እግዚአብሔር እንዴት ሰው ሊሆን ቻለ?

እግዚአብሔር እንዴት ሰው ሊሆን ቻለ?

እግዚአብሔር ፈቅዶልን ባለፈው ጊዜ ቤተ ፍቅር ዘአቢሲኒያ የተረጎመውን የአባ ታድሮስ ማላቲን እግዚአብሔር ልጅ አለውን? የሚለውን ጽሑፍ ማቅረባችን የሚታወስ ነው። እነሆ ዛሬ ደግሞ በፈጣሪ መልካም ፈቃድ እግዚአብሔር ልጅ ካለውና ይህም ልጁ ራሱ እግዚአብሔር ከሆነ ይህ እግዚአብሔር እንዴት ሰው ሊሆን ቻለ? የሚለውን አባ ታድሮስ ማላቲ አዘጋጅተው  ቅ/ሚናስ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ያቀረበችውን ቤተ ፍቅር ዘአቢሲኒያ እንደተረጎመው እንደዚህ ቀርቧል። እግዚአብሔር ልባችንን ይዳብሰው ይባርከን፥ አሜን። እግዚአብሔር እንዴት ሰው ሊሆን ቻለ V.2

63655_319340098175655_625967428_n

አንድ ወቅት ወጣት የመከላከያ መኮንን አግኝቼ ነበር በወቅቱም ወጣቱ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጠየቀኝ

  • ስለኢየሱስ ምን ታስባለህ? እርሱ እግዚአብሔር ነውን?

  • እንዴት ፍጹም የሆነው የእግዚአብሔር ማንነት ሊበላ፣ ሊጠጣ፣ ሊጠማ፣ ሊራብ፣ ሊተኛ፣ ከህመም ጋር ሊሆን፣ ሊሰቀልና ሊሞት ይችላል?

በአጭሩ እንዲህ ጠየኩት

“ወደ መከላከያ ሰፈርህ ስትግባ ነፋሱ ያፏጫል ዝቅትኛ ማዕርግ ያላቸው መኮንኖችና ሁሉም ወታደሮች ለአንተ ሰላምታ ለመስጠት በተጠንቀቅ ይቆማሉ። ከመሃከላቸው አንዱ ወታደር በወታደራዊ ሠላምታ በአግባቡ ሰላምታ ሊያቀርብልህ ፍቃደኛ ባይሆን ምን የሚፈጠር ይመስልሃል?”

እርሱም መለሰ “ወደ ወታደራዊ ማረሚያ ቦታ ይወሰድ ነበር”

ጨዋታችን በቀጠለ ጊዜ እንዲህ አልኩት “ወደ ቤትህ በመጣህበት በማንኛውም ወቅት ልጆችህና ባለቤትህ በተጠንቀቅ ቆመው ሰላምታ እንዲያቀርቡልህ ትጠብቃለህን? ወይስ ልጅህ ሊስምህና ጭንቅላቱን በእጅህ ላይ ሊጥል ትጠብቃለህ? ልጅህ ምናልባትም ምን እንዳመጣህለት በመጓጓት ትንሿን እጁን ወደ ኪስህ ሊሰድ ይችላል። አዎ እርግጥ እንደዚህ ዓይነት ጸባይ ከአንድ መኮንን ወይም ወታደር ሲመጥ አግባብ የሌለው ይሆናል።”

እኛ እግዚአብሔርን እቤቱ እንዳለን ሆነን ስንቀበለው አንተ ግን በወታደራዊ ሰፈር እንዳለ አድርገህ ታስተናግደዋለህ። እርሱ በፍቅሩ ወደኛ መጠቶ ከኃጢአት በስተቀር ሁሉን ተካፈለን። ከእኛ እንዳንዳችን ሆኖ የእኛን ቋንቋ ተናገረ። ይህ እውነተኛ ለሆነ የተግባራዊ ፍቅር ምሳሌ ነው። እኛ ያገኘነው ጣፋጭ የእውነታ ጉዳይ ሲሆንልን አንተ ግን ልትፈልገው የማይቻል ሆነብህ።

እግዚአብሔር በፍቅር ውስጥ የማይቻለውን ሰጠን። ለሰው ልጆች የበለጠ አመክንዮ ያለው የትኛው ሃሳብ ይመስልሃል? በሰማያት ተገልሎ ነገሮች እንዳይከናወኑ የክልከላ ትእዛዝ የሚሰጥ ፍጹም እግዚአብሔር? ወይስ እኛ ወዳለንበት ወርዶ በፍቅሩ የሚያቅፈን ወደ ሰማያት ይዞ የሚወሰደን እግዚአብሔር? ለዘላለም ከሰዎች በሩቁ ተለይቶ የሚኖር እግዚአብሔር ነው? ወይስ በፍቅር ከእኛ ጋር እና በእኛ ውስጥ የሚኖር እግዚአብሔር?

አንዳንዶች ስለምን የመለኮት ሥጋ መልበስ እምነትን ይቃወማሉ?

፩. የሰው ልጅ እግዚአብሔር ሰውን እስከ ሰማያት ወስዶ በዘላለም ክብሩ መንግስቱን ለማውረስ ያለውን ፍላጎት አለመረዳቱ እና የራሱን ዋጋ በእግዚአብሔር ዐይን መረዳት [መገንዘብ] ያለመቻሉ [ለተቃውሞው ምክንያት ይሆናል]

፪. እግዚአብሔር ስለሚጠላውና ስለሚጸየፈው የሰው አካልና የሰው ተግባራት ያለው የተሳሳተ እምነት [አመለካከት]

፫. አንዳንዶች የእግዚአብሔርን መለኮታዊነት ሥጋ መልበሱ እንደገደበው ያስባሉ። ይህ የተሳሳተ እምነት ነው። ለምሳሌ የሰው ልጅ ራሱ ገደብ ባለው ቁመተ ሥጋ የተወሰነ ነው ምንም’ኳ ነፍሱ በተመሳሳይ ሁኔታ የተገደበች ባትሆንም። ቴሌቪዥንና ራዲዮም ምሳሌዎች ናቸው። ሁለቱም  ሊይዙት በሚችሉት ስፍራ መጥን በአካል የተወሰኑ ናችው ዳሩ ግና እነርሱ የሚረጩት ጨረር ብዙ አእላፍ ማይሎችን በዓለም ላይ ይጓዛል። ታዲያ እግዚአብሔር የሠራው አካል [ሥጋ] የእርሱን መለኮትነት ሊገድብ ይችላል?

፬. የፀሐይ ጨረሮች በየቤታችን ይገባሉ፥ በጎዳናዎቻችን ላይ ያበራሉ- በቆሻሻ ማቀፊያ ላይ ባሉ ቆሻሻዎች ላይ ሁሉ ሳይቀር። ጨረሮቹ የደረሱባቸውን ማናቸውም ነገር ያነጻሉ እነርሱ ግን አይቆሽሹም። በጨለማ ስፍራ በገቡ ጊዜ ከጨለማው አይወስዱም ነገር ግን ስፍራውን በብርሃን ይሞሉታል። በተመሳሳይ፥ እግዚአብሔርም ለጨለማችን ብርሃን ሊሠጠን በፍቅሩ በውስጣችን [በላያችን] ያበራል። ነብዩ ሚልክያስ እንዳለው “ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩ ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፥ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል” (ሚል ፬፥፪)

165605_182920358398480_100000415528663_556712_8194340_nእግዚአብሔር ለምን ሰው ሆነ?

፩.  የመለኮታዊ አስተማሪ መፈ’ለግ

የሰውነትን እይታ ኃጢአት አቆሽሾታል [ሰውሮታል]። በኃጢአት ከተበከለው የምድር አካል እጅጉን ተለይቶ በመራቅ በራሱ መንግስት ተገልሎ እንደሚኖር ፥ እግዚአብሔርን ማየት የማንችል ሁነናል። አንዳንዴ ራሳችንን ድኅነት፣ ምኅረት ወይም እርዳታ የማያስፈልገን አማልክት አድርገን እናስባለን። እንዲሁም ሌላ ጊዜ ደግሞ ራሳችንን ያለምንም ኃይል እና ያለምንም ዓላማ የሚኖር ዋጋቢስ ማንነት [ፍጥረት] አድርገን እናያለን። ከሁለቱ በአንደኛው መንገድ እንደምንሄድ አድርገን ራሳችንን እናያለን።  እግዚአብሔር እኛን የሚያፈቅርና በትጋት የሚፈልገን እንደሆነ ፥ ዐይናችንን ከፍቶ እግዚአብሔርን ማየት እንድንችል ሰማያዊ አስተማሪ መለኮት ሥጋ ለመልበስ ወደ እኛ ወረደ። እግዚአብሔር በሠማይ [በመንግስቱ] ምን እንዳዘጋጀልን ወደማሰተዋል የመጣነው ከዚህ ጊዜ በኋላ ብቻ ሆነ።

፪. እርሱ ወዳንተ ቀርቦ በዚህም አንተ ወደ እርሱ እንድትቀርብ

ስለፍቅሩ ምክንያትም ወደ እኛ ዓለም በመምጣት እርሱ ቅድሚያውን [የጀማሪነትን] ወሰደ። ስለዚህም አሁን እንደ አባት ከአንተ ውስጥ ባለው የእርሱ መንፈስ ሥራ ምክንያት ወደ እርሱ ትቀርብ ዘንድ እየጠበቀህ ነው። በንስሓ ወደ እርሱ ለመቅረብ የተማረክ ሁን ምክንያቱም እርሱ ኃጢአተኞችንና ቀራጮችን ይወዳልና። ሁሉን ኃጢአታችንን ይቅር ስላለን ነፍሳችን ከኩነኔ ትድን ይሆናል። እርሱ ወዳንተ ሊሮጥና አንገትህን አቅፎ ሊስምህ ፍላጎቱ ነው። (ሉቃ ፲፭፥፳) በማዳን ሥራዎቹ ውስጥ እርሱን ካልተገናኘኸው ከመጽሐፍ ውስጥ ብቻ ልታገኘው አትችልም። አጎንብሶ እግርህን ሊያጥብህ ሲጥይቅህ ተመልከተው ያኔ በገነት ከእርሱ ጋር ትካፈልና በመኖሩ ሃሴት ታድርግ ይሆናል።

፫. የመለኮታዊ አዳኝ [መድኃኒት] መፈ’ለግ

ከክርስቶስ በፊት በአስራ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ነብዩ ሙሴ ስለመጀመሪያው ሰው ውድቀትና ተከተሎት ስለተገባለት መለኮታዊ ቃልኪዳን ታሪክ ጽፎልናል። በዘፍጥረት ፫፥ ፲፭ ላይ እንደተገለጸው የሴቲቷም ልጅ የቀደመውን እባብ (ሰይጣን) ራስ ይቀጠቅጣል። ከብዙ ትውልዶች በኋላ ስለ ዓለም መድኃኒት መሲህ መምጣት የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ። የአይሁዳውያን ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው ብሉይ ኪዳን የያዛቸው ብዙ ትንቢቶች በአንዱ ሰው በኢየሱስ ብቻ ፍጻሜን አገኙ። በብዙ ነብያት በሺህ ዓመታት ውስጥ ስለመሲው የተጻፉት እነኚህ ትንቢቶች  ስለተፈጥሮው፣ ስለመልዕክቱ፣ ስለሥራዎቹ እና ሞቱና ትንሣኤው ስለሚፈጸሙበት ሁናቴ ሰፊ ገለጻዎችን አካተዋል። የዓለም መድኃኒት ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ማንም ስለ መሲው የተጻፈውን በሙሉ ያሟላ በየትኛውም ታሪክ ውስጥ የለም። እርሱ ሕዝቦች ለረጅም ዘመናት ሲጠብቁት የነበሩት መለኮታዊ መድኅን [አዳኝ] ነው። ነብዩ ኢሳይያስ እንደተናገረው “ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ. . . እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ።” (ኢሳ ፶፫፥ ፲፣ ፲፪)

የነብያት ምስክርነት [ትንቢት]

የነብዩ ዳዊት ምስክርነት (፩፼፲ ቅ.ል.ክ) “ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ ወረደም” (መዝ ፲፰፥ ፱)

የነብዩ ኢሳይያስ ምስክርነት (፯፻፴ ዓመት ቅ.ል.ክ) “ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ!” (ኢሳ ፷፬፥፩)

“ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” (ኢሳ ፯፥፬)

“ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል. . . . የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል።” (ኢሳ ፱፥፮፣፯)

የነብዩ ሚክያስ ምስክርነት (፯፻፲ ቅ.ል.ክ) “አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።” (ሚክ ፭፥፪)

የፍጥረት አለቃን [አስገኚን] መፈ’ለግ

የሰው ልጅ  በምድር ላይ ያለ ታላቁ የእግዚአብሔር ውብ ተፈጥሮ ነው። እግዚአብሔር በአምሳሉና በመልኩ ፈጥሮታል (ዘፍ ፩፥፳፮፣ ፳፯) ከሥልጣን ጋር ንጉስ አድርጎ ሠራው። እጅግ ድንቅ የሆነ የአእምሮ ኃይል፣ ነጻ ፈቃድና ዘላለማዊ ነፍስም ሰጠው። በጨረቃ ላይ [planet] የብስና ህዋን መድረስ እንዲችል ከችሎታ ጋር አዘጋጀው። ለዘላለም በጣም ደስተኛ ሁኖ ይኖር ዘንድ በሰማይ መኖሪያ አዘጋጀለት። ነገር ግን ይህ መልክ [ገጽ] በኃጢአት በቆሸሸ (በተበከለ) ጊዜ፥ የፍጥረት ሁሉ አስገኚ የሆነ አንድ እርሱ እግዚአብሔር የሆነ -የቆሸሸውን ሊያነጻ ወደ ሰው ልጅ የመጣ። ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ እጅግ ወዳጁ [ተወዳጅ] ወደሆነው ፍጥረት መጣ።

እግዚአብሔር እንዴት ሰው ሊሆን ቻለ? የሚለው ወሳኙም ጥያቄ ቀረ።

  • ጌታ ሆይ ነፍሴ ትናፍቅሃለች

            ሠማያት ዝቅ ዝቅ አደረግህ ወደ እኔም መጣህ። በፍቅር ውስጥ ሰው ሆንህ. . .

           በሰዎች መሀከል በተገኘህ ጊዜ የሰውን ልጅ አከበርከው።

           የሰውን ሥጋ በለበስክ ጊዜ የእኔንም አካል አከበርከው።

           ማንኛውንም የቀን ሥራዎች ብሠራ ከእንግዲህ አላፍርም ምክንያቱም ሰው ሁነህ አንተ ሠርተህዋልና 

            የእኔን ተፈጥሮ ለመካፈል ባለመጸየፍህ ክብሬ [ሀብቴ] ነህ ስለዚህም ክብርህን እካፈላለሁ።

  • አንተ ታላቅ አስተማሪዬ ነህ

           ገጽህን እኔ ውስጥ አኑረሃልና እኔም ያንተ ቋሚ ምልክት [ምስል] ሆንኩኝ።

  • አንተ ሰማያዊ አስተማሪዬ ነህ

           እይታዬን ስለከፈትህ  በውስጤ አይሃለሁ ፥ በፊቴም የገነት በር ተከፍቶለኝ አያለሁ።

  • አንተ መልካም መድኅኔ [አዳኜ] ነህ

           ካንተ ጋር ወደ ሰማያዊው ክብር እሄዳለሁ።

____________________

አባ ታድሮስ ማላቲ አዘጋጅተው ቅ/ሚናስ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ያቀረበችውን

ቤተ ፍቅር ዘአቢሲኒያ እንደተረጎመው ጥር ፳፻፰ ዓ.ም

One thought on “እግዚአብሔር እንዴት ሰው ሊሆን ቻለ?

Add yours

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑