጣ ዕድገት የለም። ዕድገት በነፃ መተንፈስ ፣ በነፃ መወዳደር ፣ በነፃ መብለጥ ፣ በነፃ ቀድሞ መገኘት ማለት ነው። በነፃ መሪዎቹን የመረጠ ህዝብ እንደ አውሬ ታድኖ በሚፈጅበት አገር ከቶውንም ዕድገት ሊታሰብ አይችልም።
ስር ሰዶ የቆየው እና ‘አገር ‘ለማልማት’ ከአገር ማፈናቀል’ የሚለው የወያኔ የመሬት ፖሊሲ ድሀውን ገበሬ ብቻ ሳይሆን ድሀውን የከተማ መሬት ባለቤት ከአፅመ ርስቱ ሲያፈናቅል መቆየቱ ይታወቃል። አዲስ አበቤዎች ለምዕተ ዓመታት ከኖሩበት ቄየ ዛሬውኑ ፎቅ ካልሰራችሁ ልቀቁ እየተባሉ ለአጥር መስሪያ እንኳ የማይሆን ብር በንቀት እየተወረወረላቸው በመፈናቀል ላይ ናቸው። ድሀ ዜጎች የቆረቆሩት ሰፈር ፣ የኖሩበት ዕድር ፣ አድባሩ አውጋሩ ሁሉ ተደፍጥጦ ከተማዋን ለቀው አንዳችም መሰረተ ልማት ወደሌለበት ኮረብታ እንዲሰፍሩ ተገደዋል። የልጆች ትምህርት ቤት በዚህ የተነሳ ተስተጓጉሏል። ቢታመሙ መታከሚያ ቀርቶ ‘ይማርህ’ ብሎ የሚጠይቅ የቅርብ ወዳጅ እንዲያጡ ተደርጓል። ዜጎች ቀን ከሌት በወያኔ አውሬአዊ ጭካኔ እየተቀጠቀጡ ነው።

ከድሀ ዜጎች የተነጠቀ መሬት ለወያኔ ኢንቨስተሮች በሚሊየን ብር እየተቸበቸበ ሹማምንቱ ባንድ ጀምበር ቢጠሩት የማይሰማ ዲታ ሆነዋል። ይኼ እንግዲህ በህዝብ ላይ የተፈፀመ ፀሐይ የሞቀው በኤግዚቢትነት የሚቆጠር አንዱ ተጨባጭ የወያኔ ወንጀል ነው።

ወያኔ የብሔረሰብ ነፃ አውጪ ነኝ በሚል የዘረጋው ጎጠኛ ፖሊሲ ለስልጣኑ መራዘም አስተዋፅኦ አድርጓል። ከየመንደሩ የተመለመሉ ሆድ አምላኪዎች ዘር እየቆጠሩ በመሿሿም በደል ሲፈፅሙ መቆየታቸው በሰነድ ጭምር የተረጋገጠ ነው። ባልጠግብ ባይነት በራሳቸው ፣ በዘመድ አዝማዳቸው ስም በየሜዳው የኮለኮሉት ፎቅ የዝርፊያ ወንጀላቸውን ቆሞ የሚመሰክር ኤግዚቢት ነው። በልማት ስም የተጨፈጨፉ ታላላቅ ደኖች ፣ ለአበባ ልማት ተብሎ ከገበሬዎች ተቀምቶ ዛሬ ለምነቱ ተሟጦ የአይጥ መፈንጫ የሆነው የእርሻ ማሳ ሁሉ ቋሚ ምስክር ነው።

ዛሬ ገንፍሎ የወጣው ግዙፍ ህዝባዊ አመፅ በኦሮሞ ክልል ህዝብ የተቀጣጠለ ይምሰል እንጂ በሁሉም የአገሪቱ ክልል ሲፈፀም የቆየው ግፍ ውጤት መሆኑን የሚስት አለ ብዬ አልገምትም። ኦሮሞ ደግሞ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አገር ላይ ጉዳት ጥቃት ሲገባ ፣ ዋልታ እና ማገር ሲናጋ በቁጣ ተነስቶ የጠየቀውን መስዋዕትነት ሲከፍል የቆየ ዜጋ ነው። ዛሬ የወያኔ ጎጠኛ ፖሊሲ አሽክላ በዘረጋው ውጥመድ ውስጥ ገብቶ ከሌሎች ዜጎች የተለየ ማስከበር የሚፈልገው ጥቅም የለም።

በመሰረቱ እስከዛሬ በየዘርፉ ሲፈፀም የቆየው አፈና ፣ እስር እና ግድያ ኦሮሞን ፣ አማራን ፣ ጉራጌን ወላይታን ለይቶ የደረሰ አይደለም። ፃፋችሁ ፣ ተናገራችሁ ፣ አሰባቸሁ ፣ ተሰበሰባችሁ እየተባለ ሁሉም ዜጎች በሁሉም ያገሪቱ ክልለ በብረት እየታመሱ ሀያ አራት ዓመታት አሳልፈዋል። ዛሬ ወህኒ የሚማቅቁ የሁሉም ክልል ዜጎች ቁጥራቸው የት እየለሌ ደርሷል። በመሆኑም ጥያቄው የኦሮሞ ገበሬዎች በልማት ስም የመፈናቀላቸው ጉዳይ ተብሎ የሚጠብ አይደለም። ከወያኔ የባርነት ሰንሰለት ሰብሮ ለመውጣት የሚደረግ የነፃነት ጥያቄ ነው።

መረን የለቀቀ ግፍ መሸከም ታከተኝ ብሎ ህዝብ ተነስቷል። ከታሰርኩበት ሰንሰለት ሌላ የማጣው ነገር የለም ብሎ በቁርጠኝነት ተሰልፏል። ለወያኔ ነብሰ ገዳዮች ግምባሬን አላጥፍም ብሎ እየተጋፈጠ ነው። ህዝብን በብረት ሀይል አንበርክኮ ስልጣን ላይ ለዘላለም የቆየ መንግስት እንዳልነበረ ሁሉ የወያኔ ዕጣ ፈንታም ወደ ቆሻሻ የታሪክ ክምችት መወርወር መሆኑ ገሀድ እየታየ ነው።

አልፎ አልፎ እንደምንታዘበው አገሪቱ ውስጥ የሚነሱ የመብት ጥያቄዎችን ሁሉ ወደ አንድ ወይንም ሌላ ብሔረሰብ ወይንም ክልል ብቸኛ ችግር እና ጥያቄ አድርጎ የማስተጋባት ዝንባሌ እየታየ ነው። ይህ ደግሞ በቀጥታ ወያኔ ሲዘረጋው እና ተግቶ ሲተበትበው ወደ ነበር ወጥመድ ውስጥ የሚከት አደጋ ነው። የወያኔ አላማ ቀድሞውኑ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚያስተሳስራቸው ጉዳይ እንዲደበዝዝ ፣ የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በጋራ እንዳይቆሙ ቁሳዊ ፣ ክልላዊ እና ስነልቦናዊ ድንበር በማስመር እርስ በርስ እንዳይተማመኑ ማድረግ ነበር። ዛሬ በየትኛውም ክልል የሚነሳ ህዝባዊ ጥያቄ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነው – እናም ትግሉ የሁሉም ዜጎች ነው።

መከፋፈል የሚበጀው ለማን እንደሆነ ማን ለማን ይመክራል?

ሁሉም ብሔረሰቦች ባህላቸውን ፣ ቋንቋቸውን ማበልፀግ እንዲችሉ በህግ ዋስትና ማረጋገጥ አንድ ነገር ነው – ሁሉም ብሔረሰቦች ነፃ ወጥታቹሀል በሚል መፈክር ጥላ ስር እርስ በርስ እንደ ጠላት እንዲተያዩ ማድረግ ግን እነሆ እንደምናየው አገር የሚያሳጣ ከይሲዎች የሚቀይሱት የጥፋት ጎዳና ነው። ወያኔ የተመኘልን በብሔረሰባችን ነፃ የመውጣት ጎዳና አንድም ለሁሉም ዜጎቿ አለኝታ የሆነች አገር ማሳጣት ሁለትም ተከፋፍለህ ስትናቆር አሁን የምታየውን አይነት አይና ያወጣ የጠራራ ፀሐይ ዘረፋ ማቀላጠፍ ነው። የወያኔ ተልዕኮ መምከን የሚችለው ደግሞ በአንድነት ቆመህ አገሬን ስትል ነው

አገርህን አድን ስንል ተልዕኮው ግልፅ ትርጓሜ ያዘለ ነው። አገር ማዳን ፣ አገርን መታደግ ማለት ከያንዳንዱ ዜጋ የትናንት ዛሬ እና ነገ ማንነት እና ህልውና ጋር የተሳሰረ መሆኑን ማን ይክዳል?

እጅግ ሁዋላ ቀር በሆነችው አገራችን የፖለቲካ ሀይሎች ህብረት ጥያቄ ፋይዳው ግዙፍ መሆኑን የሚያረጋግጥ ጥያቄ መሆኑም እሙን ነው። በጠበቀ መርህ እና እምነት ጥላ ሥር ተሰባስቦ ፣ ለደንብ እና የጋራ ውሳኔዎች ተገዢ ሆኖ አገርን ከድርጅት በላይ አስቀምጦ ለመራመድ ሙሉ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ግዙፍ ተልዕኮ ተሸክሞ በህብረት ሊንቀሳቀስ እና ከግብ ሊደርስ የሚበቃ ሀይል ሊመጣ አይችልም። ሀያ አራት ዓመታት ሙሉ ‘ህብረት ሲሉ ህብረት ስንል’ እየተባለ ሙት ፣ በድን ሀተታ ስናረቅ ብቻውን የቆመ ጎጠኛ ቡድን ደንደሱን አሳብጦ በንቀት ቁልቁል እንዲያየን አድርገናል። ተነጣጥለን በመቆየታችን ወያኔ እየነጣጠለ እያነጣጠረ ህዝባችንን እንዲፈጅ ተደፋፍሯል።

አገራችን የተጋፈጠችውን ጠላት ለመቋቋም የሚያበቃ መጣኝ ህብረት ለማምጣት ‘ከድርጅት በላይ አገር’ ለሚለው አቋም መቆም አማራጭ የለውም። ይህ ካልተሟላ ደግሞ ትግሉ እንደተውሸለሸለ እንደ ትናንቱ ነገም ወያኔ መፈንጨቱን ይቀጥላል።

ህብረት እንደ መሸጋገሪያ ወይስ እንደ ግብ የሚለው ጉዳይ ከህብረት ጥያቄ አንገብጋቢነት እና አማራጭ የለሽነት አኳያ ሚዛን ላይ ተቀምጦ በተገቢው ረገድ መልስ ሊያገኝ ይገባል። ባንድ በኩል ፅኑ ህብረት እስከሌለ ድረስ ህዝቡን ለድል አበቃለሁ ማለት ዘበት ነው እየተባለ ይዘመራል ፤ በሌላ በኩል ግን ለህዝብ ድል ቆመናል የሚሉ ሳይቀሩ በሚፈጥሩት ህብረት ውስጥ ተገቢ የህብረት ማጎልመሻ ተግባር ሲፈፅሙ አልታዩም። አልፎ ተርፎ ህብረት የፈጠሩ ድርጅቶችን ማሽሟጠጥ እና መሸርደድ እንደ ፖለቲካ አላማ ተደርጎ ገና ሲፈጠር አናት አናቱን እየፈለጡ ለመግደል ተግተው የሚሠሩ ‘ህብረት ሰባኪዎች’ እየበረከቱ ነው።

እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚለው የወያኔ እንሰሳዊ ፖሊሲ አገራችንን ወደ ጥፋት አዘቅት ከመክተቱ በፊት ሁሉም ዜጎች ትከሻ ለትከሻ ተያይዘው ሊጋፈጡት ይገባል። ወያኔ በባርነት ቀንበር አግቶ መግዛቱን ለመቀጠል ሲከፋፍለን – እኛም አገራችንን ከምንም ነገር በላይ አስቀድመን ለህግ የበላይነት መረጋገት መቆም ከተሳነን እነሱም እኛም ለጥፋቱ እኩል ተጠያቂዎች ነን። ከፈጠሩት የጎጥ ክፍፍል ሰብረን ሳንወጣ የአገራችንን መፃኢ ዕድል መተንበይ አንችልም ፤ የያንዳንዳችን ሙሉ ነፃነት የሚረጋገጠው እያንዳንዳችንን እኩል የሚያስተናግደን ህግ ሲገዛን ብቻ ነው።

ስለሆነም ካንድ ጫፍ ወያኔ የለኮሰው የጥፋት ዘመቻ ይህ ነው የማይባል አደጋ የሚያስከትል አገሪቱ ልታገግም ከማትበቃበት አዘቅት ውስጥ ለመጨመር የታለመ መሆኑን አበክረን ልንገነዘብ ይገባል። ይህን የጥፋት ቋያ በተባበረ ሀይል ማዳፈን ያስፈልጋል። የወያኔ የጥፋት ቋያ የሚዳፈነው የሁሉም ዜጋ ሙሉ መብት በህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑን መቀበል አማራጭ የለውም።

ወያኔ እንደሚሰብከው የብሔረሰብ ነፃነት የሚባል ነገር የለም። ያለው የኢትዮጵያ ነፃነት ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ነፃ የምትሆነው ደግሞ ማንኛውም ዜጋ በህግ ፊት እኩል መሆኑ ዋስትና ሲያገኝ ብቻ ነው። አንደኛ ደረጃ ዜጋ ፣ ወርቅ ዜጋ ፣ ነሀስ ዜጋ እየተባለ በብሔረሰብ ምሽግ ሌላውን ህዝብ ለማዋረድ እና ለመቀማት መሰለፍ የወያኔ ተግባር ብቻ መሆኑን ማስመስከር ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ ሳንችል ቀርቶ አገራችን ለወያኔ ጥፋት ተልዕኮ ሰለባ ከሆነች እነሱ ብቻ ሳይሆኑ እኛም ተጠያቂ እንሆናለን።

ኢትዮጵያችን በሁለት ጫፍ የምትቃጠል ሻማ እንዳትሆን እጅግ ብርቱ የሆነ ታሪካዊ ተልዕኮ ከያንዳንዳችን ትከሻ ላይ ወድቋል። በሌላ የብሔረሰብ ነፃነት አዙሪት ውስጥ ለመግባት የሚፈቅድ ሁኔታም ቦታም የለም። ዛሬ አገራችን ከኛ የምትሻው የብሔረሰብ ነፃነት በሚል ወያኔአዊ መፈክር መጓዝ ሳይሆን የህግ በላይነት የሚረጋገጥባት – ሁሉም ዜጎች በህግ ፊት እኩል መሆናቸው ዋስትና ያለው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲፈጠር መታገል ነው። ለዚህ ነው በየትኛውም ክልል የሚነሳ እምቢተኛነት በሁሉም ክልል ዜጎች ሙሉ ድጋፍ እና ተሳትፎ መራመድ አለበት የምንለው።

ኢትዮጵያ በህግ የበላይነት ኮርተው ለመኖር በሚሹ ህዝቦቿ ትግል ነፃ ትወጣለች።

ኢካድ የተገኘ

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.