ኩሩ ኢትዮጵያዊ ለመሆን አንድ ተጨማሪ ምክንያት -አድዋ ሁለት

ኩሩ ኢትዮጵያዊ ለመሆን አንድ ተጨማሪ ምክንያት –አድዋ   ሁለት

ኩሩ ኢትዮጵያዊ ለመሆን አንድ ተጨማሪ ምክንያት ያገኘንበት ታሪክ የየካቲት ሃያ ሦስቱ የአድዋ ድል ቀጣይ ክፍል ቀጥሏል። TO READ IN PDF

adwa

የአድዋ ጦርነት በኢትዮጵያውያን አኩሪ ድል ቢጠናቀቅም ዳግማዊ ምኒልክ የጦር ኃይሉ ድካምና ለመሰጠት (ለመዋጋት) ያለው አቅም መመናመንን ተከትሎ ጣሊያንን ከባህር አሻግሮ አልገፋውም። በመቶዎች የሚቆጠሩ የጣሊያን የጦር ምርኮኞች ወደ አዲስ አበባ በጥድፊያ ከምኒልክ ቀድመው ተልከው ነበር። የአድዋ ድልን ባከበሩበት የጃንሜዳ ሥነ ሥርዓት ላይ የጣሊያን ምርኮኞችም በፊቱ ተቆጥረዋል። ምርኮኞቹ በሰብአዊ ክብር የተያዙ ቢሆንም’ኳ በቫቲካን የበዛ ጉትጎታና ጥያቄ ወደ ጣሊያን ተመልሰዋል። ምኒልክ ሩህሩህ፣ ቸር ለጋስ፣ ደግ እና ለስህተቶች ጨዋ ነበር። ለአዲሲቷ አዲስ አበባ ተዘጋጅቶ የነበረውን የመጀመሪያውን የጃንሜአ (ወይም ጃንሆይ ሜዳ) ማስታወስ እንችላለን። አሳዛኙ ነገር ግን ከመቶ ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ የቀረው ብቸኛ የህዝብ ቦታ ቢኖር ይህ መሆኑ ነው። ከተማው ባልተለመደ ሁኔታ በቂ ችሎታ ያላቸው የከተማ ነዳፊዎች (Planner) እና መሃንዲሶች የሉትም። እስከ ወጣትነታችን ዘመን የምናውቃቸው የነበሩና የከተማው ውበት የነበሩትን ግዙፍ ዛፎች (እንደ ሾላ፣ ዝግባ፣ ግራር ወዘተ ያሉ) ተተኪ የተባሉት “መሃንዲስ” ተብዬዎቹ ገንድሰው ጨርሰዋቸዋል። እነሆም መለሎዋን (በረሃ የሆነች) የቀረች ከተማ አስቀርተውልን ዝነኛ የሆነውን ተስማሚ አየር እንኳ አበላሽቶታል። እንዲሁም ፍጹም የእግረኛ መሄጃ የሌለው የሚያስብል መንገድ ይገነቡልናል፥ 90% ለሆነው መኪና ለሌለው ነዋሪ መሆኑ ነው! እስከአሁኑ ቀን ድረስ የሚተገበር ታላቅ ድንቁርና!!

የአድዋ ድል የሮማ ከተማ ጠባቂ ከሆነው ከጣሊያን ወታደር ጀምሮ በዓለም ላይ ወዲያውኑ ውጤት አምጥቷል። ቪቫ ምኒልክ እና ውድቀት ለክርስፒ (የዛን ጊዜው የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስተር) የሚል መፈክሮችን ያነገቡ ድንገተኛ ሰላማዊ ሰልፎች ነበሩ። ታላቅ አስደናቂ ነገር የታየው ከአፍሪካ ውጪ የበዛ የጥቁር ሕዝብ ካለባት ከወደ ላቲኗ ሃገር ብራዚል ርቆ ነበር። ብቸኛው የጥቁሮች ጋዜጣ የነበረው ወዲያውኑ ስሙን ምኒልክ አለው። ከርቀት ከደቡብ አፍሪካ አዲስ የኢትዮጵያዊነት እንቅስቃሴ ተወለደ። በቆይታ የመጣው ውጤትም በአሜሪካ ሃርለም የአቢሲኒያ ቤተ ክርስቲያን መከፈት እና በጃማይካ የራስ ተፈራውያን እንቅስቃሴ መነሣት ነበር።

amanflagምኒልክ ወደ ጦርነቱ ሲሄድ ከሶስት ነገሮች ጋር ነበር።

አ) ባለሦስት ቀለሙ የኢትዮጵያውያን ሰንደቅ

ቡ) የኢትዮጵያን ባንዲራ የያዘ ዘውድ የደፋ አንበሣ ያለበት እና  “የይሁዳ አንበሳ ተገለጠ” የሚል (በመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስን የሚያመለክት ነው) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የተጻፈበት ንጉሣዊ ዓርማ፣ በኋላ ላይ የተበረዘውና “ሞአ አንበሳ ዘእም ነገደ ይሁዳ” ወደ ማለት የመጣው ጥቅስ አይደለም።

ጊ) ምኒልክ ሌላም ዓርማ ነበረው። ለክርስቲያን ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ሁሉ መጽናኛ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱሱ ዝነኛ ጥቅስ ያለበት ዓርማ፥ ጥቅሱ እንዲህ ይነበባል “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች”

ከእነዚህ ሦስቱ መለኪያዎች ጋር ነው ወደ ድል ጎዳና ያቀናው።

ለምኒልክ ብቸኛ የቆመለት መታሰቢያ ቢኖር በታላቋ ልጁ በአራዳ፣ አዲስ አበባ የቆመለት ፈረሰኛው ሀውልት ነው። ይህ በዓይFB_IMG_1456820870786ነቱ የመጀምሪያው የፈረሰኛ     ሀውልት ነው። የፈረሱ እግሮች ከቋሚው ጋር ተያይዘዋል። (የዚህ ዓይነት ሁለተኛው ሀውልት የሲሞን ቦሊቫር ነው)። ሀውልቱን የጣሊያን ፋሲሽቶች ነቃቅልው በደረቅ ሌሊት ቀብረውታል። የኢትዮጵያን ሕዝብ ምላሽ ይፈሩ ነበርና ነው በሌሊት ማድረጋቸው። በኋላም የተቀበረበት ቦታ እንደታወቀ ተቆፍሮ በመውጣት ወደ ቀደመ ቦታው (ጥንተቱ) ተመልሷል። በንጽጽሩ የዛሬዎቹ ፋሲሽቶች፥ ምክንያታዊና ተሞክሮአዊ ያልሆነ ድፍን የምኒልክ ጥላቻ ያለባቸው የህወሃት መሪዎች እርሱ የሚወክለውን ነገር ሁሉ ለዘላለሙ ማጥፋት ይፈልጋሉ። መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል ሀውልትንም መልሶ መገንባት ይቻላል። ለሁልጊዜው ምኒልክን ያጠፉት መስሏቸው ይህን ሀውልት አቅልጠው ለሚስቶቻቸውና ለእቁባታቸው ጌጣጌጥ ይሰሩበት ይሆናል። ዳሩ ግና ታሪክ ፈጽሞ አይሞትም። ለአድዋ ጀግኖች ሌላ ምንም ዓይነት ሀውልት የቆመ የለም። የአራዳው ዓለም አቀፍ ታዋቂ ሆቴል የነበረውና ከእቴጌ ጣይቱ በኋላ እቴጌ ሆቴል ተብሎ የተሰየመው በእውሩ ደርግ ወደ ሌላ (አውራሪስ) ስም ተቀየረ። ኋላ ስያሜው እቴጌ መነንን ሳይሆን እቴጌ ጣይቱን ተከትሎ መውጣቱን ሲረዱ በተለመደ ተራ ስም “ጣይቱ ሆቴል” ብለው ሰየሙት። ጣይቱ ካለ ማእረግ ስም ምንም ማለት ስለሆነ ወደ ቀደመ የሚያኮራ የጥንት ስሙ እቴጌ ሆቴል ሊመለስ ይገባዋል። ዳሩ ግና ይህ ሆቴልና የምኒልክ መኖሪያ በመጥፋት ደረጃ ላይ ናቸው። መኖሪያ ቤቱ ጣሪያው የሚያፈስ፣ የተሰባበሩ ደረጃዎችና ወለሎች ያሉት ስለሆነ በማንኛውም ቀን ሊወድቅ ይችላል። የቀደሙት ተከራዮች፥ መንግስቱ በተደጋጋሚ ቦታውን ያረከሰ፣ የቅርቡ መለስም ቢሆን ከምልክትነቱ በቀር ስለምኒልክ መኖሪያ ቁብ የማይሰጠው ነበር።  መንግስቱ ከምኒልክ ጋር እንግዳ ቁርኝት ያለው ነው። በተጨማሪም መኖሪያ ቤቱን እንደ እስር ቤት ተጠቅሞበታል። (እኔ እዛ ታስሬ ነበርሁ)።

የምኒልክ የመቃብር ሥፍራ (mausoleum) በበኣታ ቤተ ክርስቲያን ይገኛል። በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ውስጥ ለመንግስቱና በደርግ  ውስጥ የወንጀል ግብረ አበሩ የክፋት ሥም ባለዝናው ለካፒቴን መንግስቱ ገመቹ ሁለት ተጎራባች ቪላዎች ተሰርቶላቸዋል። አምልኮ የለሾቹ ወንጀለኞች የቤተክርስቲያናችንን የተቀደሰ ሥፍራ ያረከሱበት ሌላኛው ሥራ ነው። ለምን እንዲያ እንዳደረጉ ግን የቅርብ ወዳጆቻቸውና ራሳቸው ናቸው የሚያውቁት። ትንሽ ለማለት ግን ግራ የሆነ ነው።

የአድዋ ጦርነት ድል አንድን ያልታወቀ ሰው ትንቢታዊ ስንኝ እንዲጽፍ አነሳስቶት ነበር። ኢትዮጵያውያን በድል ባይወጡ ኑሮ ምን ይፈጠር ነበር፥

ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ  

ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ

ከአርባ ዓመት በኋላ ፋሲሽት ጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የወረራቸውን ሕዝቦች በትክክል ይህንን ነበር የጠየቃቸው። ብዙ እንቁላል እንዲያቀርቡ! እዚህ ጋር ከጭብጡ ብወጣም ለማለት የምፈልገው ከድኅረ ነጻነት በኋላ ብዙዎቹ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ሥራ የጀመሩት በፋሽስት ዘመን የእንቁላልና ዶሮ አቅራቢዎች በመሆን ነው።

ከአድዋ ድል በኋላ እንግሊዞች እንደልምዳቸው ምኒልክን ወዲያውኑ ታላቁ የሚል ቅጽያ ሰጡት። ለደቡብ አፍሪካዊው ታላቅ ጦረኛ ሻካ ዙሉም እንዲህ አድርገዋል። በምኒልክ ጉዳይ ግን ከጥቂት ዓመታት በኋላ የተለጠፈበት ሥም ተነሣ። ምክንያቱ ደግሞ የጣሊያኖች ክፉኛ ማባበል ነበር። ያሳመኑበት መከራከሪያቸው ምኒልክን “ታላቁ” ብሎ መጥራት ለሁልጊዜውም ቢሆን የሚያዋርደው ጣሊያንን ብቻ ሳይሆን መላው የነጭ ዘርን ነው የሚል ነበር። የዚያን ጊዜዎቹ የአውሮፓ ኃያላን ከ1987ቱ (እ.ኤ.አ) የፋሾዳ ድንገቴ የንግሊዝና የፈረንሳይ ግጥሚያ ጅምሮ  ምኒልክ የተጫወተውን ምስጢራዊ ሚና ዝምታና ውሳኔ ያውቁ ነበር። ይህን አስደማሚ ታሪክ The Race to Fashoda: European Colonialism and African Resistance in the Scramble for Africa (Weidenfeld&Nicolson, 1987).  በተባለው መጽሐፉ David Levering Lewis አውርቶታል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በምማርበት ወቅት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው ሁለት ፕሮፌሰሮች ነበሩ። አንደኛው ስዊዲናዊው ሩበንሰን ሲሆን የአፄ ቴዎድሮስ አድናቂ ነው። ሁለተኛው አሜሪካዊው ማርከስ ሲሆን የእርሱ መመሰጫው አፄ ምኒልክ ነው። ሁለቱም በተከታታይ ስለየ ጀግኖቻቸው የጥናት ጉባኤ አዘጋጅተዋል። እርግጥ ነው ለወጣት አእምሮአችን ቴዎድሮስ የተሻለ ስሜት የሚነካ ነው። “ፈጣሪ ከደነገገ ዓለምን ሙላዋን ልገዛ አስቤያለው፥ እንዲሁም ምኞቴ ካልተሳካ ለመሞት ሃሳቤ ነው” ሲል ቴዎድሮስ አውጇል። ጥቂት ፈረንጆችን የመድፍ መስሪያ ማቅለጫ በጋፋት ከመሠረቱ ጀምሮ እንዲሠሩ አስገድዶ ነበር። “ሴባስቶፖል” ብሎ የሰየመውን መድፍ በጦርነቱ ዋዜማ ወደ መቅደላ የሚገኝ የተራራ ምሽግ ተወሰደ። ያለመታደል ሁኖ ጉጉዎቹ ወታደሮች በአንድ ፈንታ ሁለት የመድፍ ኳሶችን ቢያስግቡበት መድፉ በመጀመሪያ ሙከራው ብቻ ፈነዳ። እስካሁን መድፉ እዚያው ይገኛል። ፓንክረስት የቴዎድሮስን ሙከራ ያልጠነከረ (tongue in cheek) ይለዋል ልክ “እንደጨነገፈ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ አብዮት”። በተጨማሪም ቴዎድሮስ ኢየሩሳሌምን ከኢ-አማኒያን በማንኛውም አርብ ቀን ነጻ እንድትሆን ወስኗል። እንዲህ እንደተዜመ  … አርብ  አርብ  ይሸበራል  ኢየሩሳሌም።

የማርከስ የምኒልክ ተረኮች የመረጃ ሀብታም በመሆኑ በማያልቅ ጥበባቸው አስደስቶናል። የምኒሊክ ጠንካራ ድምጽ ለመጪው ትውልድ ሲባል በንግሊዝ ቤተ መዘክር ተጠብቋል። ይህ ድምጽ ለንግሥት ቪክቶሪያ የላከው መልእክት ነበር።

ስለሆነም የካቲት ፳፫ በመጣ ወቅት ሁሉ የአድዋንና የታላቁን ምኒልክ ክብር እናወድስ። በልጆቻችንንና በቀጣዩ ትውልድ ሁሉ ደግሞ ደጋግሞ የሚተረክ ይሁን። እርሱ የጥቁር ዘር ሁሉ ኩራት ነው። የጥንታውያንን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወደ አንድነት የማምጣት ችሎታ የነበረው እና በመጽሐፍ ቅዱስና በቁራን እንዲሁም በጥንታውያን ጽሑፎችና ቅርሶች ተገልጦ የነበረውን የኢትዮጵያን ታላቅነት ዳግም ያረጋገጠ ውድ የሰው ልጅ ነው። ምኒልክ በአንኮበር ከአደገ በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከመሆኑ በፊት እዛው ነግሧል። ህወሃትና የወያኔ ጀሌዎች የማይሞት ጥላቻ ቢኖራቸውም ቅሉ ምኒልክ ኦርቶዶክስ ክርስቲያንና የሸዋ አማራ ነበረ (አራት ነጥብ) ታዋቂ የኢራን ባለቅኔ ኦማር ካያም (b.1048) እንዳለው “የሚንቀሳቀስ ጣት ይጽፋል፥ እየጻፈ ያለ ይንቀሳቀሳል፥ ማናቸውም ቅድስናም ሆነ ወግ ግማሹን መስመር ሊያጥፉና ወደኋላ ሊያባብሉት አይሆንላቸውም”

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች!

FB_IMG_1432835691972የዶ/ር ምስማኩ አስራት ጽሑፍ ከ ethiopia.org ተገኝቶ በቤተ ፍቅር ዘአቢሲኒያ የተተረጎመ።

የካቲት ፳፻፰ ዓ.ም

አዲስ አበባ

 

One thought on “ኩሩ ኢትዮጵያዊ ለመሆን አንድ ተጨማሪ ምክንያት -አድዋ ሁለት

Add yours

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑