የግንቦት ፍሬዎች ሁለት

የግንቦት ፍሬዎች ሁለት

To Read in PDF

ዘመነ ግንቦታውያን ከሰጡን ፍሬዎች መቅመስ ጀምረናል። የጎልማሳው ትውልድና የተተኪው ትርክት እንደቀጠለ ነው። ከፍሬዎቹ አንዱ በሆነው የዜግነት ክብር ላይ ዛሬ እንቆያለን። ከዚህ ቀደም በዚህ ርእስ ላይ ጽፌ ነበር። ይሄኛው ጽሑፍ ዝርዝር ዜናሁ ነው። ሰው በመሆን ጸጋና በጥቅሙ ደስታ አንድ ሆነን ተሰርተናል። በምንኖርበት ሥፍራ ባስቀመጥናቸውና በተቀመጡብን አለቃዎች ምክንያት ይህ የሰውነት ድርሻ እንዲለያይ ሁኗል። ዳሩ ግና የሥሪታችን መሠረት አንድ መሆን ተገቢውን ሁሉ እንድናገኝ እንዲገባን ያስረዳናል። ይህን መረዳት ከማምጣት ይልቅ ‘ጸጋ የበዛላቸው’ ሰዎች ወዳሉበት መሳብና መጎተት ምርጫችን ሁኗል።

ጎልማሳውና ተተኪው ትውልድ በሃገሩ ሊያሳካውና ሊያገኘው ያልቻለውን ክብር በሌላ ሃገር ውርደት ውስጥና ክብር የማግኘት ሂደት ውስጥ ይፈልገዋል። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂ በላይችን ቁብ ያለው ‘መንግስት’ ነኝ የሚለው አለቃ ይሆናል። 

ከአንዱ አገር ወደሌላው እንድንሰደድ/እንድንፈልስ የሚያደርጉን ኃይሎች የሚገፉ ወይም የሚስቡ ኃይሎች ይሆናሉ። ታዲያ ምን ዓይነት የተለየ ኃይል ነው ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን አደጋና ችግሩን ሁሉ ሊጋፈጡ ያለማስረጃ ወደ ሩቅ ሃገር እንዲዘምቱ የሚያደርጋቸው?

ከአንድ ቦታ ወደሌላው የሚስቡ ኃይሎች ለምሳሌ ሰዎች በህይወታቸው ለውጥ ሲፈልጉ፣ ሌላ አይነት ባህል ለመልመድ ሲሹ፣ የተሻሉ የሥራ ወይም የአገልግሎት እድሎችን ለማገኘት ሲመኙ ይሆናል። ወደ ሌላ ቦታ የሚገፉ ኃይሎች ደግሞ በአብዛኛው በሰዋዊ ፍቃዶች ግፊት የሚመጡ ኃይሎች ይሆናሉ። እነዚህም ግፊቶች የስነልቦና፣ የስሜታዊነት፣ ና የአካላዊ ድካም ሊሆኑ ይችላሉ። ጦርነት፣ የፖለቲካ ተጽእኖ፣ የከፋ ድህነት፣ የማህበረ-ባህል ተጽእኖ የግፊት ሃይል ምሳሌዎች ይሆናሉ።

በአሁን ጊዜ ወደ 232 ሚሊዮን የሚሆኑ ህዝቦች ከቤታቸው እርቀው ይኖራሉ። ከ25 ሚልየን በላይ ህንዳውያን እና ወደ 7 ሚልየን የሚሆኑ ደቡብ ኮርያውያን ከትውልድ ቀያቸው ርቀው ይገኛሉ። ከ3 እስከ 6 ሚልየን አሜሪካውያንም በሌላ ሃገር ይኖራሉ ተብሎ ይታመናል። የሚደንቀው ግን አሜሪካ ከዓለም ክፍል ላሉ በሚልየን ለሚሆኑ ህዝቦች የስደት መዳረሻ በመሆን መመረጧ ነው። በዚህ ወቅት 3 ከመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ ከሃገሩ ተለይቶ በሌላ ሃገር ይኖራል።

በኢትዮጵያ ያለው የፍልሰት ኃይል ከሚጋፋው የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ኃይል ይገለጻል። በአሁኑ ጊዜ ያለውን የኢትዮጵያ ፍልሰት ለመረዳት በጥልቀት እንመልከተው። የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉተ አስርት ዓመታት የሁለት አሀዝ እድገት ይዞ መዝለቁን ይገልጻል ዳሩ ግና ከዓመት ወደ ዓመት የወጣት ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል። በዓለም በየትኛውም ሁናቴ ቢሆን አንዲት ሃገር እድገት ካስመዘገበች የሥራ እድልና ገቢ ሊጨምር ይገባዋል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ያለማስረጃ የሚጓዙት ወጣቶች ቁጥር ሊቀንስ እንደሚገባ ትገምታላችሁ። ምንም’ኳ ስደትን ማጥፋት ባይቻል የምጣኔ ሀብት እድገት ካለ መቀነስ ይቻላል። እውነቱ ይህ ከሆነ ስለዚህ ለወጣቶቹ ይህ እድገት የተተረጎመበት መንገድ የሆነ ስህተት ያለበት ይመስላል።

የሥራ አጥ ቁጥር ውስጠ ወይራ ሁኖ ከግሪክ 26.8%፣ ከስፔን 24.3%ና ከደቡብ አፍሪካ 25% እጅግ አንሶ 17.5% ብቻ እንደተመዘገበ የመንግስት ዘገባዎች ይገልጻሉ። ይህ ግን ቅኔ ነው-ለወጣቱ። ይህም ሁኖ ግን በከተማ ከ15-30 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣት ወንዶች የሥራ አጥነት ቁጥር 48% ነው። የሥራ አጥነት ቁጥር ለተከታታይ ዓመታት መዝለቁም ILO የገመታቸው ከ70-80% የሚሆን ሠራተኛ ኃይል ወደ informal economy (ድብቅ ምጣኔ ሀብት) እንዲገቡ አድርጓቸዋል ይላል financial standard forum, 2009 ላይ። የሥራ እጦት አስጊ አይደለም ብለን የእርሱን ዘገባ ብንከተልም የስደት ምክንያት ሊሆን የሚችለው በመጪው ጊዜ አለመተማመንና አነስተኛ ገቢ ይሆናል። ለአዲስ አበቤና ለሌሎቹ ወጣቶች ሌላው ቅኔ የ‘አብረቅራቂ እድገት’ አሉታዊ የስነልቡና ተጽእኖ ነው። ሃገራት ‘አብረቅራቂ እድገት/glitz economy’ እየፈጠሩ ሲሄዱ የወጣቱን የምጣኔ ሀብት ፍላጎት ማሟላት አይችሉም። ምክንያቱም በአቅርቦትና ፍላጎት መሃል ያለው ርቀት የትየለሌ ስለሚሆን። አዳዲስ መዝናኝዎች፣ ውብ ሆቴሎች፣ ድንቅ ቤቶች ለወጣቱ ኢፍታዊ ሁኖ ይሰማዋል- ያያቸዋል እንጂ አይጠቀምባቸውም ምክንያቱም ዋጋቸውን ስለማይችል። ዘመናዊ መኪና ቢያይም እርሱ ግን ታክሲ ወይም ባስ እንኳ መክፈል አይችልም። ይህም ግጭት የአዲሱን ትውልድ ስነልቦና ይጎዳል። ስለሆነም ከዚህ ለማምለጥና ሊሳተፍባቸው የሚችላቸው እድሎች ወደ ሚፈጥሩለት ሃገር ለመሄድ ይነሣል። ይህም ያንን አደገኛ ጉዞ ለመጀመር በቂ ምክንያቱ ይሆናል።

ሌላው ትልቁ ተጽእኖ ፈጥሪ ምክንያት ወላጆቹና ቤተሰቡ ከልጁ የሚጠብቁት ነው። ድህነት ማህበራዊ ችግር እንደመሆኑ ራሱንና ቤተሰቦቹን ለመርዳት ሲል ተገፍቶ ይወጣል። ለወጣቱም ሆነ ለአረጋውያን ምንም ዓይነት የማህበራዊ ዋስትናም ሆነ ድጋፍ በመንግስት በኩል የለም። ወላጆች ከልጆቻቸው አንዴ ካደጉላቸው በኋላ እርዳታ ይጠብቃሉ። የወላጆቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት በቂ እድል ስለሌለ ልጆቹ ሥራ ለማግኘት በመጓጓት አሳዛኙን ሕይወት ይጀምራሉ። ይህም እውነታ ልጆች ወላጆቻቸው በህይወት እንዲቆዩ ለመርዳት ደህንነታቸውን እንዲሰዉ ይገፋቸዋል።

በዚህም ሴቶች ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው ሆነው ይገኛሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴት ኢትዮጵያውያን ዝቅተኝ ክፍያ እንደሆነ፣ የአካል ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል፣ የጾታ ትንኮሳ እንዳለ እያወቁም ቢሆን ወደ አረብ ሃገራት በመጓዝ ለሚወዷቸው መስዋእት ለመሆን ሲሉ አደጋውን ይጋፈጣሉ። ወንዶቹም ቢሆኑ ወደ አውሮፓ ሃገራት የመካከለኛ ምስራቅ በረሃንና ህጋዊ ባልሆኑ ጀልባዎች የሜድትራንያን ባህርን በማቋረጥ የምጣኔ ሀብት እድል ፍለጋ ሂወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ። በአጠቃላይ የምጣኔ ሃብት ግፊት ዋነኛ የፍልሰት ኃይል በመሆን ወጣቶች ሃገራቸውን በመልቀቅ አስፈሪና አስቸጋሪውን ጉዞ ያለ ማስረጃ ይቀላቀሉታል።

የፖለቲካ ግፊት በኢትዮጵያ እንደ ምጣኔ ሀብቱ ዋነኛ የግፊት ኃይል ሲሆን በመሰረቱ ግን በኢትዮጵያ ሁናቴ በፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ግፊቶች መካከል ያለውን ልዩነት በትክክል ለይቶ ማስቀመጥ አይቻልም። ምክንያቱም ለብዙ ዜጎች የምጣኔ ሀብት እድሎች የተያዙት ወይም የማይገኙት በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በመሆኑ ነው።

15ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በተደጋጋሚ እንደሚናገረው ስደት በሁሉመ ሃገር መኖሩ እርግጥ ነው። የስደቱን ምንጭ ለማጥናት ፍላጎት ስለሌለው ነው እንጂ። ዋነኛ ምክንያቱ የነገ ሁኔታ አስተማማኝ አለመሆኑና የነጻነት እጦት መሆኑ ጠንቅቆ ስለሚረዳ ነው። ቢያንስ ደላላዎች ላይ ብቻ ከማላከክ የተሻለ ሊያሳየን ይገባል። ሌላኛው የሚያቀርበው ምክንያት በአዲሱ ትውልድ የተገነባው በአቋራጭ (ፈጥኖ) የመበልጽግ ዝንባሌ ነው ይለናል። ለዚህም ምሳሌ 66 በኬኒያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሌላ ሃገር ለመሄድ 4.2 ሚሊየን ብር ማዋጣታቸውን ይገልጻል። ይህ በጣሙን ብዙ ችግሮች ያሉበት ብያኔ ነው። በመጀመሪያ ላይ ወጣቱ ተስፋ የሚቆርጠው በሃገሪቱ ያሉትን የንግድ እንቅስቃሴዎች መንግስት በብቸኝነት ስለተቆጣጠራቸው ነው። ብድር፣ እገዛና እርዳታ ገበያውን ነጻ አድርጎ ቢያቀርብ ማንም እግሩን ሊያነሣ ባልተመኘ ነበር። አሁንማ ከውጭ የሚላከው ብር (remittance) መብዛትና ከጉዞው ኪስ የሚያስገባው ብር ከፍ ያለ በመሆኑ ቁብ አይሰጠውም። የሠራተኞቹን መብት ለማሰጠበቅ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በመንግስት በሚደገፉት ላኪ ድርጅቶች (agencies) ወደ አረብ ሃገራት ሠራተኞችን ይሸጣል። ቢያንስ ከሃገራቱ ጋር ያለው ትብብር እንዲደናቀፍ አይሻም። በተጨማሪ የፈለሱትን ሠራተኞች መብት ለማስከበር ከመከራከር ይልቅ በሙስና በበሰበሰው መንግስት በሚታገዙ ድርጅቶች (agencies) ጋር በመሆን ህጋዊ ካልሆኑ ስደተኞች ገንዘብ ለመሰብሰብ ከሰው አዘዋዋሪዎች ጋር ተባበሮ ይሠራል።

የኢትዮጵያ ‘መንግስት’ የህዝቡን ሰብአዊ መብት እንደሚረግጥ ብዙ ማሰርጃዎች አሉ። ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እቀባና የነጻነት መነፈግ ዋነኛ ተጠቂም ወጣቱ ክፍል ነው። ይሄም ዋነኛ የፍልሰት ገፊ ኃይል ይሆናል። ስደተኛና ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር በዘመነ ወያኔ ከምንግዜውም በላይ ከፍቶ ይገኛል። በአንድ ሲምፖሲየም ላይ የቀረበ ጥናት እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ 75% የተማረ የሰው ኃይሏን በአስደንጋጭ ሁኔታ አጥታለች። በአብዛኛው የጤና ባለሙያዎች፣ መሃንዲሶችና ሳይንቲስቶች በአደጉ ሃገራት ጥገኝነት ለመጠየቅ ከኢትዮጵያ ይወጣሉ። ‘መንግስት’ እንደሚለው ይህ የሚሆነው የተሻለ ኑሮን ከመፈለግ ነው። አስገራሚው እውነታ ግን ምንም’ኳ ባለሙያዎች ቢሆኑም ከምርጫቸው ውጪ ያለ ሥራ የሚያገኙ በመሆኑ ከሙያቸው ጋር ተያያዥነት ያለው ሥራ አይሠሩም። በሚኖሩበት ሃገርም አንዳንዱ የጤና ባለሙያ የታክሲ ሹፌር ሲሆኑ፣ አንዳንዶች መሃንዲሶች አስተናጋጆች ይሆናሉ፣ ሌላም ሌላም። የተሻለ የፖለቲካ ክበብ ቢኖር ኖሮ በእርግጠኝነት ይህ የባለሙያዎች አስደንጋጭ ቁጥር ይቀንሳል ሃገራቸውንም ያገለግላሉ።

በመሆኑም ጎልማሳውም ሆነ ተተኪው ትውልድ የተሻለ ነገን ለመጠበቅ በመንግስት ላይ እምነት የለውም። የማይፈልጉትን መንግስትም በምርጫ የማስወገድም ምኞት የማይታሰብ ነው። ስለሆነም ይህ በህልማቸውና በተስፋቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ለማሳደሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ትውልዱም በየትም ቦታ ተስፋ እንደሌለ ሲረዳ ጠቅላላውን በአንድላይ ለቆ መጥፋት የተሻለ እንደሆነ ሊያስብም ይችላል። የእርሱ እኩያዎች ሌላው ዓለም ላይ ዲሞክራሲን ሲለማመዱ ሰብአዊ መብት ሲከበርላቸው ሲያይና በእርሱ ዘንድ ግን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ሲዋረዱና የተለየ ሃሳብ እንደ ጠላት ሲያስቆጥር ያለጥርጥር ያ ትውልድ ሃገሩን ለጥሩ ነገር ሲል ጥሎ መሸሹ አይቀርም።

በዚህ ሁሉ የመሸሽና የስደት ሕይወትም ለጆሮ የሚሰቀጥጥ፣ ለዐይን የሚያጸይፍና ለህሊና እርፍት የሚነሣ ችግሮችን እንሰማለን። አሁን በያዝነው ወር እንኳ ከሁለት ዓመት በላይ የሆናቸው ስደተኞች ጨምሮ የማሊ መንግስት 119 ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እስርቤት አስገብቷቸዋል። ስለመውጣታቸው የማይታሰብ ነው። ወደ ሃገራቸው ለመመለስም በቂ ገንዘብ የለኝም ስትል አውጃለች።

የስደት መዳረሻ የሆኗቸው ሃገራትም ከመንግስት ጋር በገቡት የጎንዮሽ መወዳጀት ወይም ከራሳቸው መንግስት ፍላጎት ወደ የመጡበት መመለስ የተለመደ ከሆነ ከራርሟል። በተለይ ኢትዮጵያውያን-ምክንያቱም ስለዜጋው ግድ የሚሰጥው ‘መንግስት’ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሌለ። በሕገ ወጥ መንገድ የኬንያን ድምበር ተሻግራችሁዋል በመባል የተከሰሱ ከ28 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዉያን ኦሮሞ ስደተኞች ወደ አገራቸዉ እንዲመለሱ የማርሳቢት ፍርድ ቤት ወስኗል። ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (UNHCR) ስደተኞቹ ጥገኝነት እንዲያገኙ ለኬንያ መንግስት ያቀረበዉ ጥያቄ አንድ ስደተኛ ከማስጠልል በስተቀር ተቀባይነት እንዳላገኘ ተናግሯል። እንዲመሰሱ የተደረጉት ስደተኞች ግን አሁን ያሉበት ሁኔታ አልታወቀም። በአስርቤት የሚገኙትም በርሃብ አድማ ውስጥ ለመጮህ ከመሞከር ባለፈ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብም የረዳቸው ነገር የለም።

ታንዛንያና ኬንያም መሪ የሌላቸው ሕዝቦች በሆኑት ኢትዮጵያውያን ይነታረካሉ። ታንዛንያ ወደ ኬንያ ድንበር አውጥታ ስትጥል ኬንያ ደግሞ ውሰጅልኝ ትላለች። በዚህ ሁሉ ውስጥ አለው የሚል ተቆርቋሪ ለመስማት መሞከር የወያኔን ሬሳ መጠበቅ ወይም ማግኝት ማለት ነው። 

በያዝነው ዓመት ኅዳር ወር ላይ የ253 የኢትዮጵያ ስደተኞች ከታንዛኒያ ወደ አገራቸው የመመለሳቸው ዜና እንዲህ ተዘግቧል። የመንግስት ቱሪናፋ የሆነ ጣቢያ በመሆኑ ዜጎቹን ህገወጥ እያለ ቢጠራም ቅር አልተሰኘም።

በታነዛኒያ እና ደቡብ አፍሪካ በህገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ከሄዱት 453 ስደተኞች መካካል 253 ያህሉ ናቸው በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ የገቡት። ተመላሽ ኢትዮጵያውያኖቹ ለጉዞ ከ80 እስከ 120ሺ ብር ለህገወጥ ደላሎች ከፍለዋል። ሁሉም ከስደት ተመላሾች ወንዶች ሲሆኑ፥ አብዛኞቹም ከደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማና አጎራባች ከተሞች በህገወጥ መንገድ ከአገር የወጡ ናቸው ተብሏል። ከእነዚህ ውስጥ ከ30 በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ18 በታች የሆኑ ታዳጊዎች ናቸው። ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያዊያኑ በጉዟቸው ወቅት ከፍተኛ ስቃይና ፈታኝ ሁኔታዎች እንደገጠሟቸው የተናገሩ ሲሆን፥ አንዳንዶቹም ከደረሰባቸው መከራ ብዛት የተነሳ በበረሃ ለህልፈት መዳረጋቸውንም ነው የተናገሩት። በአለም አቀፉ የፍልሰት ተቋም (አይ ኦ ኤም) እና በኢፌድሪ የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ትብብርና ድጋፍ አማካኝነት 253 ስደተኞች ዛሬ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን፥ በቀጣይ ሳምንትም 200 ያህል ስደተኞች ወደ አገራቸው እንደሚገቡም ነው የሚጠበቀው።

በየበሃሩ የሚተፉና በየበረሃው የሚወድቁትን የትየለሌ ኢትዮጵያውያን ጎልማሶችና ተተኪዎችን ታሪክ ይቁጠረው። በየመን እየደረሰ ያለው ሰቆቃ “በየሜዳው ወድቆ ፈላጊ ያጣው ውሻና የሐበሻ ዜጋ ነው” እስኪባል ቢደርስም ቢሆንም አሁንም ቀጥሏል። ሳውዲ አረቢያ ከመቶ ሺህ የሚበለጡ ለሥራ የፈለሱ ስደተኞችን አባራለች። አሳዛኙ ነገር እነዚህ ከስደት መዳረሻቸው ተገደው የሚመለሱ ዜጎች በሃገር ቤት አለመገኝታቸው ነው። ወደ ዛው ማለቂያ ወደል ሌለው ችግር የሞላው ስደት ጉዞ ላይ ናቸውና።

ከሃገር የሚወጣውን ለአፍታ አስቀምጠን ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰውን ብናይ እንኳ ከተመሳሳይ ትንታኔ መድረስ እንችላለን። Journal of global health perspective የኢትዮጵያውያን ከገጠር ወደ ከተማ የመፍለስ ሂደት ትንታኔ በሰጠበት ጽሑፉ ላይ እንዳስቀመጠው

ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረጉ ፍልሰቶች ዋነኛ ምክንያት 73% የሆኑት የእርሻ መሬታቸው አነስተኛ መሆን፣ የማዳበሪያ ዋጋና የግብርና ግብዓቶች ወጪ ከፍተኛነትና ዝቅተኛ ምርት ምክንያት በቂ የሆነ ምግብ አለማከማቸት ሲሆን አብዛኛዎቹ ፈላሾች (73%) ከአንድ ሄክታር በታች፣ 22%ቱ ከአንድ እስከ ሁለት ሄክታርና 6%ቱ ብቻ ከሁለት ሄክታር በላይ መሬት ያላቸው ናቸው። ሁለተኛው ዋነኛ ምክንያት ለ64% ቱ ከሚያመርቱት በቂ ገንዘብ ስለማያገኙ ወይም በመንደራቸው በቂ የጉልበት ሥራ ስለሌለ ተጨማሪ ገንዘብ ወይም የተሻለ ሥራ ፍለጋ ነው የሚፈልሱት። ከቀያቸው የሚፈልሱት በመንደራቸው በቂ ነገር ቢያገኙ ወይም በቂ የሆነ የመንግስት ድጋፍ ቢያገኙ ንቅንቅ እንደማይሉ ይገልጻሉ።

ባለፈው ዓመት በአልጀዚራ ላይ የወጣ If ethiopia is so vibrant why are young people leaving? (‘ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያ ለመኖር ምቹ ከሆነች ስለምን ይሰደዳል?’) የሚል ጽሑፍ እንዲህ ያስረዳናል። የሊቢያው ISIS ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን አንገት ሲቀላ የሚያሳየውን ቪዲዮ ሲለቅ በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው ጸረ-ስደተኛ እንቅስቃሴ ቀናት ብቻ ነበር ያስቆጠረው። በዚህም እንቅስቃሴ በትንሹ ሶስት ኢትዮጵያውያን ሲገደሉ ሌሎች ብዙዎች ቆስለዋል። አልጀዚራ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያያ ዜጎች በየመን የጦርነት ቀጠና ውስጥ መግቢያ ጠፍቷቸው እየባዘኑ እንደሆነ መግለጹ ይታወቃል። እንዲሁም ወደ 900 የሚሆኑ ሰዎችን ጭና ሚያዝያ 19 ከሊቢያ ዳርቻ ተነስታ ወደ አውሮፓ ድንበር ስትጠጋ የነበረች ጀልባ በመስጠሟ በሮቤዋ ኦሮሚያ ከተማና አጎራባቾቿ ያጧቸውን ዘመዶቻቸውን ሲቀብሩ እንደነበር ተዘግቧል።

ይህ ሁሉ አሳዛኝ ክስተት የተፈጠረው ኢትዮጵያ ፈጣን በሆነ ተአምር ምናልባት የኤዥያዎቹ ‘ታይገሮች’ ብቻ የሚነጻጸሩት የምጣኔ ሀብት ለውጥ (transformation) ባለፉት 10 ዓመታት ሲመዘገብ በነበረበት ወቅት ነበር። ታዲያ ምጣኔ ሀብቷ ከአፍሪካ በፍጥነት የሚያድግና ዲሞክራሲዋ እጎነነ ነው ተብሎ በሚጠበቅባት ኢትዮጵያ በሽዎች የሚቆጠሩት ወጣት ወንዶችና ሲቶቿ ሃገሯን ለቀው ለምን ይሰደዳሉ? በማለት ጽሁፉ ይጠይቃል።

በ2012 እ.ኤ.አ በለንደን መሰረቱን ያደረገው International growth center ባደረገው ጥናት የከተማ ሥራ አጥነት፣ images_12በገጠሩ የመሬት አልባነትና ለውጥ መፍጠር የሚችል የሥራ እድል ፈጠራ አለመኖር እየከፋ እንደመጣ መረዳቱን ገልጿል። “ምንም እንኳ ትምህርትን ለማዳረስ የሚታይ ለውጥ ቢኖርም ቅሉ ለአዲሶቹ ተመራቂ ሥራ ፈላጊዎች የሚሆን የሥራ እድል ፈጠራ እምብዛም የለም” ይላል ጥናቱ።

በሊቢያ ከተሰዉት ወጣቶች ቢያንስ በእጅ የሚቆጠሩት ከኮሌጅ የተመረቁ ናቸው። ሳውድ አረቢያ መቶሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን አባራለች። ከአፍሪካ ሃገራት ከፈተኛውን የወጣት ኃይል የያዘችው ኢትዮጵያ ከግብርናና ከንግድ ቀጥሎ መንግስት ዋነኛ ሥራ ቀጣሪ ነው። እንደ ሰብአዊ መብት ጠባቂው (HRW) 2011 ዘገባ “ለዘር፣ ለማዳበሪያ፣ መሣሪያዎችና ብድር. [. . .] ለመንግስት ሥራ፣ ለትምህርት እድልና ለምግብ ድጋፍ” ብዙውን ጊዜ በኢህአዴግ ደጋፊነት ላይ የተመረኮዘ ነው። ይህ የወጣቱ ስደት ግን በምጣኔ ሀብትና የሥራ እድል ማጣት ላይ ብቻ የተመረኮዘ አይደለም። እኚህ ሁኔታዎች ኢንተርኔትና አማራጭ የመረጃ ምንጭ ከመከልከልና ከመቆጣጠር ባጭሩ መንግስትና ካለማመን ጋር የተዛመዱ ናቸው። የአልጀዚራ ጽሑህ “አብዛኛዎቹ ፈላሾች ተጽእኖውን (persecution) በመሸሽ የሄዱ የፖለቲካ ስደተኞች ናቸው።” ይላል።

የኢትዮጵያውያን የስደት መዳረሻ የሆኑት ሃገራት ዩኒሴፍ ባዘጋጀው የ2013 እንዲሁም የስደተኞች ማእከል የኢትዮጵያ የፍልሰት ዘገባ መሰረት በኬንያ 22, 221 ፣ በአሜሪካ 10, 508፣ በደቡብ ሱዳን 5,891፣ በደቡብ አፍሪካ 5,538ና በየመን 7,000፣ ግብጽና ሱማሊያ በእያንዳንዳቸው ወደ 3,000 ተመዝግበው ይገኛሉ ይላል። ይህ ቁጥር የሚያመለክተው በስደተኝነት ተመዝግበው ያሉትን ብቻ ነው። መረጃና ማስረጃ የሌላቸውን ቤት ይቁጠረው። Migration in Ethiopia: History, Current Trends and Future Prospects የሚለው የማሳቹሴት ዩኒቨርስቲ ተከታታይ የሃገራት ዘገባ ላይ እንደሚያሳየው ከምስራቅ አፍሪካ አጠቃላይ ስደተኞች ሶስት እጁን ኢትዮጵያውያን ብቻቸውን ይሞሉታል። (ገጽ 11) የዚህ ሁሉ ማጠቃለያ የዚህ ጥናት ማጠቃለያ ይሆነናል “የኢትዮጵያውያን ዋና የስደት ምንጭ የፖለቲካ ተጽእኖ political repression ፣ ተገዶ መመለስ forced repatriation ፣ ተገዶ መፍለስ forced resettlementና ድርቅና ርሃብ ናችው።” (ገጽ 35፣ 2009) እነዚህ ሁሉ ውስጥ ሰፊው እጅ የግንቦታውያን ‘መንግስት ነኝ’ ባይ ነው።

 

የዘመነ ግንቦታውያን መራራ ፌሬ እንደዜጋ አለመቆጠርና ክብር ማጣት ብቻ አይደለም። ይህ ዋነኛው ጉዳይ ሁኖ አነሣነው እንጂ። ይቆየን–

 

 

Leave a comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

Start a Blog at WordPress.com.

Up ↑