እግዚአብሔር ልጅ አለውን?

እግዚአብሔር ልጅ አለውን?

  • እግዚአብሔር ልጅ አለውን?
  • እግዚአብሔር ልጅ የሰጠችው ሚስት ነበረውን?
  • ይህ ማለት እግዚአብሔር ከአንድ በላይ ነው ማለት ይሆን?

የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዐል (ገና) እያከበርን ባለንበት ወቅት በአንዳንድ ወንድሞቻችን ልቡና ውስጥ ሞልቶ ተርፎ ለሰማነውን ተመላላሽ ጥያቂዎች መልስ ማዘጋጅት ወደድን። በተመሳሳይ ርዕስ ጽሁፋቸው ተሰናድቶ ያገኘነውን  አባ ታድሮስ ማላቲ አዘጋጅተው  ቅ/ሚናስ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ያቀረበችውን ቤተ ፍቅር ዘአቢሲኒያ እንደተረጎመው እንዲህ ቀርቧል። እግዚአብሔር ልባችንን ይዳብሰው ይባርከን። በ PDF ለማንበብ ይህን ይጫኑ

NA1

እግዚአብሔርን በቁስ አካላዊ እይታ መመልከት አግባብ አይሆንም ይላሉ አባ ታድሮስ ስለዚህ ርዕስ ሲጽፉ። እርሱ ሰው አይደለም ወይም ሌላ ዓይነት አንዳች ፍጡር አይደለም። ‘አባትና ልጅ’ የሚለው አገላለጽ እግዚአብሔር ተጋብቶ ሌላ አማልክ ወለደ ማለትም አይደለም። እግዚአብሔር ጾታ የለውም።

አባት ልጁን ወለደ ስንል ፀሐይ ጨረሯን እንደወለደችው ማለት ነው። ወይም እንደሰው ልጅ ነፍስ መወለድ ያለ እና ነጸብራቅን ከብርሃን እንደ ማግኘት ያለ ምክንያት ነው።

ልጁ ከብርሃን ብርሃን እንደሚወጣ ወጣ። ሻማ በለኮስህ ጊዜ ከሻማው ብርሃን ተነስተህ ይህ ብርሃን የዚኛው ልጅ ነው ትላለህ- ምንም’ኳ ሁለቱም አንድ ብርሃን ቢሆኑም።

ይህን ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ማጣቀሻዎች በመውሰድ የበለጠ ማብራራት ይቻላል።

፩. ቅዱስ መጽሐፍ ልጁን (ወልድን) “ቃል” ወይም “መለኮታዊ ቃል-Logos” በማለት ይጠራዋል። ይሄ ማለት የአእምሮ ነባቢ ቃል (uttered mind) ወይም የአመክንዮ መገለጫ (logical utterance) ማለት ነው። እርሱ የእግዚአብሔር ጥበብ ተብሎም ይጠራል። ‘ወልድ’ እና ‘የአእምሮ ነባቢ ቃል’ በሚለው በሁለቱ ቃላት መሃከል ምንም ዓይነት ልዩነት የለም። መጽሐፍ ቅዱስ ወልደ አብ ብሎ እርሱን በመጥራት ከአብ የተወለደ ልጅ እንደሆነ ያረጋግጥልናል።

አንድ መሆናቸውንም ሲያረጋግጥልን ‘መለኮታዊ ቃል’ ተብሎም ይጠራል። በተመሳሳይ ሁኔታ ሁለት ማንነትን (two being) ለሰው መጥቀስ አይቻለንም። ምክንያቱም ሰው ነባቢት ነፍስ [ውስጣዊ ቃላት ያሏት ነፍስ] ያለው ነውና ሁለት መሆንን ለሰው ተግባራዊ መሆን አይቻልም።

ስለዚህም የእርሱን ልጅነት ከመንፈሳዊ እይታ በመነሣት መመርመር ይገባል። ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲህ ብሏል “ደግመን አሁንም እንላለን። ይኸውም የመለኮታዊ ልደትን ከሰዎች ልደት ጋር ማነጻጸር አስፈላጊ አይደለም። ወልድን የእግዚአብሔር ክፍል አድርገን ማሰብ አይቻለንም። እንዲሁም መለኮታዊ ልደት ምንም ዓይነት ስሜት ቢሆንም’ኳ ማንኛውንም ስሜት አያካትትም። ሰዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ይወልዳሉ፥ ግና እግዚአብሔር እንደዚያ አይደለም። እግዚአብሔር ከክፍሎች የተዋቀረ አይደለምና መለወጥ የለበትም። እንዲሁም ወልድ የአብ ክፍሉ እንዲለይ ወይም የተቀየረ እንዲሆን አላደረገውም። ይህ በግልጽ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ተቀምጧል። የእግዚአብሔር ቃል ወልድ ነው። ወልድም የእግዚአብሔር ቃልና ጥበብ ነው።  እርሱ የእግዚአብሔር ክፍል አይደለም፥ እንዲሁም ቃል ወይም ጥበብ አይፈጠርም ። እርሱ መራባት የሚችል ትውልድ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱም አገላለጾች ይገኛሉ።

ስለልጁ (ወልድ) ሲናገር የእርሱን ትክክለኛውን ተፈጥሯዊ ልደት የሆነውን ተፈጥሮ ሲያረጋግጥልን በተመሳሳይ ሰዓት ከሰዎች ልደት ጋር ግራ አንጋባም። እርሱ ቃል፣ ጥበብ፣ ነጸብራቅ ተብሎ ይጠራል። በዚህም የእርሱ ልደት እንዳልተቀየረ ያስተምረናል። ዳሩ የእርሱ ልደት ዘላለማዊ የእግዚአብሔርነት ነው። 

፪. ለምን ወልድ ተብሎ ተጠራ?

በእግዚአብሔር እና በመለኮታዊ ቃል መሃል ያለው ግንኙነት ከተገደበው መረዳታችን በላይ መሆኑን እርግጠኞች ነን። ‘ልጅ’ ወይም ‘አንድያ የተወለደ ልጅ’ የሚለው አገላለጽ በራሳችን አገላለጽ ለመረዳት እንችል ዘንድ እንዲረዳን ነው። እርሱ ከእግዚአብሔር አብ የተወለደ ሲሆን በተፈጥሮም ከአብ ጋር አንድ ነው። ስለዚህም እኛን በተዋሃደ ጊዜ ልጅነቱን በጸጋ ውስጥ እንደ መለኮታዊ ነጻ ሥጦታ ተደሰትንበት።

ይሄን ወልድ የሚለውን ስያሜ ዋጋ የምንሰጥበት ምክንያት በዚህ ውስጥ እግዚአብሔር የሸለመንን ዘላለማዊ ሥጦታ አግኝተንበታልና ነው። በመንፈስ ቅዱስ ከልጁ ጋር ተዋህደን የእግዚአብሔር ልጆች ሆንን።

፫. እግዚአብሔር በንግስና ዙፋን ላይ ተቀምጧል። ይናገራል፣ ይሰማል፣ ያያል ተብሏል። ምንም’ኳ ለመቀመጥ የሚሆን አካል (ለመስማት ጆሮ፣ ለማየት ዐይን) ባይኖረውም ቅሉ።

እግዚአብሔር እነዚህን ችሎታዎች የሚያደርጋቸው እኛ ከምናደርገው በጣም በተለየ መንገድ ነው። ስለዚህም ልጁ በጣም የተለየ መሆኑ እኛ ሰዎች ለሰው ልጅ ካለን እይታ እጅጉን የበለጠ ሊሆን አይችልምን? [ይህን ልዩ ልጅነት] ራሱ እግዚአብሔር እንዲህ አውጇል “የምወደው ልጄ ይህ ነው” ማቴ ፫፥፲፯ ሲል። እንዲሁም ሊቀ ካህናቱ እርሱን “የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን?” ብሎ ሲጠይቀው ክርስቶስም እንዲህ መልሷል “እኔ ነኝ!” ማር ፲፬፥፷፩,፷፪ በማለት።

ሰው የመሆኑን ብስራት ያወጀው መልአክ እንዲህ ብሎለታል “የታላቁ ልጅ” ሉቃ ፩፥፴፪ እርሱ [የእግዚአብሔር ልጅ] ብቻ እንጂ ሌላ ማንም እንዲህ ማለት አይችልም “ማንም በእኔ ካልሆነ በቀር ወደ አብ አይመጣም” ዮሐ ፲፬፥፮ “እኔን ያየ አብን አይቷል”  ዮሐ ፲፬፥፱

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእርሱና [በወልድ] በሌሎች ሁሉም ነብያት መሃል ያለውን ልዩነት በግልጽ ሲያስቀምጥ እንዲህ ብሏል “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን”

ቭቭቭ

፬. የእግዚአብሔርን ተፈጥሯዊ ፍቅር የገለጸው የልጁ ዘላለማዊ ልደት ነው። እንዴት ብትሉ ልጅን ወልዶ፥ ማለቂያ [ስፍር] ስለሌለው ፍቅር  ፍጹም አንድ ዓይነት የሆነ መለኮታዊ ባህርይ ከልጁ ጋር ተጋርቷል። ከእርሱም ጋር አንድ ሆነ። ፍጹም የሆነውን ራሱንና የራሱን ተፈጥሮ በመስጠቱ የእርሱ ፍቅር የማይነጻጸር ነው። ይሄንን የማይነጻጸር ፍቅር ለእኛ የተገለጠልንና ያወቅነው እኛ ልንገነዘበው በሚቻለን መንገድ ነው።

‘እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረት እርቆና ተገልሎ ይኖራል’ የሚለውን መሠረተ ሀሳብ ይህ ልዩ ልደት አጠፋው፥ እርሱ መስጠት ይችላልና።

እያንዳንዱ ነገር ወይም ፍጥረት የግዱን አንድ ነገር ማምረት [መስጥት] ይኖርበታል። እሳት ብርሃንን እና ሙቀትን ይወልዳል። የቁስ አካሎች ራዲዮ አክቲቭ አካል የአቶሚክ ኃይልን ይፈጥራል። ለሰው ልጅ አዕምሮም ተመሳሳይ ሁኔታን ማስቀመጥ ይቻላል። ሃሳቦችና አስተሳሰቦች ከሰው አዕምሮ ይመነጫሉ፥ ይወለዳሉ። ስለዚህ እግዚአብሔርን  መስጠት የማይችል አካል አድርጎ መግለጽ የማይቻል ይሆናል። የብርሃናት ብርሃን፣ የክብር ነጸብራቅ የሆነውን ቃል እርሱ [እግዚአብሔር አብ] አመጣው። ለዚህም ነው ሐዋረያው ቅ/ጳውሎስ እርሱም ‘የክብሩ መንጸባረቅ፣ የባህርዩ ምሳሌ’ በማለት ስለ እርሱ የገለጸው (ዕብ ፩፥፫) ብርሃንን ያለ ነጸብራቅ ማሰብ የማይቻል ነው። በእውነቱ ብርሃንን የማይሰጥ ብርሃን ጨለማ ነው።

እናም እግዚአብሔር መስጠት አይችልም የሚለውን ሃሳብ መቀበል አንችልም። አባቱ [እግዚአብሔር አብ] ያለ ልጁ የኖረበት [ከዘመናት አስቀደሞም ቢሆን] ቅንጣት ጊዜ የለም። ፀሐይ ያለ ጨረርና ሙቀቷ መኖር እንደማትችለው አባቱም ያለ ልጁና ከእርሱ ከሰረፀው መንፈስ ቅዱስ ተለይቶ ብቻውን ሁኖ አያውቅም።

[ይህን እግዚአብሔርን በተፈጥሮ የሚስተካከለው ልጅ እንዳለው ያተትንበትን ጽሑፍ ከአባቶቻችንን አንደበት ጨልፈን እናብቃ]

የእስክንድርያው ቅዱስ ዲዮናሲዮስ

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ተጽፏል “የክብሩ መንጸባረቅ፣ የባህርይ ምሳሌ [. .]” (ዕብ ፩፥፫) “እርሱ የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው” (ቆላ ፩፥ ፲፭) ልክ ስንናገር የሚወጣው ቃል የማይታየው አዕምሮ ምሳሌ እንደሆነው ማለት ነው። ነገር ግን የብርሃን ነጸብራቅ ዘላለማዊ ነው ስለዚህም በእርግጠኝነት ልጁ ራሱም ዘላለማዊ ነው። ብርሃን ሁልጊዜ እንዳለ ካየን ነጸብራቁም ምንግዜም አብሮት እንዳለ ግልጽ ነው። የነጸብራቁ መኖርም የብርሃኑን መኖር እንደሚያመለክተው። ስለዚህም ብርሃን የማይሰጥ ብርሃን አይኖርም። ዘላለማዊ ነጸብራቅ በፊቱ ያበራል፥ ከእርሱ የተወለደውም ሁልጊዜ በእርሱ መኖር ያበራል። እንዲህ እንደተባለ “እለት እለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፥ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ (ምሳ ፰፥፴) ስለዚህም እርሱ የብርሃናት ብርሃን ነውና አባቱ፥ እንዲሁም ልጁ፥ ዘላለማዊ ነው።

ሐዋርያው ጳጳስ አትናቴዎስ

አንዳንዶች እንደሚሉት የእግዚአብሔር ተፈጥሮ በራሱ ፍሬያማ አይደለም ወይም እክል አለበት ካልን እርሱ ብርሃን እንደማይሰጥ ብርሃን ወይም እንደ ደረቀ ምንጭ ነው ማለት ይሆናል። የእርሱ ፍጥረታት የሚቻላቸው ሆነው ግና የእርሱን ተፈጥሮ ክደው ስለ እሱ ሥልጣን ሲያወሩ አያፍሩምን?

ኦሪገን

ስለብርሃን ከእግዚአብሔር አብ ሌላ ምን ልናስብ እንችላለን? ከእርሱ ጋራ የሚኖር የእርሱ ነጸብራቅ (ዕብ ፩፥፫) አይደለምን? ብርሃንን ያለ ነጸብራቅ ማሰብ ፈጽሞ የሚቻለን አይደለም። ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ ወልድ ልጅ ያልሆነበት ጊዜ አልነበረም ማለት ነው።

 

_____________________

አባ ታድሮስ ማላቲ አዘጋጅተው  ቅ/ሚናስ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ያቀረበችውን ቤተ ፍቅር ዘአቢሲኒያ እንደተረጎመው ታኅሳስ ፳፻፰ ዓ.ም

 

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑