የግንቦት ፍሬዎች

የግንቦት ፍሬዎች

untitled

የግንቦት ወር ተለይቶ የሚታወቀው ፀሓያማ ወር በመሆን ነበር። የመስከረምን ድርሻ ከነጠቀ በኋላ ግን ዝነኛና የማይረሳ አዚማም እና ተስፋ ፈንጣቂ ወር በመሆን ተገልጧል። አሁን ግን ብዙን ነገር ተቀያይሯል ከሩብ ምዕት ዓመት በኋላ የአንድ ትውልድ ዘመን ጎልምሶ ሌላኛው ተተኪ ትውልድ እየበቀለ ይገኛል። ለእኒህ ትውልዶች ታሪካቸው ግንቦትን በወራት ሁሉ ላይ ነግሦ ሲንገዋለል ከትቦታል።

የብር ኢዮቤልዩ (ሃያ አምስት ዓመታት) ከማክበራችን በፊት ጎልማሳው ትውልድ ዘመኑን እንዴት ገነባው? ተተኪውስ በምን መሠረት ላይ ተተከለ? የሚለውን ማየት ይገባናል። ከዚያ ባለፈ የፌሽታውም ሆነ የደረቅ-አድርቅ አሉባልታው (propaganda) እና ለዚህ የሚባክነው የድሃውና የታግሎ ተራፊው ሕዝብ ገንዘብ መዳረሻ ማስተዋል ይገባናል።

ቢሆንና ረጅም ጊዜን ወስደን የዘመነ ግንቦት አውራዎችን ከመስከረሞቹና ከኅዳሮቹ ዘመን የግዛት አስተዳደሮች ጋር የንጽጽር ዘገባ ባቀረብን ነበር። ግና ግንባሮቹም ለ ሩብ ምዕት ዓመታት ይህን ይህንኑ ሲያደርጉ ስለነበርና የእኛም ቅኝት የመልስ ምት እንዳይሆንብን፥ ይልቁን ከላይ ላነሣናቸው ሁለት ትውልዶች ስለኖሩበትና ስለሚያውቁት ነባር ሁነት ለማተት ሃያ አምስት ዓመት ከበቂ በላይ ስለሆነ ስለዚህ ወር (ግንቦት) ዜና ግብር እንጽፋለን።

የግንቦት ወር ገዢዎች በነጻ አውጪ መሪነት ግንባራችንን ተቀነባብደን አንድ ኩል ቀብተናል በማለት በከለሉት ቅን’ድብ የንግሥና ዙፋኑን የቤተሰብ አልጋ ወራሽ እያበጁ ቀፍድደው ይዘውታል። ወንበር ምን ታህል እንደምትጣፍጥ በህይወት ያሉት የአፍሪካ መሪዎችም ሆኑ በግድ የተነሱ እንደ መለስ ያሉት አስረድተውናል። ስልጣን ምን ያህል እንደሚያሳውር ከወንበሩ መውጣት ሳይጠበቅብን ተምረንዋል። ከወንበሩ ሲወጡ ከፈጣሪ የተስተካከሉ የሚመስላቸው እድሜያቸው በጤና ሲታወክና ጥሪ ሲመጣ ትንኝ እንደሆኑ ስለሚረዱት የየሰዓታቱ ጸሎታቸው ትንሽ ‘እድሜ’ የምትለው ትሆናለች። የስነልቦና ምሁራን “የምትመኙትን ትሆናላችሁ” እንደሚሉት ሲሆንላቸው እናያለን። ያኔም the dictator handbook ጸሐፊው ብሩስ ቡኖ እንዳለው ‘በአብዛኛው መጥፎ ጸባይ ሁልጊዜ ለምን ጥሩ ፖለቲካ ይሆናል?’ ብለን እንጠይቃለን።

አንድ ትውልድ ለመኖር ሊሟሉለት የሚገቡ መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ይኖራሉ። ያለ ቅድመ ሁኔታዎቹ ግን ዜጋ የመሆን ጥቅሙ እርባና ቢስ ይሆናል። መጠሪያ ከመሆን ካልዘለለ በቀር። ይሄም ሁኔታ ወደ ሊብራሎች አሳብ መርቶን ወደ ግሎባላይዜሽን ወይም ዓለመ አቀፍ አስተዳደር ያስገባናል። መንግስታት ለዜጎቻቸው መሠረታዊውን ፍላጎት ማሟላት ባለመቻላቸው ዜጎች የተሻለ ወደሚመስላቸው ይኮበልላሉ፥ ያልኮበለሉቱም የተሻለ አቅም ያለው ማናቸውም አካል ቢገዛቸው ግድ የማይላቸው ይሆናሉ። መንግሥታቱም ለሕዝባቸው ጥቅም ሳይሆን ጥለዋት ለሚሄዷት ከርሳቸው ስለሚኖሩ ከማንም ሌላ አካል ጋር ይወዳጃሉ። ከመወዳጀት አልፎም ዜጎቻቸውን አሳልፈው ይሸጣሉ። መጨረሻውም ወደማይቀር ወደሚመስለው አንድ ባለጉልበት ወደመመራት ጽንስ ይተገበራል።

አንድ ባለጉልበት የሚመራው ዓለም ደግሞ ከባሪያና ሎሌ ሕይወት እንጂ ሌላ ተስፋ የለውም። ባርነቱን አምኖና ራሱን ክዶ ለሚኖር የያኔውም ሆነ ያሁኑ ዘመን ልዩነቱ አይገባውም። የሁለቱም ዘመን ሰው ከሆዱ ፍትወት ያልተላቀቀና ወደ ምድር የመምጣቱ ጉዳይ ነገር የማይረዳው በመሆኑ የሥጋ ፍቃድ እውር ነው። ይህቺ ዓለምም በእንደዚህ ዓይነት እውሮች የምትመራ ናት። ለእውራኑ ልዩነቱ በጠገበና በተራበ፣ በእንቅልፋምና በሚባንን፣ በንፉዝና በጀገነ በዘገምተኛና በፈጣን ሕዝብ ላይ የመሾሙ ነው። ዳሩ ግና እፎይ የሚሉበት ሁሉም አይነት ሕዝብ በየትም ሃገር መኖሩ ነው። ከዚህ በላይ አስገራሚው ግን ብሩስ ቡኖ የሚሞግተውን ስንሰማ ነው “አምባገነኖች ከዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ መሪዎች ጋር መሠረታዊ ልዩነት የላቸውም፥ በተለያዩ ከባቢ ውስጥ የሚገዙ ቢሆንም’ኳ የሚፈልጉት አንድነው እርሱም ፍላጎታቸውን መጫን ነው”

 

ዘንድሮ ላይ ግንቦትን ስናስባት (የዚህን መታሰቢያ ለየት የሚያደርገው እንዲሉ) እኛ ስለዜግነትና ሰው የመሆን ጉዳይ ሃሁ በምንልበት ወቅት ዓለም የት እንደደረሰች በመደነቅ ውስጥ መገኘታችን ይሆናል። ጣጣው ደግሞ ፈጠንንም ዘገየን አንኳኩቶ መምጣቱ አይቀርም ምክንያቱም ከአሳቢዎቹ ተርታ ሳንሆን ከሚታሰብላቸው ረድፍ ነንና።

ለኔ አዲስ የሆነው ዜና ይህን የማይቀየርና የማይጠፋውን የእግዚአብሔርን ቃል ይጠራልናል፤

“ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥ የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል።” ዮሐ. ራዕይ ፲፫፥፲፮

ቃሉም በቅርብ ጊዜያት ሊፈጸም ስለሚችል ጉዳይ ማናቸውም ያለዚህ ምልክት ሊገዙ ወይም ሊሸጡ እንደማይችሉ ይነግረናል። ይህም ምልክት ምን ሊሆን እንደሚችል ለረጅም ጊዜያት ሲገመት ቆይቷል። ንቅሳት? የተመረጠ የክንድ ላይ ዓርማ ወይም በግንባር የሚታሰር ዓርማ ይሆን ተብሏል። አሁን ዘመናዊው ቴክኖሎጂ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት ሊፈጽም እንደተዘጋጀ መረዳት ይቻላል።

ዜናውን በማኅበራዊ ገጾች ስሰማ ጉዳዩን ከተነሣበት ምንጭ ለመድረስ ማጣራት ያዝኩኝ። ጉዳዩ በፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ ኦባማ ኬር (በታወጀ ስሙ Affordable Care Act) የተባለው የጤና ሽፋን ከተረቀቀ ጀምሮ ይታወቃል። የሰዎችን የጤንነት መረጃ ለመሰብሰብ የሚተከል ማይክሮ ቺፕስ እንደሚኖር የሚያትተው ክፍል ከረቂቁ አልፎ በጸደቀው ህግ ላይም ሰፍሮ ይገኛል። እስካሁን በክሬዲት ካርድ ላይ፣ በድሮን ወዘተ ይደረጋል እንጂ በሰዎች ቆዳ ውስጥ አይቀበርም በማለት ብዙ ማስተባበያ ሲሰጥበት የነበረው ይህ ጉዳይ ለእኔና ለፋና ራዲዮ ሰሞነኛ የሆነው ዓመት ያለፈው ዜና ነበር። ያኔ እንዳዲስ በዜና ማሰራጫዎች በሙሉ አንድን ምንጭ በመጥቀስ ሲተነተን ሰንብቷል። ከዚህ ቀደምም ይሄን የመሰለ ጉዳይ “የአሜሪካ ትምህርት ቤቶች በ2015 በልጆች ላይ ማይክሮ ቺፕስ እንዲተከል ሊያስገድዱ ነው” ተብሎ ተነዝቶ ነበር።

የእኛ የሰሞኑ ኦባማ ኬር ጉዳይ ዋነኛ የወሬ ምንጭ ኤን ቢ ሲ የተሰኘው የራሳቸው የዜና ጣቢያ ሲሆን ሌሎች የእርሱን ምስለ ድምጽ በመቅዳት ሲያስተጋቡ ከርመዋል። የተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በመቀበልና በመከላከል ተከፋፍለዋል። ኤን ቢ ሲ በ2007 ላይ ከአስር ዓመት በኋላ በ2017 አሚሪካውያን በቆዳቸው ስር የሚቀበር ማይክሮ ቺፕስ እንደሚጠቀሙ የተንበየበትን ዘገባ አስታውሶ አምና ባወጣውና ሰሞኑን በፋና በተዘገበው ዜና አሜሪካውያን በሙሉ በ2017 በቀጣዩ አመት ማይክሮ ቺፕ ሊገጠምላቸው እንደሆነ ይገልጻል።

williamsእስቲ እናንብበው

 አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 18 ፣ 2008 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ በቀጣዩ አመት ሁሉም ዜጎቿ እጅ ላይ ማይክሮ ችፕ ልትገጥም ነው። ይህ የሚሆነው የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥና እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ነው እየተባለ ነው። የማይክሮ ችፕ ገጠማው በቀኝ እጅ ላይ የሚከናወን ሲሆን፥ ተጠቃሚው በመሳሪያው አማካኝነት መገበያየት፣ መግዛት፣ ገንዘብ መላክ እና ሌሎችን ነገሮች ማድረግ ይችላል ተብሏል። በአጋጣሚ መንገድ የወጣ ሰው ገንዘብ ባይኖረው እና ችግር ቢያጋጥመው እንኳን፥ መሳሪያው ስለተገጠመለት የተሰጠውን የአይ ፒ አድራሻ በማስመዝገብ የፈለገውን መግዛትና መገብየት ይችላል ነው የተባለው።

ቀጠን ያለ የሩዝ ፍሬ የሚያክል መጠን ያለው መሳሪያ የተገጠመለት ሰው እያንዳንዱ እንቅስቃሴም በመንግስት ቁጥጥር ስር እንደሚሆን ኤን ቢ ሲ ኒውስ የሰራው ዘገባ ያሳያል። በተለያዩ ግዛቶች ተዘዋውሮ በተሰራው በዚህ ዘገባ፥ መሳሪያው ከጨቅላ ህጻናት እስከ አዋቂዎች ከዚህ አልፎም በእንስሳት ላይ እንደሚገጠም ያሳያል። ይህም የዜጎችን እንቅስቃሴ መቆጣጠር እና ብሎም የሚጠፉ ህጻናትን ለመከታተል ያስችላል ብለዋል በኤን ቢ ሲ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎች እና የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች። “ለስራ ከቤት ስወጣ አሳሳቢ የሚሆንብኝ የልጆቸ ጉዳይ በዚህ ቴክኖሎጅ ይቀረፋል” ብላለች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ የሆነች እናት። እንደ እርሷ ገለጻ በልጆቿ ላይ የሚገጠመው ቴክኖሎጅ የእነርሱን አጠቃላይ ውሎ መከታተል ስለሚያስችል ከክፉ ነገር የራቁ ናቸው፤ እናም ወድጀዋለሁ ብላለች።

ከዚህ ባለፈም ህገ ወጥ እንቅስቃሴንና እንደ ሽብር ያሉ አለም አቀፍ ስጋቶችን ቀድሞ መለየት እና መከላከል የዚህ መሳሪያ አላማ መሆኑም ተገልጿል። ይህ ቴክኖሎጅ እንደ ችካጎ ባሉ ግዛቶች በርካታ ተጠቃሚዎች ሲኖሩት፥ በቨርጅኒያ ግን እንዳይተገበር ቅስቀሳ ተጀምሯል። ምክንያቱ ደግሞ “የምናደርገው እንቅስቃሴም ሆነ የዕለት ተዕለት ውሎ እና አለፍ ሲልም የጤናችን ሁኔታ በዚህ መሳሪያ ክትትል መደረጉ ምቾት አይሰጠንም” በማለት። ከዚህ ባለፈ “ምናልባትም መንግስት ታዛዥ አይደሉም ብሎ ያሰባቸውን ሰዎች፥ በዚህ ቴክኖሎጅ አማካኝነት የመቅጣት አቅም አለው” ሲሉም ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል። ያም ሆነ ይህ ግን እያንዳንዱ አሜሪካዊ ወደደም ጠላም ይህን መሳሪያ በቀጣዩ አመት ማስገጠምና፥ በልዩ ክትትል መኖር ግዴታው ነው ተብሏል። ይህ ማይክሮ ችፕ በ10 አመታት ውስጥ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እንደሚገጠምም ባለሙያዎች ተናግረዋል። በኦባማ ኬር አማካኝነት የተዘጋጀው ማይክሮ ችፕ ዝግጅቱ ሙሉ በሙሉ ያለቀ ሲሆን፥ ከወራት በኋላ አሜሪካውያን እጃቸው ላይ ያስገጥሙታል።”

የግንቦት ጹሁፌ ላይ ይሄን ማንሣቴ ነገርን ነገር ስቦት ቢሆንም ቅሉ ዓለም የደረሰችበትና እኛ እንመኘው ዘንድ ያለንን ለማናጸር እንዲረዳን ይሆናል በማለት ነው። አንድ ዜጋ በሚኖርበት (በተወለደበት) ሥፍራ (ሃገር) ባለይገባኛል ይሆን ዘንድ ከትውልድ ቦታ ስሙ በዘለለ ሊሟሉለት የሚፈልጋቸው መሠረታዊያን ጉዳዮች አሉት። ተተኪውም ሊተካበት የሚያረጋግጥለት ዋስትና ያስፈልገዋል። እንዲህ እንየው የ’መወለድ ቋንቋ’ ብሂል ለሁሉም ይሆናል፥ መወለዱ ሊያስገድደው ምን ጉዳይ ይኖረዋል?

አዲስ ተተኪ ትውልድ ዋስትና ሊኖረው ይሻል፤ የምግብ ዋስትና፣ የደህንነት ዋስትናና የመኖር ዋስትና እንዲኖረው ያስፈልገዋል። ይህ ሰው ለሆነ ሁሉ የሚያስፈልገው ነው። ዳሩ እያንዳንዱ ሰው ከብዙ ሕዝብ ጋር እየኖረ ብቻውን ሊያሳካው ስለሚከብደው አስተዳዳሪ ይሾማል፥ ውክልናውን ይሰጠዋል። መንግስት (አስተዳዳሪ) ያስፈለገው መብቱን ሊያስጠብቅለት እንጂ መብቱን ሊሰጠው አይደለም። ገዢዎች ሲሆኑ የመብት ሁሉ ምንጭ ወንበራቸው ይመስላቸዋል እንጂ።

ስለሚበላውና ስለሚጠጣው፣ ስለሚለብሰውና ስሚያርፍበት ዋስትና ሊሰጥው ያልቻለ ሃገር ለተወላጁ ምኑነው? ሀገር ከስሟ ምን ጉዳይ አላት? ቆጵሮስ ሆነች ሶማሊያ፣ አሜሪካ ሆነች ሊቢያ፣ አፍጋኒስታን ሆነች ራሽያ ሁሉም እንደሃገር አንድና እኩል ናቸው-ተወለደባቸው። ሃገራቸውን የበለጠ የሚያስውባትና የሚያስወድዳት ልታሟላላቸው ባዘጋጀችው ሙላቱዋ ይሆናል። ማንም ሃገሩ ምኞቱና ፍላጎቱን ካሟላችለት ሌላ ለመቀላወጥ ህልም የሚኖረው አይመስለኝም። ህዝቤ ሁላ በህልሙ የሚያስባት ሆነ ‘እዛ እንዲህ ሁኜ ብወለድ. . .’ የሚልባት አሜሪካ ፍላጎትን ለማሟላት የምታቀርባቸው ምርጫዎቿ ናችው ማማለያዋ።

ታዲያ ሃገር ይህን እንድትሆን አሊያም ያን እንድትሆን የሚያደርጋት ውክልናውን የያዘው መንግስት ነው። በሌላ አነጋገር ለሃገር ያነሣናቸው ተጠይቆች ለመንግስት የሚቆሙ ናቸው። ስለዚህም ተተኪው ቢያንስ መሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶቹ እንዲማሉለት ይፈለጋል። ከዚያም ቢያንስ በፍላጎቱ ላይ የተመሰረተ ትምህርትና ሥልጠና ሊያገኝ፣ ለተማረበትና ለሰለጠነበት ሙያ የሥራ ዕድል ሊያገኝ፣ በነጻነት ሃሳቡን ሊገልጽና በሃገሩ ጉዳይ ተሳትፎ ሊያደርግ ተሳትፎውና ተጠቃሚነቱም ፍትሃዊነት የተሞላው እንዲሆን ይፈልጋል፥ ፍላጎቶቹ ግን ከምኞት በላይ ናቸው። ሌላኛው ጎልማሳ ደግሞ ከተተኪው ፍላጎት ከፈ ባለ መልኩ ምርጫውና እንዲሟሉለት የሚሻው ይበዛል። ሲሟሉለትም በጥራትና በብዛት ይመዝናቸዋል። መሠረታዊ የአገልግሎት ዘርፎች የሆኑት የውኃ፣ የመብራት፣ የስልክና የመገናኛ አውታሮች እንዲሟሉለት፣ የመጓጓዣ አቅርቦት፣ የመንገድ፣ የጤና፣ በነጻነት የመንቀሳቀስ ወይም በቡድን ያለመበየን ወይም ያለመገለጽ ፍላጎት፣ በነጻና በፍትሃዊነት መሪውን የመምረጥ የመረጠውንም አካል የመቆጣጠርና ለሚሰራቸው ጥፋትና መልካም ሥራዎች ተጠያቂ እንዲሆኑለት ይፈለጋል።

“በፖለቲካ ውስጥ በአጋጣሚ የሚሆን ነገር የለም፤ ከሆነም ግን እንደዚያው ታቅዶ እንደነበር እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ” ይላል ፍራንክሊን ሩስቬልት። ሃገራችን አሁን ያለችበትን መልክና ጸባይ እንድትይዝ የሆነው ታቅዶና ታልሞ እንደሆነ የመሪዎቻችንን ፍሬያቸውንና ሰንዶቻቸውን በማጋላበጥ መረዳት ይቻላል። ወጣቱ በሱስ ጊዜውን እንዲያጠፋ ማደንዘዣዎቹን ያቀረበለት ማነው? ስለ ራሱ የተሻለ ለውጥ ወይም ስለ ሃገር መሻሻል ለማሰብ ትውልዱ ጊዜ አልተረፈውም፤ ብዙውን ጊዜ ስለማይነቃ ሲነቃም ያው ማደንዘዣው ይጠብቀዋል። ስለሆነም የትውልድ ስብዕናና ቁመና ተሰልቧል። ያለምርጫና ያለፍላጎት ወይም ኑሮ አስገድዶት የተማረውም የሥራ ያለህ የሚለውን ቁጥር በየጊዜው ያበዛዋል። መማር እንጂ ሥራ መያዝ ብርቅ ስለሆነ።

በአጥር ተቧድኖ የሚያስተሳስረው ክር እየተበጠሰ በየወቅቱ ሲጎነታተልና ሲቦጫጨቅ ማየት የዘመናችን ጀግንነት ከሆነ ሰንብቷል። ማነው የአንድነት ስሜትን የሚያጠለሽ፣ የጋራ የሚሏትን ጣራ ሃገር የሚያከፋፈል፣ በህብረትና በአንድነት ተሰባስቦ የተሻለችውን የሁሉን ስሜት የምትገዛ መንደር የመፍጠር በሽታን ለማስታገስ ማነው ይህን መድኃኒት የፈጠረው?

የቀደምት ነዋሪዎች ማንነትና መለያዎች ለዛሬዎቹ መነሻችን የሆነው ማንነታችንን ከረግረጉ ወድቆብን በጨቀየው እጃችን ለማጽዳት የምንዳክረው ስለምን ይሆን? እረ ለመሆኑ ማነው ረግረጉን የገለጥው? ኩራታችን ታሪክ፣ ህልማችን የተፈጸመ ተስፋ የሆነብን። የያዝነውን ጥለን የማይያዘንን ስንጎትት፣ የተያዛቸው የመሰላቸው ከያዙት በኋላ ስለሚያደርጉት ግራ የሚጋባቸው፣ ለምልክት የሚሆን መለያ የሚያወድም ጭራ ትውልድ የሆንነው ስለማን ዕቅድ ነው?

EPRDF

 

ዛሬ ግንቦት ላይ ሆነን ግንቦትን ብናማት ፍራንክሊን ስላንቺ ተቀኘ በማለት ይሆናል። ያልተዘራ አልታጨደም። በአጋጣሚ የሆነም የለም። የሆነ ቢመስለን እንኳ እንዲያ እንዲሆን ታቅዶ ስለነበር ነው። ይቺን ኢትዮጵያ ከሃያ አምስት ዓመት በፊት የሳሏት ባለ አስራ ሰባት ቁምጣዎች ነበሩ። የሳሏትን እያደመቁ ሩብ ምእት ዓመት ቆጠሩ።

የተሳለው ከደመቀ

                                                                     በልብ ሁሉ ጸደቀ

                                                                      ጆሮም ደጋግሞ ከሰማ

                                                                      ከሆድ ገብቶ ተስማማ

                                                                       ያኔም. . .

                                                                       ‘ውሸት ቢደጋገም’ ሚሉት ቀረርቶ

                                                                       ጩኸት ሁኖ ቀርቷል እውነት ሁኖ በርቶ። 

ምናልባት የጆሴፍ ጎብልስ ንድፈ ሃሳብ ይሄ ሳይሆን ይቀራል?! ይቆየን (ይቀጥላል)

 

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑