ኩሩ ኢትዮጵያዊ ለመሆን አንድ ተጨማሪ ምክንያት –አድዋ ዜና መዋዕል
<<የዛሬ ሳምንት አድርገው!! በዚህ ላንተ የሚደነግጥ ሰው የለም። ሂድ የፎከርክበትን አሁኑኑ አድርገው። እኛም የመጣውን እንመልሰዋለን። እግሩን ለጠጠር፣ ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የማያድን ሰው የሌለ እንዳይመስልህ። ደሙን አፍስሶ ለአገር መሞት ጌጥ ነው እንጂ ሞት አይባልም። አሁኑኑ ሂድ አይምሽብህ፣ የፈከርክበትን ባሻህ ጊዜ ታደርገዋለህ። እኝም እዚያ እንጠብቅሃለን። እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም፣ ግን እንዲህ ዓይነቱን ውል ከመቀበል ጦርነት እመርጣለሁ>> እቴጌ በኮንት አንቶኔሊ ንግግር ተናድው የተናገሩት
ይህ ጽሑፍ የአድዋን ድል 117ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በ2005 በእደ ማርያም እጅጉ ረታ የተጻፈ ነው። TO READ IN PDF TO READ IN PDF
ኢትዮጵያ ጥንታውያን ከሚባሉት ሀገሮች አንዷ ስትሆን፣ ከአምስት ሺህ ዓመት ያላነሰ ታሪክ አላት። በእነዚህ ዘመናት፣ ቀደምት አባቶቻችን ሠርተው፣ ትተውልን ካለፉት ሥራዎች መካከል የአክሱም ሐውልት፣የላሊበላ ቤተ መቅደስ ሕንፃዎች፣ የጎንደር ቤተ መንግስቶች ለምስክርነት የሚጠቀሱ ናቸው። ባለፉት በእነዚህ ዘመናት ሀገራችን የእርስ በርስ ጦርነትና ከውጭ በመጡ ወራሪዎች፣ ብዙ ቅርሶች ወድመዋል፣ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። ከእዚህ ሁሉ ፈተና በኋላ፣ በዐሥራ ስምንተኛውና ዐሥራ ዘጠነኛው ምዕት ዓመት፣ ሀገራችን ዘመነ መሳፍንት በመባል የሚታወቀው ጊዜ ውስጥ ገባች። ያ ወቅት ደግሞ አውሮጳውያን አፍሪቃን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመከፋፋል ወስነው ዘመቻቸውን የጀመሩበት ወቅት ነበር።
በዚያ ወቅት፣ ይህች በዘመነ መሳፍንት አገዛዝ ኀይሏ የተዳከመችውን ሀገር መልሶ አንድ ለማድረግ፣ የቋራው አንበሳ ካሣ ኀይሉ፣ በኋላ ዳግማዊ ዐጤ ቴዎድሮስ ተብለው የነገሡት ተነሡ። ዐጤ ቴዎድሮስም በእነዚህ መሳፍንት ላይ በመዝመት ድል አድርገው፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ተመልሳ እንደ ቀድሞው አንድ እንድትሆን መንገዱን ከፈቱ። ባደረጉትም ዘመቻ፣ አንድም ቀን ድል ሆነው የማያውቁት ንጉሠ ነገሥት፣ ከአውሮጳውያኑ ጋር በተፈጠረው ችግር፣ የእንግሊዝ ጦር እስረኞቹን ለማስፈታት በዘመተባቸው ጊዜ፣ እጃቸውን ለወራሪው ጦር መስጠትን እንደ ውርደት ቆጥረውት መቅደላ አፋፍ ላይ ሽጉጣቸውን ጠጥተው የክብር ሞትን ጽዋ ተቀብለዋል።
ይሁን እንጂ፣ ዐጤ ቴዎድሮስ ከሞቱ በኋላ የተነሡት ነገሥታት እሳቸው የጀመሩትን ዓላማ በመከተል ኢትዮጵያ ተመልሳ አንድ እንድትሆን አድርገዋል። ከዐጤ ቴዎድሮስ ቀጥለው የነገሡት ዐጤ ዮሐንስ 4ኛ ሲሆኑ፣ በእሳቸው ዘመን የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ እና የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ግዛቶቻቸውን እንደያዙ የዐጤ ዮሐንስን የበላይነት አሜን ብለው ተቀብለው ዕውቅና ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ በየበኩላቸው በቀጥታ ከውጭ ሀገር መንግሥታት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያደርጉ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
አውሮጳውያን የአፍሪቃን ምድር፣ እንደ ቅርጫ ሥጋ በሚቀራመቱበት በዚያ ወቅት፣ ኢጣሊያ በበኩሏ፣ በባህረ ነጋሽ በተባለው፣ እነርሱ ግን በኋላ ኤርትራ የሚል ስም የሰጧት፣ የቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ እግሯን ተክላ ነበር። እንደልቧ ለመስፋፋት ግን፣ ዐጤ ዮሐንስ እንቅፋት ስለሆኑባት፣ የወሰደችው አማራጭ ከሌሎቹ ነገሥታት (ንጉሥ ምኒልክ እና ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት)ጋር ጥሩ የወዳጃነት ግንኙነት መፍጠር ነው። ይኽም ኢጣሊያ ወደፊት ዐፄ ዮሐንስ ላይ ስትዘምት እንዲተባሩዋት ለማድረግ በማሰብ ነበር። ዋናው ሐሳብ ይህ ሆኖ ሳለ ነገር ግን በአሰብ ወደብ ስለሚገቡ ዕቃዎች ቀረጥና በሸዋ ስለሚኖሩ ኢጣሊያኖች ሁኔታ ለመነጋገርና ፔትሮ አንቶኔሊ መልእክተኛ ሆኖ ወደ ንጉሥ ምኒልክ በ21 ሜይ 1883 ዓመተ ምሕረት በመምጣት ውል ተፈራረመ። ንጉሥ ምኒልክም ወደፊት በዐጤ ዮሐንስ ላይ ለመዝመት እንዲያስችላቸው የጦር መሣሪያ እንዲገዙ ተስማሙ። ኢጣሊያኖችም በእውነት ንጉሥ ምኒልክ በዐፄ ዮሐንስ ላይ ይዘምታሉ ብለው ስላመኑ ተጨማሪ የጦር መሣሪያ በመስጠትና እንዲሁም ብዙ ብድር በመፍቀድ የንጉሥ ምኒልክ ጦር ይበልጥ እንዲጠናከር አደረጉት። በዚህ መኸል፣ ዐጤ ዮሐንስ፣ እንግሊዞች በስምምነታቸው መሠረት፣ ምፅዋን ለኢትዮጵያ በማስረከብ ፈንታ ለኢጣሊያ መስጠታቸውን ንጉሥ ምኒልክ እንዲያወቁ አደረጉ። ንጉሥ ምኒልክ አንቶኔሊን በአስቸኳይ ጠርተው፣ ሁኔታውን እንዲያስረዳ ለጠየቁት የሰጣቸው መልስ ስላላረካቸው፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጣሊያኖች ላይ ጥርጣሬ አደረባቸው። እቴጌ ጣይቱና ዳግማዊ አጤ ምንልክ
እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር (እ.አ.አ)ሚያዚያ 1889 ንጉሥ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ወሎ ላይ ውጫሌ በሚባለው ቦታ ሳሉ እያሉ ዐጤ ዮሐንስ መተማ ላይ መሞታቸውን ሰሙ። በአጋጣሚ ሆኖ አንቶኔሊ ተጨማሪ የጦር መሣሪያ ይዞ ሲመጣ ንጉሥ ምኒልክ እንጦጦ ስላልነበሩ፣ ውጫሌ ሄዶ አገኛቸው። አንቶኔሊ ንጉሡ ወደ መናገሻ ከተማቸው እስኪመለሱ ድረስ መታገስ አቅቶት ወደ ውጫሌ የሄደው፣ በኢጣሊያኖች የተረቀቀውን ውል ለማስፈረም ነበር። ሃያ አንቀጽ ያለውን ይኽን ውል ንጉሥ ምኒልክና እንዲሁም በንጉሥ ኡምቤርቶ ስም አንቶኔሊ ሆኖ ፈረሙ። ይህ ውል፣ በተፈረመበትን ቦታ ስም <<የውጫሌ ውል>> ተባለ። ይሁን እንጂ፣ ከዚህ ውል ውስጥ 17ኛው አንቀጽ አማርኛው፣ <<የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮጳ ነገሥታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል>> ሲል፣ የኢጣሊያንኛው ደግሞ <<የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮጳ ነገሥታት ለሚፈልጉት ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት አማካይነት ማድረግ ይገባቸዋል>> ይላል። ይህ አንቀጽ ውሎ አድሮ በሁለቱ ሀገሮች መካካል የአድዋ ጦርነት ተብሎ ለሚታወቀው መነሻ ምክኒያት ሆኗል።
የአድዋ ጦርነት
የኢትዮጵያ ሠራዊት በአድዋ አካባቢ ከሰፈረበት ከፌብሩዋሪ 23 እስከ 28 ጀምሮ፣ ምሽጋቸውን አጠናክረው ሲሠሩ ለጦርነት ዝግጁ ሆኑ። ኢጣሊያኖችን ከምሽጋቸው እንዲወጡ ለማድረግም የፕሮፓጋንዳውን ሥራ ተያያዙት። ይህንን ያደረጉት የኢትዮጵያ ሠራዊት ምግብና አንዳንድ ነገሮችን ፍለጋ ኢጣሊያኖቹ ወደ አሉበት መንደር አካባቢ ሲሄዱ፤ የኢጣሊያኖቹ ሰላዮች በምስጢር ግን የዐጤ ምኒልክ የሆኑት ለጣሊያኑ ጦር አዛዥ ለባራቴየሪ፤
-
ብዙ ወታደሮች ጦርነቱ ገና ብዙ ጊዜ ይወስዳል እንዲሁም የጣሊያንን ትልልቅ መድፍ ለመቋቋም አንችልም ብለው ፈርተው እየከዱ ወደመጡበት ሀገራቸው እየተመለሱ ነው።
-
የጐጃሙ ንጉሥ ከዐጤ ምኒልክ ተቃቅረዋል ስለዚህ ጦራቸውን ይዘው ወደ ጐጃም ሊመለሱ ነው።
-
እንዲሁም ራስ መኮንን ለማመጽ እየተዘጋጁ ነው።
-
አብዛኛው ሠራዊት አክሱም ጽዮን ለመሳለም ሄዷል የሚል የፈጠራ ወሬ ሪፖርት አቀረቡ።
በፌብሩዋሪ 28፤ ጄኔራል ባራቴየሪ፣ ሌሎቹን የጦር ሹማምንቶች ጄኔራሎች፣ አልቤርቶኒን፣ አሪሞንዲን፣ ዳቦርሚዳንና ኤሌናን ስብሰባ ጠራ። ጄኔራል ባራቴየሪም ያላቸው ስንቅ ለ4 ቀን ብቻ የሚበቃ መሆኑን ገልጾ፣ ያለውም አማራጭ ወደ አስመራ ማፈግፈግ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያን ጦር ማጥቃት ነው ሲል ስብሰባውን ጀመረ። አራቱም ጄኔራሎች ወደ አስመራ ማፈግፈግ የሚለውን በአንድ ድምፅ ተቃውመው፣ በኢትዮጵያ ጦር ላይ ዘምተው ጥቃት በመፈጸም፣ አምባላጌና መቀሌ ላይ የደረሰባቸውን ውርደት ማስወገድ እንዳለባቸው በቁጭት ተናገሩ። ጦርነቱም በማግሥቱ በፌብሩዋሪ 29 ሊያደርጉ ወሰኑ።
በአድዋ የኢትዮጵያ ሠራዊት አሰላለፍ እንደሚከተለው ታቀደ። ዐጤ ምኒልክ፣ በአባ ገሪማ ኮረብታ ከቤተ መንግሥቱ የጥበቃ ሠራዊት ጋር ሲሰፍሩ፤ እቴጌ ጣይቱ ደግሞ እዚያው አጠገብ 5 ሺህ የሚሆን ጦራቸውን ከመድፋቸው ጋራ ይዘው ሰፈሩ። ከእቴጌ ጋራ ወ/ሮ ዘውዲቱ ምንሊክና ሌሎች የቤተ መንግሥቱ ሴቶች ነበሩ። እነዚህ በጦርነቱ ሰዓት ውሃ፣ ጥይት በማቀበልና ቁስለኞችን በመንከባከብ የሚረዱ ነበር። በዚህ ጊዜ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት 12 ሺህ ጦራቸውን ይዘው በመሄድ፣ በስተቀኝ በኩል አጥቂ ሆነው ተሰለፉ። ራስ መንገሻና ራስ አሉላ፣ 13 ሺህ ጦራቸውን ይዘው ኪዳነ ምሕረት ላይ ሰፈሩ። የራስ መኮንን፣ የራስ ሚካኤል እና የራስ ወሌ ጦር ደግሞ የመኻከሉን ቦታ ያዘ።
የጦርነቱ ዋዜማ የካቲት ፳፪
3:00 (9:00 pm)
ቅዳሜ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ላይ ጄኔራል ባራቲየሪ ጨለማን ተገን በማድረግ ቁጥሩ 17 ሺህ (10,600 ኢጣሊያኖች እና 7000 ተወላጆችን) የሆነውን አራት ብርጌድ ጦር ይዞ፣ አድዋ ላይ የሰፈረውን የኢትዮጵያን ጦር ለመውጋት ጉዞ ጀመረ። የጉዞውም ዕቅድ፣ አራቱ ብርጌዶች በተለያየ አቅጣጫ ተጉዞው፣ እተመደበላቸው ቦታ ላይ ከመንጋቱ በፊት እንዲደርሱና፣ የኢትዮጵያን ጦር ከከፍታ ቦታ ላይ ሆነው ከበው እንዲያጠቁ ነበር። ይሁን እንጂ፣ በዚያ ጭለማ የያዙት ካርታ ትክክል ስላልነበር፣ በተጨማሪም ጦሩን የሚመሩት ኤርትራውያን በምሥጢር የሚሠሩት ለዐጤ ምኒልክ ስለነበር፣ ጉዞአቸው አስቸጋሪ ነበር።
Leave a comment